“የመተካካት” ትምህርት ከሰሜን ኮሪያ

“መተካካት” ስለተሰኘው የሰሞኑ ማዘናጊያ ትክክለኛ ትርጉም ለመረዳት ሰሜን ኮሪያን መመልከት ይበጃል።

የሰሜን ኮሪያው ኪም ኢል ሱንግ ከጥንት ነገሥታት በባሰ መንገድ አገራቸው እንደግል ሃብታቸው፤ ህዝቡን ደግሞ እንደግል አገልጋዮቻቸው ገዝተዋል። የአገሪቱን ሬድዮኖችን፣ ቴሌቪዥኖችንና ጋዜጦችን እንዲሁም ወታደርና ሰላይ በመጠቀም የገነቡት ተክለ ሰውነት ከሰው ዘር የተለዩ ድንቅ የሆነ ልዩ ፍጡር መስለው እንዲታዩ አድርጓቸዋል። አድናቂዎቻቸው “በዓለም ላይ የእሳቸውን ያህል ታላቅ መሪ ኖሮ አያውቅም፤ ወደፊትም አይኖርም” ብለው አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ። “ታላቁ መሪ” የሚሉ ቃላትን ከስማቸው ማስቀደም ግዴታ ነው። የልደት በዓላቸው የአገሪቱ ብሄራዊ በዓል ነው።

እኚህ ሰው በ1994 እአአ ሲሞቱ የኮሪያ የዘለዓለም ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ። ለዘለዓለማዊ ፕሬዚዳንትነታቸው የህግ መሠረት ለመሥጠት በ1998 ህገመንግሥቱ ተሻሻለ። በተሻሻለው ህገመንግሥት የፕሬዚዳንትቱ ሥልጣን ከህገ-መንግሥቱ ወጥቶ ሥራው በሌሎች እንዲሸፈን ተደረገ። ስለሆነም ዛሬም የሰሜን ኮሪያ ፕሬዚዳንት በህይወት የሌሉት ኪም ኢል ሱንግ ናቸው።

ፕሬዚዳንቱ ከሞቱ በኋላ በሥራ ገበታቸው ላይ ለመገኘት “ስላልተመቻቸው” የእለት ለእለት ሥራቸውን “በውክልና” በመሥራት ላይ የሚገኙት የፓርቲው ፀሃፊና የጦሩ አዛዥ የሆኑት ልጃቸው ኪም ጆንግ ኢል ናቸው። ኪም ጆንግ ኢል “ፕሬዚዳንት” ተብረው አይጠሩ እንጂ ሙሉ የመንግሥት ሥልጣን በእጃቸው ነው። አባታቸው በህይወት እያሉም ኪም ጆንግ ኢል “ተወዳጁ መሪ” ተብለው ነበር የሚጠሩት። ከአባታቸው ሞት በኋላ ደግሞ “የላቁ መሪ” ተባሉ።

አሁን ኪም ጆንግ ኢል በእድሜ ገፍተዋል፤ የጤናቸው ሁኔታም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ከሁለት ዓመት በፊት በአሳሳቢ ሁኔታ ታመው ነበር። ይህን እግምት ውስጥ በማስገባት ይሆናል በያዝነው ወር የሃያ ሰባት ዓመት ልጃቸውን የጄኔራልነት ማዕረግ በመስጠት ለተከታይ “ተወካይ ፕሬዚዳንትነት” መታጨቱ ህዝብ እንዲገምት ተደርጓል፤ ከስሙ በፊትም “እጅግ ብልሁ ጓድ” የሚል መጠሪያ እንዲጨመር ተደርጓል።

ይህ ልብወለድ የፈጠራ ታሪክ አይደለም። ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው። እንዲያውም በዝርዝር አልተነገረም እንጂ ከዚህም በላይ የሚገርሙ ጉዶች አሉ። “አብዮታዊ ዲሞክራቶች” እንዲህ ዓይነቶች ናቸው። እኩልነትና ብልጽግናን ሲሰብኩ የኖሩት የሰሜን ኮሪያ አብዮታዊያን በተግባር የሚያደርጉት ይህ ነው። ሰሜን ኮሪያ በአቅሟ በላይ የጦር ኃይል ያደራጀት አገር ናት። የዚች አገር ገዢዎች በጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ጎረቤት አገሮችን – በተለይም ደቡብ ኮሪያን – ማሸበራቸው እንደ ጀብድ ይቆጥሩታል። ከወታደራዊ ጀብድ ውጭ ግን ሰሜን ኮሪያ በምግን ራሷን መቻል ያቃታት ድሃ አገር ናት። በፓሊሶች፣ ወታደሮችና ሰላዮች ታፍኖ ባይያዝ ኖሮ የአገሪቷ ህዝብ ወደ ደቡብ ኮሪያ እና ሌሎች አገሮች ነቅሎ በተሰደደ ነበር።

አገራችንን እየገዛ ያለው የትግራይ ኦሊጋርሂ የሰሜን ኮሪያው ኪም ቤተሰብ አምሳያ ነው። ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያ አምሳያዎቹ በመተካካት ስም ኦሊጋርሂውን እያጠናከረ እንደሆነ በተግባር አይተነዋል። በአሁኑ ሰዓት የህዋህት የሥራ አስፈፃሚ አባላት መለስ ዜናዊ፣ አዜብ መስፍንና ዘመዶቻቸው ናቸው። ብልህ እነሱ ብቻ ናቸው፤ የአመራር ችሎታ ያለው እነሱ ቤት ውስጥ ብቻ ነው። ስለዚህም ሥልጣን ወደ መለስና አዜብ ቤተሰብ ይሰበሰባል። እነሱ ሲያረጁም ልጆቻቸው እንዲተኳቸው ይደረጋል። ለትግራዩ ኦሊጋርሂ “መተካካት” ማለት ይህ ነው።

ይህንን ድምዳሜ የሚጠራጠር ካለ በቅርቡ የተደረጉትን የህዋህትና አጨብጫቢዎቹ “የመተካካት የመጀመሪያ ሂደት” ውጤትን ያስተውል። እነዚህ ግብዞች በቅርቡ ካደረጓቸው ስብሰባዎች ውጤቶች ሁለት ዓበይት ነገሮች ነጥረው ወጥተዋል።

  1. በህዋህት ውስጥ የመለስና አዜብ የሥጋና የጋብቻ ዘመዶች ተጠናክረዋል፤
  2. በሌሎች አጨብጫቢ ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ ፕወዛ ተደርጓል።

እነዚህ ሁለት ነገሮች በአንድነት ሲታዩ የመተካካቱ ግብ ሥልጣንን በመለስና አዜብ ዘመዶች መዳፍ ውስጥ ማስገባት ነው። በሎሌ ድርጅቶች ውስጥ ደግሞ በስልጣን መደላደል እንዳይኖር ከፊሎቹ ማሰናበት፤ ቀሪዎቹን ማሸጋሸግ ተደርጓል። የኦሮሚያ፣ የአማራና የደቡብ አጫፋሪዎች በቀላሉ የሚወረወሩ ጠጠሮች መሆናቸው መገንዘብ ያቃቸው ግብዞች መሆናቸው አሳፋሪ ነው።

በመተካካት ስም ሥልጣን በአንድ ቤተሰብ የሚያዝበት ሥርዓት አገራችን ወደባሰ ድህነትና ጭለማ እየመራት እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል። በመተካካት ስም የትግራዩን ኦሊጋርሂ ከመጠናከሩ በፊት መባረር ይኖርበታል፤ ለዚህም ሁላችንም ጠንክረን መታገል ይጠበቅብናል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!