የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከእስር መለቀቅ አስመልክቶ ከግንቦት 7 የነፃነት የፍትህ እና የዴሞክራሲ የወጣ መግለጫ

የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አባላት ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2003 ዓም የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ከእስር የመፈታት ዜና  የሰማነው በታላቅ ደስታ ነው። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በድጋሚ እስር ውስጥ በነበረችባቸው 646 የግፍ ቀናት በሙሉ በመንፈስ አብረናት ነበርን። እነዚህ 646 ቀናት እጅግ አፋኝ ህጎች የወጡበት፣ ወያኔ ህገወጥ ስልጣኑን በህገወጥ ምርጫ የማረጋገጥ ድራማ የተጫወተበት፤ የፓለቲካ ምህዳሩ እጅግ የጠበበት፤ የመሬትና የንብረት ዘረፋ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መጠን የተስፋፋበት፤ በአጠቃላይ የትግራዩ ኦሊጋርሂ ዘረኛ ሥልጣኑን ወደ አንድ ቤተሰብ ጠቅልሎ ያስገባበት ወቅት ነበር።

በዘረኛው እስር ቤት የደረሰባት እንግልትና ሰቆቃ ከፍተኛ እንደሆነ እናውቃለን። ይኸ መስዋዕትነት የከፈለችው ለእውነት ስትል መሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ወ/ት ብርቱካን የከፈለችው መስዋትነት በአገራችን የነፃነት ትግል ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለን እናምናለን።

ስለሆነም ከሁሉ አስቀድሞ “እንኳን ከህፃን ልጅሽ ሃሌ፣ እናትሽ እና ሌሎች ቤተሰቦችሽ ጋር ለመቀላቀል አበቃሽ“ እንላለን። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንደከዚህ በፊት ሁሉ ለወደፊቱም በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ሁነኛና አዎንታዊ አስተዋጽዖ ይኖራታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።

በዚህ አጋጣሚ ልክ እንደብርቱካን ሚደቅሳ ሁሉ ያለአንዳች ወንጀል በወያኔ እስር ቤቶች በመሰቃየት ላይ ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን መኖራቸውን ለደቂቃም አንዘንጋ። እነዚህ የህሊና እስረኞች የሆኑት ወገኖቻችንን በሙሉ፣ ራሳችንና አገራችንን ነፃ ሳናወጣ ደስታችን የተሟላ ሊሆን አይችልም።

ደስታችን የተሟላ የሚሆነው፤ በአገራችን ህገወጥ እስር የሚያበቃው፤ የትግራዩ  ኦሊጋርሂ ከስልጣን ተባሮ በምትኩ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን አውቀን ቀበቶዓችንን እናጥብቅ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!