በአዲሱ የሊዝ አዋጁ ሕዝብ ተደናግሯል

(Reporter) — በቅርቡ የመሬት ሊዝ አዋጅ በፓርላማ ፀድቋል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድርም በዋና ዋና መንገዶችና ኪስ ቦታ ውስጥ ያሉ መሬቶች ሕንፃ እንዲሠራባቸው መመርያ አውጥቷል፡፡

በየቀበሌው የሚመለከታቸውን እየሰበሰበ የሚሠሩ ወይም የማይሠሩ መሆናቸውን በፊርማ እንዲያረጋግጡ እያደረገ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በእኛ በኩል የሊዝ አዋጅ ለምን ወጣ? ሕንፃ ሥሩ ለምን ተባለ? ብለን መቃወምም አንፈልግም፤ ግሩም መመርያና አዋጅ ነው ብለንም መደገፍ አንችልም፡፡ ከሁሉም በፊት የሚቀድመው አዋጁና መመርያው ለኅብረተሰቡ ግልጽ ስላልሆነለት እየተደናገረና እየተጨነቀ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት አዋጁም መመርያውም ምን እያሉ እንደሆነ በግልጽ ከሕዝብ ጋር በመቀራረብ ያስረዱ! ያብራሩ! ያወያዩ! ነው የምንለው፡፡

በሊዝ አዋጁ ዙሪያ ባለይዞታው ግለሰብ ልነጠቅ ነው ማለት ነው ወይ? ማውረስ አልችልም ማለት ነው ወይ? የገዛ መሬቴን በሊዝ ግዛው እየተባልኩ ነው ወይ ያለሁት? ወዘተ እያለ በጣም እየተጨነቀና እየተረበሸ ነው፡፡

መሬት መግዛት የሚፈልገው ደግሞ ለባለይዞታው ከከፈልኩ በኋላ እንደገና በሊዝ ለመንግሥት ልከፍል ነው ወይ? ሁለት ክፍያ ከሆነ ዋጋው አይንርም ወይ? እኔ በውድ የምገዛው ከሆነና ግንባታ ካከናወንኩበት በኋላ እኔም በውድ ዋጋ መሸጥ አለበኝ ማለት ነው ወይ? እያለ እየተደናበረ ነው፡፡

ከአምስት መቶ ካሬ ሜትር በላይ ይወሰዳል ወይም በሊዝ የሚያዝ ይሆናል የሚለውም መደናገር እየፈጠረ ነው፡፡ እስካሁን የያዝኩትስ ምን ይሆናል ማለት ነው? መገንባት ብፈልግ አልችልም ማለት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡

በአተገባበሩ ላይም ለመሆኑ ካሁን በኋላ ለሚደረገው ሽያጭና ግዥ ነው ወይስ ላለፉት ሃያ ዓመታት የነበሩ ይዞታዎችም ወደኋላ ተመልሰው ክፍያና የሊዝ ውል ሊፈጸምባቸው ነው? ካሁን ቀደም የገዛና የገነባ እንደገና ወደኋላ ተመልሰህ ክፈል ሊባል ነው ወይ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡

የሊዝ አዋጅ ያስፈልጋል፡፡ በየጊዜው እየተከታተሉ ግልጽ ማድረግና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን ማካተትም ያስፈልጋል፡፡ አዋጁ ለአገርና ለሕዝብ ይጠቅማል ወይ? አዋጁ ለልማት ዋስትና ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳ እንደሆነ እንጂ የአዋጁን አስፈላጊነትና ጠቃሚ መሆን ማረጋገጥ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ሕዝብ አዋጁ ጠቃሚ ነው ብሎ ሊቀበለው የሚችለው ደግሞ ሲብራራለት፣ ሲወያይበትና ሲያምንበት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታወጀ እንጂ ለሕዝቡ ግልጽ የሚያደርግና የሚያብራራ አልተገኘም፡፡ በዚህ ምክንያትም ሕዝቡ ፍርኃት፣ ጭንቀት፣ መደናበርና መደነጋገር በዝቶበታል፡፡

ውይይት ከተደረገበት ጠቃሚ ነው ወይም ጠቃሚ አይደለም ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ ይህ ይጨመር ይህ ይቀነስ ማለትም ይከተላል፡፡ ይህ እንዲሆን የሚመለከታችሁ የመንግሥት አካላት አስረዱ! አብራሩ! አወያዩ! እንላለን፡፡

ያለው መደናገር በሊዝ አዋጁ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በሕንፃ ግንባታ ዙርያም መመርያው ላይ መደናገር አለ፡፡ ሕንፃ ካልገነባሁ እነጠቃሁ ማለት ነው? መገንባት ያለብኝ በስንት ቀን፣ ወር ወይም ዓመት ውስጥ ነው? ለመሆኑ የሚገነባውስ ባለ አራት ፎቅ ነው? ባለ ሰባት ፎቅ ነው? ባለስንት ነው? የሚል ጥያቄ አለ፡፡

በተለይም መገንባት የሚፈልግ ባለይዞታ ገንዘብን በሚመለከት ከዘመድ አዝማድ ለመወያየት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ለመሐንዲሶች ሥራ መስጠትና ዲዛይን ማሠራት አለ፡፡ የግንባታ ስምምነት አለ፡፡ የግንባታ ፈቃድ አለ፡፡ ማቴሪያል ማዘጋጀት አለ፡፡ ይህ ሁሉ ከባድ ሥራ እያለ የሚሰጠው ጊዜ በቂ አይደለም፤ እያቻኮሉን ነው የሚል ስሞታ ይደመጣል፡፡

አዲስ አበባ ዘመናዊ ገጽታ፣ መልክና ይዘት አይኑራት የሚል የለም፡፡ ውበት ማለት ሕንፃ ነው የሚል ትርጓሜ ብቻ እንዲሰፍን ባንስማማም፣ ከሕንፃዎች ጐን ለጐን መናፈሻዎችና አረንጓዴ አካባቢዎችም ያስፈልጋሉ፡፡ ለሕንፃ ግንባታ የተከለለ አካባቢ ይኑር ብንልም፣ የመኖሪያ፣ የኢንዱስትሪ የመዝናኛና የሥራ አካባቢዎች ይለዩ ባዮች ብንሆንም፣ አዲስ አበባን ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችንና ሙከራዎችን እንደግፋለን፡፡

ነገር ግን ምን እየተባለ እንደሆነ መደናገር አለና አሁንም የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥርያ ቤቶችና ኃላፊዎች እንዲያብራሩ፣ እንዲያስረዱና እንዲያወያዩ እንጠይቃለን፡፡

በየቀበሌው አወያያተን የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ አዎን ስብሰባዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የሕዝብ ጥያቄና አቤቱታ የቀረበቡባቸው ስብሰባዎች ስለሆኑ የሕዝብን ጥያቄ ይዞ መልስ አዘጋጅቶ ማብራራትና ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ጊዜው የኢኮኖሚ ችግር የሚታይበት ስለሆነ፣ ከምንም ጊዜ በላይ መገናኘት፣ መቀራረብና መወያየት ያስፈልጋል፡፡ መደማመጥ የግድ ይላል፡፡ የሕዝብን ጥያቄ ጊዜ ሰጥቶ ማዳመጥና መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል፡፡

ልማቱም በአንድ በኩል እንዳይደናቀፍ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝብን ከጐን አሰልፎና አሳምኖ ማልማት እየተቻለ፣ አላስፈላጊ መቃቃርና መራራቅ ፈጥሮ ልማትን ማደናቀፍ እንዳይኖር መጠንቀቅ የማይታለፍ ነው እንላለን፡፡

በተለይ በተለይ በመቀራረብ በርካታ ችግሮችን መፍታት እየተቻለ በመራራቅ ምክንያት ችግር እየተባባሰ ነውና እንጠንቀቅ፡፡

የሰሞኑን ሁኔታ ስናይ ደግሞ በሊዝ አዋጁና በሕንፃ ግንባታ መመርያ ዙሪያ ሕዝብ ተደናግሯል፤ ተደናግጧል፤ ተጨንቋልና የሚመለከታችሁ መንግሥታዊ አካላትና ኃላፊዎች አብራሩ! አስረዱ! አወያዩ!