ግንቦት 7 የፍትህ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ የወ/ት ብርትኳን ሚደቅሳን መፈታት አስመልክቶ መግለጫ አወጣ

ወ/ት ብርትኳን ሚደቅሳ ረቡእ፣ መስከረም 26፣ 2003 ቀን ከጠዋቱ 11 ሰዓት ላይ፤ ከ646 ቀናት እስር በኋላ ከቃሊቲ ወህኒ ቤት መውጣቷን ተከትሎ ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነፃነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ መግለጫ አውጥቷል።

ወ/ት ብርትኳን ሚደቅሳ ከቃሊቲ ልትወጣ እንደምትችል ባለፉት በርካታ ሳምንታት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮቹ ሲገልጹ ቢቆዩም፤ የኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት የሚመራው በአንድ ግለሰብ ስሜት ላይ ተመስርቶ መሆኑ ጉዳዩን በእርግጠኛነት ለመናገር አስቸጋሪ አድርጎት ሰንብቷል።

እስረኛዋ ወደ መኖሪያ ቤቷ እንዳመራች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ወጥተው ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላት ዘገባዎች አሳይተዋል። ከቃሊቲ መውጣቷን ተከትሎ በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን እየገለጹ ቢሆንም፤ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ከአሁኑ ጥያቄ እያነሱ ነው።

“መለስ ዜናዊ እራሱ ለፈጠረው ችግር መፍትሄ እየሰጠ ህዝቡ ጮቤ እንዲረግጥለት ይፈልጋል” ያሉን የፖለቲካ ተንታኝ፤ የዘረኛው አምባገነን አላማ የህዝባችንን ተስፋ እና ምኞት ዝቅ ማድረግ ነው ብለዋል። ይህንንም ሲያብራሩ፤ “የወያኔ ተስፋ፥ ህዝቡ ቀድሞውኑ በአገዛዙ ህገ-ወጥነት የታሰሩ ልጆቹ ከእስር ቤት ሲወጡ ታላቅ መሻሻል እንደተደረገ እየቆጠረ ሲደሰት ኢ-ፍትሃዊውን ስርአት የማስወገድ ተልኮውን እንዲዘነጋ ነው” ብለዋል።

ሌላ አስተያየት ሰጪ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መልክት፥ “ወ/ት ብርትኳን ከቃሊቲ መውጣቷ አዎንታዊ ነገር ቢሆንም፤ አገሪቷ ራሷ ትልቅ እስር ቤት በመሆኗ ከትንሽ እስር ቤት ወጥታ ወደ ትልቅ እንደገባች እንጂ ነፃ እንደወጣች ልናስብ አንችልም” ብለዋል።

ግንቦት 7 የነፃነት፣ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ፤ ወ/ት ብርቱካንን፥ “እንኳን ከህፃን ልጅሽ ሃሌ፣ እናትሽ እና ሌሎች ቤተሰቦችሽ ጋር ለመቀላቀል አበቃሽ” ብሏል። መግለጫው ጨምሮም፥ “ደስታችን የተሟላ የሚሆነው፤ በአገራችን ህገወጥ እስር የሚያበቃው፤ የትግራዩ  ኦሊጋርሂ ከስልጣን ተባሮ በምትኩ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲሰፍን ብቻ መሆኑን አውቀን ቀበቶዓችንን እናጥብቅ” ሲል አሳስቧል።

ግንቦት 7 ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል ከዚህ ላይ ያንቡ።