ወያኔ “ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ እፈጥራለሁ” ማለቱ በአዲስ አበባ የስላቅ ርእስ ሆኗል

ከሰሞኑ የወያኔ ባዶ ዲስኩሮች ውስጥ አንዱ፥ “የትምህርት ካሪኩለምን በማደስ ትምህርት ቤቶች ‘ሙስናን የሚጸየፍ ትውልድ’ እንዲፈጥሩ ማስቻል” የሚል እንደሆነ የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ባደረሰው መረጃ አሳውቋል።

ተያይዞ የደረሰን መረጃ እንደሚያሳየውም፥ የወያኔ አገዛዝ በሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ ላይ ፈጽሞ እምነት ያጣው ህዝብ በአዲሱ ዲስኩር ላይ ሲሳለቅ ሰንብቷል። የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ያናገራቸው አዲስ አበቤዎች፥ “ምነው የወያኔ ባለስልጣናት እራሳቸው ሙስናን ተጸይፈው ቢያሳዩን?” ሲሉ ጠይቀዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረውም፥ ተማሪዎች ከወሬ ይልቅ በምሳሌ ስለሚማሩ ባለስልጣናቱ ከራሳቸው ቢጀምሩ የበለጠ አስተማሪ ይሆናል ብለዋል።

የወያኔ አገዛዝ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት ጥራት በፍጥነት እያሽቆለቆለ እንደሄደ በሰፊው የሚነገር ሲሆን፤ በተለይም አገዛዙ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሆን ብሎ ያስፋፋው ባህል ከፍተኛ የሆነ የሞራል ዝቅጠትን እና ሙስናን እንዳንሰራፋ ይታወቃል። በርትቶ በማጥናት ጥሩ ውጤት ከማምጣት ይልቅ የገዢው ቡድን አባል መሆን እና ዘረኛውን አገዛዝ በስለላ ስራ ማገዝ ያስሸልማል የሚለው እምነት በተማሪዎች ውስጥ እንደሰረጸ ይነገራል።

ከትምህርት ቤቶች ውጪ፥ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ያለው ሙስና ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰም ይታወቃል። አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች “ጉቦ ሳይሰጥ እርምጃ እንኳ መራመድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” ሲሉ ለግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ስሞታቸውን እንዳሰሙ ባለፈው ነሐሴ መዘገባችን ይታወሳል።