መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ “በህዳሴው ዋዜማ ላይ እንገኛለን” በማለት በሚቀልዱበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዳቦ እጥረት እየታመሰች መሆኗ ተዘገበ
ወያኔ መላውን አገራችንን በመሳሪያ ሃይል በመቆጣጠር ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ስልጣን ሲቆጣጠር የኢትዮጵያን ህዝብ በመጀመሪያው 10 አመት ቢያንስ በቀን ሶስት ጊዜ እንዲበላ እናደርገዋለን በማለት የሃሰት ተስፋ የሰጠ ሲሆን መለስ ዜናዊና ጥቂት ግብረአበሮቹ በተከተሉት የአገር ሃብት ምዝበራና ዘረፋ ምክንያት ከ20 ዓመታት የወያኔ የስልጣን ዘመናት ቦኋላ ዛሬ አገራችን ታይቶ በማይታወቅበት የድህነት አረንቋ ውስጥ እንደገባችና በቀን አንድ ጊዜ እንኳ ለመመገብ የማይችለው የህብረተሰባችን ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እጅግ እየጨመረ መምጣቱ ታወቀ።
ቀደም ሲል በድህነት ወለል ላይ ነው ይባል የነበረው የህብረተሰብ ክፍል ሳይቀር በቀላሉ ያገኝ የነበረው ዘይትና ሳሙና ዛሬ እንደ ቅንጦት ዕቃ እየተቆጠረ እንደሆነ የሚናገረው የአገራችን ህዝብ በተለይ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ በዳቦ እጥረት ጭምር እየታመሰ እንደሚገኝ ከአዲስ አበባ የሚወጡት ዜናዎች ያመለክታሉ።
የችግሩን መንሰኤ በግልጽ ለመናገር ወያኔ የሚያደርሰው የፖለቲካ ጥቃት ስጋት የፈጠረባቸው የአዲስ አበባ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ችግሩ የተከሰተው በስንዴ ዱቄት አለመኖር ነው ሲል የቆየ ቢሆንም የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት የተባለው በመጋዘን ውስጥ በቂ ክምችት አለ በማለት ለማስተባበል መሞከሩ ብዙዎችን እያስገረመ ነው።
አድስ አበባ ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረት የሚከታተሉ ዘጋቢዎቻችን የስንዴ ዋጋ ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ እጅግ እየናረ መምጣቱን የገለጹ ሲሆን የህዝብን ብሶት ለማቀዝቀዝ ሲባል ወያኔ በመጋዘን አለኝ ሲል የነበረውን ክምች ላለፉት አምስት ወራት በንግድ ሚኒስቴር አማካይነት ለየ ዳቦ ቤቶች በረሽን መልክ ሲያከፋፈል እንደቆየ ይናገራሉ። ሆኖም የነበረው ክምችት እየተሟጠጠ በመምጣቱ ከመስከረም ወር ጀምሮ ዳቦ ቤቶች በከፍተኛ ደረጃ የዱቄት እጥረት አጋጥሟቸዋል ተብሎአል።
የዱቄት እጥረቱን ተከትሎ በርካታ ዳቦ ቤቶች የዳቦ ግራምን እስከመቀነስ እንደደረሱ የዘገበው ዘጋቢያችን የዳቦዎች መጠን ያለመጠን ማነስ እያነጋገረ ባለበት ሰዓት ይባስ ብሎ በመዲናይቱ ከሚገኙ ዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች መካከል አብዛኞቹ ስራቸውን እንዳቆሙ ገልጾአል። የሸዋ ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሀዬ ዘሙ፤ በዱቄት እጥረት ምክንያት በአዲስ አበባ ውስጥ ካሏቸው 65 ዳቦ ቤቶች 45 ቱን መዝጋታቸውን እንዳስታወቁና በተጨማሪ በቀን እስከ 350 ቶን ዳቦ የመጋገር አቅም ያለውን የዳቦ ማምረቻ ኢንደስትሪያቸውን መዝጋታቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።