ወያኔ የራስ ዳሸን ተራራ የሚገኝበትን የሰሜን ጎንደር ወረዳ በትግራይ ክልል ሥር ለማስገባት እያደረገ ያለውን ሙከራ የበየዳ ነዋሪዎች መቃወማቸው ተዘገበ
በተፈጥሩአዊ መስህብነቱ በአለማችን የሚታወቀው የራሽ ደጀን ተራራ በሚገኝበት በዬዳ ወረዳ አካባቢ የሚኖሩ የሏሪ ቀበሌ ነዋሪዎችን፣ በትግራይ ክልል ውስጥ እንዲካተቱ ለማሳመን ለ7 ተከታታይ ቀናት የተደረገው ውይይት ሳይሳካ መቅረቱን ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ሳተካይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘገበ።
እንደ ኢሳት ዘገባ የትግራይ ክልል ባለስልጣናት የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወሩ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም፣ ህዝቡ ግን እኛ በታሪክ ተወቃሽ አንሆንም፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን አጥንታቸው የተቀበረው በዚሁ ቦታ ነው። ግዛቱ የማን እንደሆነ ይታወቃል። በማለት ጥያቄውን ውድቅ ማድረጋቸው ታውቁአል።
ከዚህ ቀደም ራስ ዳሸን ተራራ በትግራይ ክልል ይገኛል በማለት በመጽሀፍ መልክ ታትሞ መቅረቡን እንዲሁም ላለፉት ተከታታይ አመታት የራስ ዳሸን አካባቢን ህዝብ ወደ ትግራይ ክልል ለማስገባት ተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉን ያስታወሱት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሚታየው ግፊት ከዚህ በፊት ከታየውም የባሰ ነው ማለታቸው ተያይዞ የደረሰው ዘገባ አመልክቱአል።
ትግራይ አካባቢውን ለመውሰድ ለምን እንደፈለገ የተጠየቁት ነዋሪዎቹ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአካባቢው ለቆርቆሮና ለተለያዩ እቃዎች መስሪያ የሚሆን ከፍተኛ ማእድን በመገኘቱ ሊሆን ይችላል፤ ሲሉ ግምታቸውን ማስፈራቸውንም ኢሳት አክሎ ዘግቡአል።
የአካባቢው ወጣቶች የትግራይ ክልል እየፈጸመ ያለውን ተግባር በእጅጉ እየተቃወሙት ነው ያለው ኢሳት የበየዳ ወረዳ አካባቢ ህዝብ ሙሉ በሙሉ አማርኛ ተናጋሪና በታሪክም የጎንደር ግዛት መሆኑን ነዋሪዎች እንደሚናገሩ ገልጹአል።
እስካሁን አካባቢውን በጉልበት ለመከለል ጥረት አለመደረጉን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አሁን የሚየታው ሁኔታ ከቀጠለ በአካባቢው ግጭት ሊነሳ እንደሚችል ያስጠነቀቁ ሲሆን፣ ራስ ዳሸን ተራራ በትግራይ ክልል ይገኛል ተብሎ በእንግሊዝኛ መጽሀፍ ውስጥ መስፈሩን በማስመልከት የክልሉ መንግስት በስህተት የተፈጸመ ነው ቢልም፣ እስካሁን የማስተካከል ሙከራ አለመደረጉን ታዛቢዎች እንደሚናገሩ ታውቁአል።
የበየዳ ወራደ ቀድሞ በደባርቅ አውራጃ ውስጥ ይገኝ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን አንዳንድ ወገኖች ራስ ዳሸን ተራራም ሆነ በዙሪያው ያለው መሬትም ሆነ ማእድን የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ሆኖ እያለ፣ አላስፈላጊ የሆነ የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት ህዝቡ እንዲከፋፈል በማድረግ ላይ ያለው ዘረኛውና ከፋፋዩ አገዛዝ ነው ይላሉ።