በርካታ የሰራዊቱ አባላት የዘረኛና አፋኙን አገዛዝ በመቃወም የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ትህዴን) መቀላቀላቸው ተዘገበ
ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ በተለያዩ ቦታዎች ተመድበው የነበሩ 14 ወጣት የኢትዮጲያ ሠራዊት አባላት የዘረኛና አፋኙን የመለስ አገዛዝ በመቃወም ከትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ጋር መቀላቀላቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘገበ።
እንደ ኢሳት ዘገባ በምህፃረ-ቃል “ትህዴን” በመባል የሚታወቀው የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የወጣቶቹንና የወታደሮች ፎቶ አያይዞ ለኢሳት መግለጫ መላኩ የታወቀ ሲሆን በመግለጫው፤ የዘረኛው መለስን ሥርዓት ከድተው ወደ ትህዴን የተቀላቀሉት ወጣቶች፤ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ከትግራይና ከደቡብ ክልሎች የመጡ መሆናቸው ታውቁአል።
የፋሽስቱን አገዛዝ የከዱ የሰራዊቱ አባላት ስም ዝርዝርም፤ 1ኛ/ ወ/ር ብዙዓለም ሽፋራው እርቄ፣ 2ኛ/ አስር አለቃ ሁሴን መሃመድ አህመድ፣ 3ኛ/ ምክትል አስር አለቃ ቦጋለ ኩራቻ፣ 4ኛ/ ወታደር እድሪስ ሁሴን መሃመድ፣ 5ኛ/ አስር አለቃ ሁሴን ደመቀ ተገኘ፣ 6ኛ/ ምክትል አስር አለቃ ኢብራሂም ደግፌ ባንቲ፣ 7ኛ/ ወታደር ጸጉ ሃፍቶም መረሳ፣ 8ኛ/ አስር አለቃ ዋርሳው ባንቲ በሪሳ፣ 9ኛ/ ምክትል አስር አለቃ ታደመ ወይዳይ ጃጓድ፣ 10ኛ/ ወታደር አታኽልቲ ታረቀ ፍቃዱ፣ 11ኛ/ ፍስሃ ጸጋይ አውዓላ፣ 12ኛ/ ተወልደ መለስ መድሃንየ፣ 13ኛ/ አጸደ ማዓሾ ገ/ጻዲቕ፣ እና 14ኛ/ ምሩፅ ዕቑባሚካኤል ገብሩ መሆናቸውን ተያይዞ የወጣው ዘገባ ያመለከተ ሲሆን ወታደሮቹ የነበሩበት እዝ፣ ክ/ጦር፣ ሬጅመንት፣ ሻምበልና፣ የመቶኛ ጓዳቸው በድርጅቱ መግለጫ ላይ በዝርዝር መመልከቱን ኢሳት ዘግቡአል።
ወጣቶቹ “ትህዴን”ን ለመቀላቀል የወሰኑት፤በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት የህዝብን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የማያከብር በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ የተናገሩ መሆኑ የታወቀ ሲሆን “ፀረ-ህዝቡ ስርዓት በብሄር ብሄረሰቦች ላይ እየፈጸመው ያለው በደልና ግፍ ከመቸውም ግዜ በላይ እየከፋ ነው”ያሉት ምክትል አስር አለቃ ሀሰን ደመቀና ምክትል አስር አለቃ ታደመ ወይዳይ፤ በተለይ ባለፈው ወር በሀዲያ በተነሳው ግጭት ብዙ ሰዎች መገደላቸውና በርካታዎች ያለበደላቸው መታሰራቸው እንዳሳዘናቸው መግለጻቸውን ኢሳት ዘግቡአል።
“የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች ሰራዊቱን በብሄር፣ በማእረግና በጥቅማጥቅም በመለያየት የስልጣን እድሜያቸውን እያራዘሙ ናቸው”ያለው አስር አለቃ ሁሴን መሀመድ አህመድ በተለይም ከ1997 ምርጫ በሁዋላ የተቀጠሩ አዲስ ምልምሎችን በማይጨበጥ ተስፋና በጥቅማጥቅም ለማታለል ጥረት ቢያደርጉም፤ አብዛኛው ሠራዊት በሥርዓቱ ላይ እምነት እንዳጡ መረጃዎችን በመጥቀስ መናገሩ ተዘግቡአል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ትህዴን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመምጣቱ ለገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ስጋት በሚሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱ ታውቁአል።