ጥሪ በመለስ ዜናዊ ጎራ ለተሰለፉ ባለሙያዎች
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለባለሙያዎች ከፍተኛ ክብር አለው። ሆኖም ግንቦት 7 ነፃነት በሌለበት ሃገር ውስጥ ሙያም ሆነ ባለሙያ ክብር የማይሰጣቸው፤ በክፍያም ሆነ በማስገደድ የአምባገነኑ ፈቃድ ፈፃሚዎች እንደሚሆኑ ይገነዘባል። ነፃነት በሌለበት ሃገር ባለሙያዎች ተገደው አሊያም ለመኖር በሚል ሰበብ ገንዘብ ለሚከፍል የጊዜው አምባገነን ሥርዓት በሎሌለነት ያድራሉ። ግንቦት 7 እንዲህ ያለው ሁኔታ በሀገር ላይ የሚያደርሰውን ከፍተኛ ጉዳት ስለሚረዳ፣ ባለሙያዎች ከተጽዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ የሙያ ግዴታቸውን እንዲወጡ ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው ይገባል ብሎ በጽኑ የሚያምን ድርጅት ነው። የሚታገለውም ለሙያ ነፃነት መረጋገጥ ጭምርም ነው።
ሙያን ከአፋኝ የፓርቲ ፓለቲካ ተጽእኖ ነፃ ማድረግ ተገቢ የመሆኑን ያህል የሙያን ክብር አዋርዶ ለገንዘብ ብቻ ሲባል በገለልተኝነት ሽፋን ከአፋኝ ሥርዓትጋር መተባበርን ግን አጥብቀን ልንታገለው የሚገባን ጉዳይ ነው። የባለሙያዎች ግዴለሽነት የመለስ ዜናዊ አገዛዝን እስካሁን ካቆሙት ነገሮች አንዱ ነው። ለፍትህና ነፃነት ግዴለሽ የሆኑ ባለሙያዎች መኖራቸው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ባለሙያዎቹ የቆሙለትን ሙያ ሳይቀር ለማዋረድ የሚያስችል አቅም ሰጥቶታል።
ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል:-
- ብዙ ድሆች ከእለት ጉርሳቸው ቀንሰው ያጠራቀሙት ገንዘብ ጥቂት የገዥው ቡድን አባላት በብድር መልክ እየወሰዱ በአንድ ምሽት ሲከብሩበት እያየ፤ ይህ ደግሞ ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መሆኑ እያወቀ፤ “እኔን የሚያገባኝ የሂሳብ ሚዛኑ ትክክለኝነት ነው” የሚል የባንክ ባለሙያ ከዘራፊዎች ጋር አልተባበረምን? ህሊናውንስ ሊቆጨው አይገባምን? በዚህ ተግባሩስ የሚወደውን የባንክ ሙያን አላረከሰምን?
- የገበየውን የኮምፕዩተርና፣ የኢሌክትሮኒክስም ሆነ የሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ እውቀት ለሬድዮ፣ ስልክና የኤሌክትሮኒክስ መልዕክቶች ጠለፋ የሚያውል ባለሙያ ሙያውን እያራከሰ አይደለምን? በተለይም ደግሞ በሙያው ለዘረኛ አምባገነን ደህንነት ሲባል የህዝብ መብት መጣሱ “ሙያተኝነቱ በቀረብኝ” አያስብልምን?
- የድሃ ገበሬዎችን ማሳ ነፃ በሚባል ዋጋ ተረክቦ ለባዕድ ባለሀብቶች አትርፎ በመሸጥ ላይ ላለው ካራቶሪ ተቀጥሮ የሚሠራ የግብርናም ይሁን የውሃ ልማት ባለሙያ ከእርሻው የተፈናቀለውን ድሃ ገበሬ እሮሮ እየሰማ “ይህ ከሙያዬ ውጭ ያለ ጉዳይ ነው፤ አያገባኝም” ቢል ሙያውን አላረከሰምን? እሱ ራሱ በግል ከዘመናዊ ጉልተኞች ጋር ተባብሯል ማለት አይቻልምን?
- ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች እንዲህ የአፈና ተቋማት ሲሆኑ፤ የትምህርት መርሃ ግብር ሲጣስ፤ ተማሪዋች በአካዳሚ እውቀት ፋንታ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሲሞሉ እያየ “ይኸ እኔን አያገባኝም” የሚል መምህር በትምህርት ሥርዓቱ መዋረድና መውደቅ ድርሻ የለውምን?
- ዘረኝነት፣ ወገንተኝነት፣ ሙሰኝነት ከተፃፉት ፓሊሲዎች በላይ ሥራ ላይ የዋሉ ፓሊሲዎች መሆናቸውን እያየና እያወቀ “እኔ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ፤ ገለልተኛ ነኝ” የሚል ባለሙያ ራሱን እያታለለ አይደለምን?
- እነዚህ ሁሉ በሙያ ሰበብ የሚታለፉ ከሆነ ማዕከላዊ እስር ቤት በዱላ የሰውን አካል እየቦጫጨቁ የሚጥሉት ገራፊዎች “መግረፍ ሙያችን ነው” ቢሉ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይደለምን?
ፓለቲካ ለመንግሥት ሥልጣን የሚደረግ ትግል እንደሆነ ብቻ አድርጎ መውሰድ ለብዙዎች ቅን አሳቢ ባለሙያዎች “እኔ የመንግሥትን ሥልጣን አልፈልግም፤ ፓለቲካን አልወድም፤ ሥራዬን ልሥራበት” እንዲሉ መንገድ ከፍቶላቸዋል።
ሃቁ ፓለቲካ ለመንግሥት ሥልጣን የሚደረግ ትግል ብቻ አለመሆኑ ነው። ፓለቲካ ለፍትህ፣ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ለእኩልነት፣ ለክብር የሚደረግ ትግልም ጭምር ነው። ለሙያ ነፃነትና ክብር የሚደረገውም ትግል ፓለቲካ ነው። በእኛ ሀገር እውነታ ደግሞ ፓለቲካ እንደ ሰው ለመታየትና እንደ ሰው ለመቆጠር የሚደረግ ትግል ነው። በባለሙያነት ወይም በገለልተኝነት ሰበብ ከፓለቲካ መራቅ ከኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ከገዛ ራስ ህሊና መራቅ ጭምር ነው። እራስን ማታለል ካልሆነ በስተቀር ዘረኝነትና አፈና ባለበት ሥርዓት ውስጥ አንገት ደፍቶም ቢሆን የሙያ ግዴታን መወጣት አይቻልም።
ስለሆነም የዛሬ ጥሪያችን አውቀውም ሆነ ሳያውቁ፤ ፈቅደውም ሆነ ተገደው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየረዱ ላሉ ባለሙያዎች ነው።
ባለሙያነታችሁን እናከብራለን። ሙያችሁ የመከራችን ማሳጠሪያ እንዲሆን እንፈልጋለን።
ይህን በማድረግ ፋንታ ግን ሙያችሁ የዘረኛ አምባገነን እድሜ እና የመከራችን ማርዘሚያ ሆኖ መገኘቱ በቸልታ የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። የቁርጥ ውሳኔ ቀን መጥቷል፤ ዛሬውኑ መስመራችሁን አስተካክሉ። ነገ ሊረፍድ ይችላል። በሀገራችሁ፤ በወንድሞቻችሁና በእህቶቻችሁ ላይ ብዙ ውድመት ከደረሰና ብዙ ጥፋት ከተሰራ በኋላ ባለሙያነታችሁ ከተጠያቂነት አያድናችሁም።
ከመለስ ዜናዊ አገዛዝ ራሳችሁን ለማግለል የወሰናችሁ ባለሙያዎች የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽዖ በማድረግ እስከዛሬ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የበደላችሁትን ህዝብ ካሱ። ባላችሁበት ቦታም ሆናችሁ ትግሉን የማገዝ እድል አላችሁ፤ ተጠቀሙበት።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!