አቡጉዳ – መድረኩ ወደ ግንባር ተሸጋገረ
የኢትዮጵያ አንድነት ፌደራላዊ መድረክ (መድረክ) አባሉ በሆኑት ድርጅቶቹ መካከል ያለዉ መቀራረብና መተሳሰር የበለጠ በመጠናከሩ፣ ከ«ጥምረት» ወደ «ግንባርነት» መዘዋወሩን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ያመለክታል።
በዚህም መድረኩ፣ የዉስጥ አሰራሩን የበለጠ ወደ አንድነት በማምጣት፣ አባል ድርጅቶቹም አንድ ጽ/ቤት መጠቀም የሚችሉበትም ሁኔታ የተፈጠረ ሲሆን፣ በአመራር አባላቱ መካከልም ያለዉን መቀራረብና መተሳሰር የበለጠ ያሳድገዋል ተብሎም ይጠበቃል።
መድረክ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ያልተሸራረፈ፣ የማያመነታ ጽኑ አቋም ያለዉ፣ በምንም አይነት መልክና ይዘት የኢትዮጵያ አንድነት ለድርድርና ለዉይይት መቅረብ እንደሌለበት ያረጋገጠ ፣ ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ሊኖራት እንደሚገባ፣ በተለይም አሰብ የኢትዮጵያ መሆን እንዳለባት በግልጽ ከማሳወቅ አልፎ ለዚያም እንደሚታገል ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አሁን ባለዉ ሕገ መንግስት የተቀመጠዉን ስታሊናዊና ዘረኛ የብሄር ብሄረሰቦች እስከመገንጠል መብትን ያሰፈረዉን አንቀጽ 39 የሚቃወም እንደሆነም በግልጽ አሳዉቋል።
መድረኩ በመሃል ከተሞች፣ በገጠር፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ሁሉ ያሉ ኢትዮጵያዉያንን ያቀፈና በኢትዮጵያዊነት ድንኳን ሥር ያሰባሰብ ሲሆን፣ በአገሪቷ በሙሉ ተቀባይነት ያለዉ እንደሆነም ይነገርለታል። በተለይም አሁን በስልጣን ላይ ያለዉ ገዢ ፓርቲ በኢትዮጵያዉያን መካከል ያስቀመጠዉን የዘር መከፋፈል ፈንጂ እያመከነ ያለ ድርጅት ሲሆን፣ እንደ አቶ አንዱዋለም አርጌ፣ አቶ በቀለ ገርባ ያሉ አንጋፋ የአመራር አባላቱ በአሁኑ ጊዜ በእሥር የሚገኙበት፣ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲና ለኢትዮጵያ አንድነት የሚደረገዉን ትግል እየመራ ያለ ድርጅት እንደሆነ በግልጽ እየታየ ነዉ።