‹‹ዋናው ጉዳይ ግንባርን በግንባር መግጠም ነው ›› ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የመድረክ አመራር አባል ከሪፖርተር የተወሰደ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ከስብስብነት ወደ ግንባር ለመሸጋገር መወሰኑን የድርጅቱ አመራር አባላት ባለፈው ሐሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በዕለቱ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የመድረክ አመራር አባልና የኦሮሞ ሕዝብ ኮንግረስ (ኦሕኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ወደ ግንባር በተደረገው ሽግግርና በሌሎች የአገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ጥያቄ፡- የመድረክ አንዱ ጥያቄ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ነው፡፡ ኢሕአዴግን ጨምሮ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት አንድ አጠቃላይ አገር አቀፍ የፖለቲካ ስብሰባ እንዲካሄድ የማድረግና ያሉትን ችግሮች የመፍታት ዓላማ እንዳላችሁ ነው የምትናገሩት፡፡ ኢሕአዴግ ግን የብሔራዊ መግባባት ጥያቄ ሲነሳ በአቋራጭ የሚመጣ የሥልጣን ጥያቄ ነው ሲል ይቃወመዋል፡፡ ይህንን የሐሳብ ልዩነት እንዴት ታዩታላችሁ?
ዶ/ር መረራ፡- ኢሕአዴግ ብሔራዊ መግባባትን ለምን እንደሚቃወም ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ በብዙ የአገራችን ማኅበረሰቦች የሚባል ነገር አለ፡፡ ‹‹ጅብ ማታ ማታ የሚሠራውን ስለሚያውቅ ቀን ቀን ሰው ይሸሻል›› ይባላል፡፡ ኢሕአዴግ በአጠቃላይ ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሠራቸውን ሥራዎች ያውቃል፡፡ በአብዛኛው ከአገሪቱ የፖለቲካና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ከመተባበር፣ ከመነጋገርና ከመደራደር ይልቅ በብቸኝነት የአንድ ፓርቲ አገዛዝን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ በጉልበት ለመጫን እየሞከረ ነበር፡፡ አሁንም ያንን ለመቀጠል ፍላጐት ስላለው ነው ብሔራዊ መግባባትን የሚቃወመው፡፡ መሰባሰብ፣ መነጋገር፣ መደራደርና ልዩነት ካላቸው ኃይሎች ጋር ተደራድሮ አንድ ነገር ላይ መድረስ ዓለም እስካሁን ድረስ የሚከተለው አሠራር ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት የተሻለ ውጤትና መረጋጋት መፍጠር ያስችላል፡፡ በርካታ አገሮች ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር የተሻለ ልማትና ብልፅግና ማምጣት እንደቻሉ ኢሕአዴግም ያውቃል፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ ብዙውን ጊዜ ሥልጣን ወይም ሞት ስለሚል ተቃዋሚ ኃይሎች ሥልጣኔን ይሸረሽሩብኛል በሚል ፍራቻ ብሔራዊ መግባባትን የሚቃወም ይመስለኛል፡፡
የእኛ አማራጭ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተሰልፈን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንቀሳቅሰን፣ አደራጅተን፣ ሕዝቡን ለመብቱ፣ ለክብሩ፣ ለነፃነቱ እንዲሰለፍ በማድረግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ምድር እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚፈልጓቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች በድምፃቸው ሥልጣን ላይ እንዲያወጡ፣ የማይፈልጓቸውን ደግሞ በድምፃቸው ከሥልጣን እንዲያወርዱ የሚያስችል የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ የእኛ እንቅስቃሴ ሁላችንንም እኩል የምታስተናግድ ኢትዮጵያ ለመፍጠር ነው፡፡
ጥያቄ፡- መድረክን የመሠረቱት ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የርዕዮተ ዓለም ልዩነታችሁን በምን መንገድ ነው ያቻቻላችሁት?
ዶ/ር መረራ፡- ብዙውን ጊዜ የኢሕአዴግ የፕሮፖጋንዳ አቅጣጫ ርዕዮተ ዓለማቸው አንድ ካልሆነ፣ ፕሮግራማቸው አንድ ካልሆነ አብረው አይቆሙም የሚል ነው፡፡ እንዲያውም ኢሕአዴግ ሲፀልይ የነበረው ይፋረሳሉ ብሎ ነው፡፡ አንፋረስም፡፡ ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ መድረክ የሚፈልገው ምንድነው? የሚል ነው፡፡ ተሰባስቦ አገሪቷን የመታደግ ሁኔታ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት የማውጣት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተባብረው የተሻለ ሰፊ የፖለቲካ መድረክ የመፍጠር፣ አንዱ ሌላውን የሚያሳድድበት የፖለቲካ ሥርዓት ሳይሆን አገሬ ነው የሚል ኢትዮጵያዊ በሙሉ ሊሳተፍበት የሚችል የፖለቲካ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ እኛ ልዩነት ላይ ሳይሆን አንድነት ላይ ነው የምናተኩረው፡፡
በነገራችን ላይ ለምን ኢሕአዴጐች በተደጋጋሚ እንደሚጠይቁን አላውቅም እንጂ በዓለም ደረጃ የሚሠራበት ነው፡፡ ለምሳሌ የብዙ ዓመታት የዴሞክራሲ ልምድ ባላት ጀርመን ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያየ ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ፓርቲዎች ጥምረት በመፍጠር ሥልጣን የሚይዙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ባለፈው ጊዜ ሥልጣን ላይ የነበሩ ፓርቲዎች ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ ናቸው፡፡ ተባብረው ጀርመንን ለአራትና ለአምስት ዓመታት ሲገዙ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በአሁኑ ምርጫ ያሸነፈው ኮንሰርቫቲቭ [ወግ አጥባቂ] ፓርቲ ሌበር ዴሞክራቲክ የሚባለውን ፓርቲ ሲያገኝ ያኛውን ትቶ ይኼኛውን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዳብሮባቸዋል በሚባሉ የሠለጠኑ አገሮች ርዕዮተ ዓለም ብቻውን ወሳኝ ጉዳይ አይደለም፡፡ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች አብላጫ ድምፅ ሲያጡና አገራዊ መደጋገፍን ሲፈልጉ በአንድነት ይሠራሉ፡፡
ለምሳሌ እስራኤል ውስጥ ብዙውን ጊዜ ቀኝም፣ ግራም፣ መሀል መንገድም የሚጓዙ ፓርቲዎች ተሰባስበው መንግሥት ይፈጥራሉ፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ አይደረግም ብሎ ኢሕአዴግ ለምን እንደሚከራከር አላውቅም፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ብቻ ነው ኢትዮጵያን ነፃ የሚያወጣውና ወደ ብልፅግናና ልማት የማያመጣው ብሎ ስለሚሰብክ ካልሆነ በስተቀር በዓለም ላይ በብዙ አገሮች የተለመደ አሠራር ነው፡፡ በግንባር ደረጃ የምንቆይበት ምክንያትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ልዩነታችንን መቶ በመቶ ብናስወግድ ኖሮ አንድ ፓርቲ እንሆን ነበር፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴጐች ይኼንን ጥያቄ ደጋግመው ባይጠይቁ ወይም ባያስጠይቁ ይሻላል፡፡
ጥያቄ፡- መድረክ ወደ ግንባር ሲለወጥ እያንዳንዱ አባል ድርጅት ያለውን ህልውና እንደያዘ ወይም ራሱን እንደቻለ ነው ወደ ግንባሩ የሚመጣው? ወይስ ድርጅቶቹ ራሳቸውን በማፍረስ ነው የግንባሩ አካል የሚሆኑት?
ዶ/ር መረራ፡- ድርጅቶች ሕጋዊ ህልውናቸው እንዳለ ነው የሚተባበሩት፡፡ ዋናው ጉዳይ ፓርቲዎች ልዩነት ላይና የራሳቸው የውስጥ ጉዳይ ላይ የማተኮር ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ተሰባስበንና ተጠናክረን በጋራ ቢሮዎችን የመፍጠርና ድጋፍን በጋራ የማሰባሰብ ሁኔታ እየጐላ እንዲሄድ ማድረግ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ሕገ መንግሥቱን በማይቃረን መንገድ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት እናቋቁማለን ተብሏል፡፡ ነገር ግን ፓርቲዎች ተስማምተው ሥልጣን የሚይዙበት አካሄድ በሕገ መንግሥቱ አልተቀመጠም፡፡ አንድ ፓርቲ መንግሥት መመሥረት የሚችለው በምርጫ ተወዳድሮ ሲያሸንፍ ብቻ ነው፡፡ ይኼ ከእናንተ ዓላማ ጋር አይቃረንም?
ዶ/ር መረራ፡- ሕገ መንግሥቱ ይህንን የሚከለክልበትን አንቀጽ እኔ አላውቅም፡፡ ያሸነፈ ወይም ያሸነፉ ፓርቲዎች መንግሥት ያቋቁማሉ ነው የሚለው፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ስግብግብ በመሆን ሥልጣን ላለማጋራት፣ ሁሉንም ነገር ጨምድደው ከሌሎች ጋር ላለመሥራት ውሳኔ ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ፓርቲዎች ደግሞ በምርጫ ሲያሸንፉ ብሔራዊ መግባባትን ሊፈጥር የሚችልና ሰፊ መሠረት ያለው ሁሉንም ሊያሳትፍ የሚችል መድረክ አመቻችተው ሊጋብዙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ዋናው ጉዳይ የፍላጐት ጥያቄ ነው እንጂ መድረክ ሲያሸንፍ ሌሎችን ጋብዞ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የሚያቅፍ መንግሥት እንዳያቋቁም የሚከለክል ነገር የለም፡፡ እኛ ይህንን የምናደርገው ስናሸንፍ ነው፡፡ አሸንፈን መንግሥት ስንመሠርት ሁሉንም አግልለን እንደ ኢሕአዴግ ሥልጣንን ለብቻችን ጨምድደን የምንሄድበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ መድረክ የተከለከሉ በሙሉ፣ በር የተዘጋባቸው ኃይሎች ጭምር በሚፈጠረው መንግሥት ውስጥ በተለያዩ መንገዶች የሚሳተፉበት ሁኔታ ይፈጥራል ነው የምንለው፡፡
ፓርላማ የሚገባው ፓርቲ ሕዝብ የመረጠው ነው፡፡ ይኼ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ከፓርላማ ውጪ ግን አንድ ሺሕ አንድ በጣም ብዙ ሕዝብን ሊያሳትፉ የሚችሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ያላቸውን እውቀት ወደ ሰፊ መድረክ እንዲያመጡ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አሉና እንደዚያ ዓይነት አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት ነው የምንሠራው፡፡ እደግማለሁ በተለይ በሽግግር ላይ የነበሩ አገሮች ያለፉበት አሠራር ነው፡፡ ሌሎችን በማግለል ሳይሆን በማስተባበር ሰፊ የፖለቲካ ሥራ በመሥራትና የመቻቻል ፖለቲካን በመፍጠር ነው እዚህ የደረሱት፡፡
ጥያቄ፡- መድረክ ከስብስብ ወደ ግንባር ሲሸጋገር ከስም ለውጥ ባሻገር በፖለቲካው እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ምንድነው?
ዶ/ር መረራ፡- በጥምረት ስንሠራ በአሠራርና በአመራር ላይ፣ ቢሮዎችን በመክፈት፣ መድረክ ሊኖረው የሚችለውን ሀብት በመሰብሰብና በጋራ በመጠቀም ረገድ የተወሰኑ ችግሮች ነበሩ፡፡ ወደ ግንባር ስንሸጋገር የተሻለ የመቀራረብና አንድ ሆኖ አመራር የመስጠቱ ሁኔታ ይሻሻላል፡፡ በአሠራር ላይ ቀላል የማይባሉ ውጤቶችን ለማምጣት ያስችላሉ፡፡ በተለይ ቢሮዎችን በየቦታው አብሮ የመክፈት፣ ስብሰባዎችን በየቦታው አብሮ የማካሄድ፣ ደጋፊዎቻችንም ወደመቀናቀን ሳይሆን ተባብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ይረዳል፡፡
ወደ አራት የሚደርሱ የተግባር ኮሚቴዎች አሉን፡፡ እነዚህ ኮሚቴዎች አንድ ላይ ሆነው ሲሠሩ፣ ዲፕሎማቲክ ግንኙነቶች ስናደርግና ከራሳችን ውጪም ከሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ስንደራደር የተሻለ ቅርፅና የመሰባሰብ ስሜት እንዲፈጥር ያደርጋል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግንባርን በግንባር መግጠም ነው፡፡ እየገዛን ያለው ግንባር ኢትዮጵያን ለሃያ ዓመታት ምን እንዳደረጋት እናውቃለን፡፡ እኛ ግን በአሠራራችን ውስጥ የተሻለ ዴሞክራሲ በማስፈን ለኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ አማራጭ ያለው ግንባር መፍጠር ነው የምንፈልገው፡፡ የመድረክ ሽግግር ግንባር ላይ ያበቃል? ለሚለው የወደፊቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚወስነው ነው፡፡
እኛ ግን ዓላማችን እስከ መጨረሻው [ውህደት] ለመሄድ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ አሁን ያለውን የፖለቲካ መድረክ መለወጥ ነው፡፡ ግንባር መመሥረቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ለምሳሌ ቢሮዎችን በቀላሉ ለመክፈት ይረዳል፡፡ ለምሳሌ ወደ ሰሜን (ትግራይ) ስንሄድ አማራና ኦሮሞ መጣባችሁ ብሎ ነው ኢሕአዴግ የሚቀሰቅሰው፡፡ እኛ ከሌለን ቀይ ባህር ሊጨምሯችሁ ይችላሉ ነው የሚለው፡፡ ወደ አማራ ክልል ስንሄድ ኦሮሞ ኢትዮጵያን ይዞባችሁ ሊሄድ ነው ይላል፡፡ ወደ ኦሮሞ አካባቢ ስንሄድ ደግሞ እነ መረራ ነፍጠኞችን ተሸክመው መጡባችሁ ነው የሚለው፡፡ ይህንን የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ስንሰብር የኢትዮጵያን ሕዝብ በጋራ ዓላማና በጋራ አገራዊ አጀንዳዎች ተቀራርቦና ተቻችሎ ለማንቀሳቀስ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብም የተሻለ ድጋፍ ለመስጠት ያስችላል፡፡ ብዙዎች የሚጠይቁን ‹‹ማንን እንደግፍ? ኪሳችን አንድ ነው፣ እናንተ ግን ብዙ ናችሁ፤›› በማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ጠቅላላ ጉባዔ ሳይወስን እንዴት ነው አሁን ወደ ግንባር ለመሸጋገር ወስነናል ልትሉ የቻላችሁት?
ዶ/ር መረራ፡- ከማንም በላይ ጠቅላላ ጉባዔው ነው ወደ ግንባር ተሸጋገሩ ብሎ ሲገፋን የነበረው፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም ከዚያም በላይ የምንደራደርባቸውን ነገሮች ወደ ድርጅቶቻችን ሥራ አስፈጻሚዎች እየወሰድንና ጉዳዩን መልሰን እያመጣን ስንደራደር ነበር፡፡ በመተዳደሪያ ደንባችን ላይ የተሰጠንን የቤት ሥራ መፈጸማችንን የቤት ሥራውን ለሰጠን አካል ወስደን የመድረክ ሥራ አስፈጻሚ የደረሰበትን ውሳኔ እናሳውቃለን፡፡ ድሮውንም ይኼ አካል ውሳኔያችሁን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ አምጡ ብሎ ሲጠይቀን ነበር፡፡ ይኼው አመጣን ብለን ስምምነት ላይ የደረስንበትን ውሳኔ እናቀርብለታለን፡፡ ይህ ውሳኔ ከስድስቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ ሥራ አስፈጻሚዎች የተስማሙበት ነው፡፡ በቀጣይ የምርጫ ቦርድ ሕግ በሚጠይቀው መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው እንዲያፀድቀው እናደርጋለን፡፡
ጥያቄ፡- መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት መድረክ በውስጡ የተሰገሰጉ አሸባሪዎችን እንዲያጠራ ጥሪ አድርጓል፡፡ ይህንን የመንግሥት ጥሪ እንዴት ታዩታላችሁ?
ዶ/ር መረራ፡- የኢትዮጵያ መንግሥትን አባሎቻችን አሸባሪዎች ናቸው የምትለው ምን ማስረጃ ይዘህ ነው ብለን ጠይቀን ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ አባሎቻችን ተይዘው ተደብድበዋል፡፡ አሸባሪዎች ናቸው ብለው እንዲመሰክሩ የሚደረጉት ደግሞ እኛን ከድተው ከመንግሥት ጋር የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱን አምጥቶ በእኛ ላይ እንዲመሰክሩ የሚደረገው ለምንድነው? ለምሳሌ ‹ኦነግ ነበርን እንዲህ እናደርግ ነበር› የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ይህንን ስታይ መንግሥት የሚለውን ትጠራጠራለህ፡፡
ለምሳሌ በሽብርተኝነት ተጠርጥሮ የታሰረው አቶ ኦልባና በጣም ጠንቃቃና በኦሮሚያ ምክር ቤት የእኛ ተወካይ ሆኖ የቆየ ሰው ነው፡፡ ይህንን ሰላማዊ ሰው ሽብርተኛ ነው ብሎ ማሰር ሊታመን የማይችል ነው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ሰውዬው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሰዎች ሲመጡ አነጋግሯል፡፡ የታሰረውም በዚያ ንዴት ይመስለኛል፡፡ በቅርበት የምታውቃቸው ሰላማዊ ሰዎች ሲታሰሩ ስታይ መረጃዎቹን ትጠራጠራለህ፡፡
አንዱን ሌላ ላይ መስክረህ ከእስር ቤት ውጣ የሚባል ነገርም አለ፡፡ በሌሎች ላይ አልመሰክርም ያለ አንድ ሰው ሁለት ዓመት እስር እንደተፈረደበት መረጃ አለን፡፡
ጥያቄ፡- እናንተ ንፁህ ከሆናችሁ ታዲያ ኢሕአዴግ ራሳችሁን አጥሩ የሚለው ለምን ይመስልዎታል?
ዶ/ር መረራ፡- እኔ እኮ ፓርላማም በነበርኩበት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሦስት አራት ጊዜ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ በሌላ ድርድርም ላይ ጠይቄያለሁ፡፡ በውስጣችሁ የተሰገሰጉ ሽብርተኞች አሉ የምትሉ ከሆነ እኛም መከታተል እንድንችል የነዚህን ሰዎች ስም ስጡኝ ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሦስት ጊዜ እሺ ብለው ቃል ከገቡ በኋላ የደኅንነት ጉዳይ ስለሆነ አልሰጥህም አሉኝ፡፡ አቶ በረከትም ቃል ከገቡ በኋላ መልሰው አይሆንም አሉኝ፡፡ ዋናው ጉዳይ የሚመስለው በሽብርተኛ ስም አጠቃላይ ተቃዋሚን ማዳከም ነው፡፡ የመንግሥት ስትራቴጂ ማስፈራራትና ማደናገጥ ይመስላል፡፡ በተለይ ብዙ ጊዜ የሚያመኝ ‹‹ኦነግ ነበርን ይኼንን ሥንሠራ ይኼን ስናደርግ ነበር›› ሲሉ የነበሩ ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ መጥተው ሲንሸራሸሩ መመልከቴ ነው፡፡ ራሱ ሲሠራው የነበረውን ወንጀል በሌላው ላይ ደፍድፎ በነፃነት ሲንቀሳቀስ ማየት ሌላ ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡
ጥያቄ፡- መንግሥት እየወሰደው ያለው ዕርምጃ በሰላማዊ ትግል ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለ?
ዶ/ር መረራ፡- በግሌ ዕርምጃው በሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን አካላት ከማጠናከር ይልቅ ለማዳከም መሞከሩ መንግሥት በአሸባሪነት የሚከሳቸውን ወገኖች ነው የሚያጠናክረው፡፡ ከዚህ ተስፋ ያጣ ወጣት ነገ ከነገ ወዲያ ይሄዳል፡፡ ሄዶ የሚያጠናክረው በሽብርተኝነት የተፈረጁትን ነው፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እኮ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ እነ ዶክተር ብርሃኑ እኮ ከእኛ በበለጠ ከኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ጋር ይቀራረቡ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከእኛም አልፈው የሄዱት እነሱ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ መጫወቻውን ሜዳ ስታጠበው ውሎ አድሮ ሁላችንንም ነው የሚጐዳው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ገዥው ፓርቲም አይጠቀምበትም፡፡ ከዚህ ተስፋ የሚያጣው ወዴት ይሄዳል? ነው ጥያቄው፡፡ መደብደቤ ላይቀር፣ መታሰሬ ላይቀር፣ ሥራ ማጣቴ ላይቀር ብሎ ወደ ሌሎች የመገፋት ሁኔታዎች እንደሚኖሩ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡
እነዶክተር ብርሃኑ ነጋ ለምን ርቀው ሄዱ የሚለውን ማየት ይቻላል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የምታገኝ አይመስለኝም፡፡ ችግሮቹ ካልተፈቱ በስተቀር ግራውንም ቀኙንም ሁሉንም ፀረ ሰላም ነው እያሉ ማሰሩ ምንም ለውጥ አያመጣም፡፡ ሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብ እኮ አታስርም፡፡ የምታስረው የተወሰነውን ነው፡፡ አንድ ሰው ስታስር ደግሞ ሃያና ሰላሳ ሰው ነው የምታስቀይመው፡፡ ቤተሰብ፣ ጓደኛ፣ ዘመድ አዝማድ እንኳን ታሰረልኝ አይልም፡፡ ስለዚህ ዕርምጃው የአገሪቱን ፖለቲካ የበለጠ የሚያወሳስብ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከዚህ በፊት ተመሥርተው የነበሩ ጥምረቶች ለአጭር ጊዜ አብረው ከተጓዙ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ፈርሰዋል፡፡ መድረክ ይኼ ዓይነቱ ዕጣ ፈንታ እንደማይገጥመው እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
ዶ/ር መረራ፡- ዋናው ዋስትናው የሕዝብ ትግል ነው፡፡ ሕዝቡ ለመብቱና ለነፃነቱ የሚታገል ከሆነ ይኼ ኅብረት ቢፈርስ ሌላ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ የተሻለ ውጤት የሚመጣው የተሻለ ሥራ የሚሠራው ተባብረህና ተረዳድተህ ለሕዝቡ የተሻለ አማራጭ ስታቀርብ ነው፡፡ መድረክ ውስጥ የሚገኙት አመራሮች ቅንጅትንና ኅብረትን ጨምሮ የተለያዩ ጥምረቶች በተመሠረቱበት ወቅት የነበሩና ካለፈው ስህተት ብዙ ልምድ የወሰዱ ናቸው፡፡ ከኢሕአዴግም ቢሆን የተወሰነ ልምደ ወስደናል፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር አብረው የታገሉ ሰዎችም ከእኛ ጋር አሉ፡፡ በኢሕአዴግ በኩልም ሆነ በተቃዋሚዎች የተገፋው መንገድ ምን እንደነበርና ምን ሠርተን ምን እንዳገኘን የምንረዳበት ሰፊ ልምድ አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጥምረቶች በተሻለ ሁኔታ ተባብረን እንሠራለን የሚል ተስፋ አለኝ፡፡