በአነስተኛ ጥቅማጥቅም በመደለል የወያኔ አገዛዝ ካድሬ ለመሆን የተዳረጉ ወጣቶች የወያኔውን ኢሃዴግ ፍጹም ህሊና ቢስነት በመገንዘብ ላይ ነን አሉ
በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጁ የአነስተኛ እና ጥቃቅን ዘርፍ ታዳሚ የሆኑ አያሌ ወጣቶች “የፖለቲካው መሣሪያ ሊያደርገን ያሰባሰበን ኢሕአዴግ ፍጹም ህሊና-ቢስ እና ከማህበረሱቡ ጋር ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት የሌለን ፍጡራን አድርጎ በመቁጠር እራሱ የፈጠረውን ችግር ህብረተሰቡን እያወናበድን እንድንቀርፍለት ጫና እየፈጠረብን ይገኛል” ማለታቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘገበ።
ኢሳት በሪፖርቱ እንደገለጸው መስከረም 30 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ለዘጋቢያችን አስተያየታቸውን የሰጡትና ምሬታቸውን የገለጹት በአነስተኛ እና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ የተደራጁ ወጣቶች “ሸረሪት አንድ ግዜ ነው የምታደራው ፤ድሯም የሚያገለግለው ለአንድ ግዜ ነው፤ እኛ ግን ሰዎች በመሆናችን እንደሸረሪት ልንሆን አንችልም፡፡ከዚህ በፊት አማራጭ አጥተንም ሆነ ተወናብደን አንድ ግዜ የኢሕአዴግን የፖለቲካ ድር በሕዝብ ላይ ለማድራት ሞክረናል፡፡ ዳግመኛ ግን አይቻለንም፡፡ የህብረተሰቡ ልጆች በመሆናችን ቤተሰቦቻችን የሚገጥማቸውን ዘርፈ-ብዙ ችግር የምናውቅና የምንጋራም ነን” ካሉ በሁዋላ “የወያኔው ኢሕአዴግ ቅጥፍት ላይታረም ከራሳችን ህሊና እና ሁሉን እያወቀ የኢሕአዴግን ውሸት ስንግተው ከሚታዘበን ህብረተሰብ ጋር የምንጋጨው ለምንድን ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ ብሉአል።
ወጣቶቹ አክለውም “የሰሞኑ ስብሰባ እና ጉዳያችንን ተወጡልን የሚለው ኢሕአዴጋዊ ውትወታ ሰልችቶናል፡፡ ሌላው ቀርቶ እኛ ከዚህ ቀደም ለተደራጀንበት የሥራ ዘርፍ ችግር ማስወገጃ አቅርበንለት ለነበረው አንድ ሺ አንድ ጥያቄዎች ለአንዱም እንኳን መልስ መስጠት ያልሆነለት ሥርዓቱ ከእንግዲህ ከኛ ጋር ተፋቷል፣ ከሕዝቡ ጋር እንደተፋታ ሁሉ…” ማለታቸውን ኢሳት ገልጹአል፡፡
የወያኔው ኢህአዴግ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአባላቱ ከፍተኛ ጥያቄ እየተነሳበት በመምጣቱ ግምሽ የሚሆኑት አባላቱን ለማባረር መወሰኑን በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲሆን በሰሜን ሸዋ የሚገኙ የኢህአዴግ መምህራን አባላት ራሳቸውን ከአባልነት ማግለላቸውንና ስብሰባዎችንም አንካፈልም ማለታቸውን ቀደም ብለን መዘገባችን ይታወሳል።
የግንቦት7 ንቅናቄ በያዝነው ሳምንት ለንባብ ባበቃው ርእሰ አንቀጹ የወያኔው ኢህአዴግ አባላት ጊዜው ሳይረፍድ መስመራቸውን እንዲያስተካክሉ ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል።