አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የአለም ባንክ የኢትዮጵያን የአምስት አመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አጣጣሉት

የገንዘብና የልማት ተቋማቱ በያዝነው ወር ባወጡት ሪፖርት የኢትዮጵያ የአምስት አመት እቅድ የተጋነነና ውጤታማ ለመሆኑም የሚያጠራጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቶቹ በመነሻቸው የወያኔ አገዛዝ ባለፉት አመታት አገኘሁ የሚለውን 11 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አጣጥለው አገሪቱ ከ 7 እስከ 8 በመቶ የሚሆን እድገት ማስመዝገቡዋንና በአምስት አመት እቅዱም አገሪቱ ከስድስት እስከ ሰባት በመቶ እድገት ልታስመዘገብ እንደምትችል ጠቁሟል። ይህ የእድገት አሀዝ አገዛዙ አገኘዋለሁ ከሚለው ከ11 እስከ 15 በመቶ ጋር ሲነጻጻር በእጅጉ የወረደ ነው።

የአምስት አመቱ የልማት ግቦች የተጋነኑና ሊሳኩ አይችሉም የሚሉባቸውን ነጥቦች የገንዘብ ተቋማቱ ዘርዝረው አቅርበዋል። የዘረኛው መለስ አገዛዝ እየተከተለ ያለው ገንዘብን የመርጨት ፖሊሲ የገንዘብ ግሽበት በማስከተሉ፣ አደጋው በመጪዎቹ አምስት አመታት በተመሳሳይ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል። ወያኔ በአምስት አመታት ውስጥ እገነባቸዋለሁ በማለት የጀመራቸው ፐሮጀክቶች ሊሳኩ የማይችሉት የታቀዱትን ፕሮጀክቶች ወጪ ለመሸፈን አስተማማኝ የሆነ የገቢ ምንጭ ባለማዘጋጀቱ ነው ተብሎአል።

በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዙሪያ ያሉ በርካታ ማነቆዎችን የዘረዘሩት አይኤም ኤፍና የወርልድ ባንክ አጥኝዎች የወያኔ አገዛዝ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ጣልቃ ገብነት ቀንሶ የንግዱ ማህበረሰብ በስፋት እንዲሳተፉበት እንዲያደርግ መክሯል። ከዚህ በተጨማሪ ሙስና ሌላው ችግር መሆኑን የጠቀሱት ተቋማቱ ወያኔ ሙስናን ለመከላከል አቅጃለሁ ቢልም የመተግበሪያ መንገዱን ግን አላስቀመጠም ብሎአል።

የገንዘብ ተቋማቱ በማጠቃላያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የገንዘብ ግሽበትና የዋጋ ንረት ልጓም ካልተበጀለት በውጭ እርዳታ የተገኙት አንዳንድ ለውጦች  ይቀለበሳሉ።

የመለስ ዘናዊ አገዛዝ አገኘሁት ለሚለው የኢኮኖሚ እድገት ሁሌም የአለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችን በዋቢነት እንደሚጠቅስ ይታወቃል። ይሁን እንጅ የገንዝብና የልማት ተቋማቱ ያወጡት አስደንጋጭ ሪፖርት በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከፍተኛ ገንዘብ ከውጭ በመበደር የልማት ተቋማቱን የመገንባት እቅድ ላለው ለመለስ አገዛዝ ብድር በማግኘት በኩል እንቅፋት ሊፈጥርበት እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአምስት አመቱ የልማት እቅድ ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ይገኛል ተብሎ የታሰበው ከምእራባዊያን ሳይሆን ከህንድና ቻይና ነው እንደሆነ ይታወቃል።