መድረክ ከቅንጅት ወደ ግንባር መሸጋገሩ ተገለጸ

አዲሱ ግንባር ከጥቅምት 2 ቀን 2004 ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው መለስተኛ የፖለቲካ ፕሮግራሙ የግንባሩ ፕሮግራም ሆኖ እንዲያገለግል በመስማማት መድረክን እስካሁን ከነበረበት የቅንጅት አደረጃጃት ከፍ ወዳለ የግንባር አደረጃጀት ለማሸጋጋር የመድረኩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወስኗል።

መድረክ በግንባሩ ዙሪያ የተሰባሰቡት የአረና ትግራይ ለፍትህና ለዲሞከርአሲ፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞከርአሲያዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ፣ የኢትዮፕያ ሶሻል ዲሞከርአሲያዊ ህብረት እንዲሁም አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በጋራ ለመታገል የተስማማሙባቸው የመለስተኛ ፕሮግራም መሰረታዊ መርሆዎች ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ እንዲሁም ኢፍተሀዊና አድሎአዊ አሰራሮች የተወገዱበት፣ በመከባበር ላይ የተመሰረተአንድነት እንዲጠናከር መቆም፤ መገንጠልን ያለመደገፍ፣ የግለሰብ፣ የብሄረሰቦች፣ ህዝቦችና የቡድን መብቶች እኩል እንዲከበሩ፣ ሰብአዊና ዲሞከርአሲያዊ መብቶች የሚከበሩባትና ማህበረ- ኢኮኖሚ ፍትህ የሰፈነባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጠንክሮ ለመንቀሳቀስ የሚሉት ይገኙበታል።

መድረክ በነጻ የመደራጀትና የመንቀሳቀስ ያልተገደበ መብት ማረጋገጥ፣ የመናገር፣ የመጻፍና ሀሳብን የመግለጽ መብቶች እንዲከበሩ፣ ነጻ ፍትሀዊ ምርጫን በገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚ ለማከናወንና የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታን እውን የሚሆንበት ስርአት ለመገንባት እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል።

መድረክ አያይዞም “በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር የብሄራዊ መግባባት ውይይት እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት፣ በዚህም የብሄራዊ ማግባባት ውይይት ላይ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ ጨምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን እና በትጥቅ ትግል አለማቸውን የሚአራምዱትን የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ ሰላማዊ ትግሉ ጎራ ተቀላቅለው በብሄራዊ መግባባት ውይይት ላይ እንዲሳተፉ ለማግባባት ጥረት ለማድረግና ለስልጣን ከበቃ ደግሞ ሁሉን የፖለቲካ ሀይሎች የሚያሳትፍ ብሄራዊ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መንግስት እንደሚያቋቁም ጠቅሷል።

የአገራችን ፖለቲካ ከቂም በቀልና ከጥላቻ ስሜት እንዲሁም ከተለያዩ ቁርሾዎች የሚላቀቅበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለመታገል፣ ህገ መንግስቱ ሁሉን የፖለቲካ ድርጅቶችና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ ውይይት ተደርጎበት በህዝበ ውሳኔ ጭምር የሚሻሻልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ተግቶ እንደሚሰራ መድረግ አስታውቋል።

መድረክ “የህንን በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች የህብረት ጥያቄ ላይ ወሳኝ የሆነውን እርምጃ ፣ ጉዳዩን በጉጉት ሲጠብቀው ለነበረው መላው ሀገር ወዳድ ህዝባችንና ለአለማቀፉ የኢትዮጵያ ወዳጅ ወገኖች ሁሉ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው” ብሎአል።