“ኢትዮጵያ ባለፉት 20 የወያኔ አገዛዝ አመታት ከ አሥራ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ተዘርፋለች” ሲሉ በአለም ባንክ ለረጅም አመታት የሰሩ እንድ ታዋቂ የምጣኔ ሃብት ምሁር ገለጹ

ወያኔ ስልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስም በልማት እርዳታና በብድር ከአለም አቀፍ ህበረተሰብ ካገኘው መጠነ ሰፊ ገንዘብ ውስጥ ከአስራ አንድ ቢሊዮን በላይይ የሆነ ገንዘብ በባለስልጣናቱ መዘረፉን በአለም ባንክ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱት ታዋቂው ኢኮኖሚስት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ገለጹ።

ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ይህን የገለጹት ባለፈው እሁድ መስከረም 28 ቀን አዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ  የአንድነት ደጋፊዎች ጋር በስካይፒ ባካሄዱት ውይይት መሆኑን የኢትዮጵያ ሳታላይት ድርጅት ኢሳት ገለጸ።

እንደ ኢሳት ዘገባ ዶ/ር አክሎግ በኢኮኖሚው ዙሪያ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ችግር ነው ያሏቸው፤ የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ የሀገሪቱ ሀብት በጥቂቶች መያዝና ሥር የሰደደ ሙስና ናቸው ፡፡

በዚህም ምክንያት የዓለም ባንክና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በጥናት ላይ የተመረኮዘ ማስረጃ በመስጠት መንግስት ፖሊሲዎቹንና አካሄዱን እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ቢመከሩም፤ ሰሚ ባለመኖሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮቹ እየሰፉ መሄዳቸውን አመልክተዋል ተብሎአል።

ዶ/ር አክሎግ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደገለፁት ”በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ 90 ሚሊዮን  ይደርሳል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤ ከነኚህ መሃል 7 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት፤ ወላጅ አልባ ናቸው፡፡ 46 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ፤ በአሁኑ ሰዓት አገሩን ጥሎ ለመሰደድ እንደሚፈልግ ጥናቶች ያረጋግጣሉ” ብለዋል ዶ/ር አክሎግ።

ባለፉት 20 የወያኔ አገዛዝ አመታት ለአገሪቷ ከለጋሾች በብድርና በእርዳታ ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ በባለሥልጣኖች እንደተወሰደ መረጃዎችን ተንተርሰው አመላክተዋል። ዶ/ር አክሎግ እንዳሉት፤ በደርግ መንግስት ዘመን ኢትዮጵያ በ17 ዓመታት ውስጥ ያገኘችው ጠቅላላ ብድርና እርዳታ 4 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሲሆን፤ በወያኔ አገዛዝ ዘመን ግን እስከ 40 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ብለዋል።

ከዚህም ገንዘብ ውስጥ ያለፉትን ሶስት ዓመታት ሳይጨምር 8.4 ቢሊዮን ዶላር በህገወጥ መንገድ በኢትዮጵያ በባለሥልጣኖች አማካኝነት ወደውጭ መወሰዱን የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራምን ጥናት ዋቢ በማድረግ አውስተዋል።

አጠቃላይ  በ20ው ዓመታት  በህገ-ወጥ መንገድ በባለስልጣናት ተወስዶ በውጪ ባንኮች ተቀምጦ የሚገኘው  የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ  ግን፤ ከ 11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ነው የገለፁት። ይህም የሚያሳየው፤ በአገሪቱ ሙስና እጅግ መንሰራፋቱን ነው ብለዋል የኢኮኖሚ ባለሙያው።

ዶ/ር አክሎግ አክለውም ”ህዝቡ የተዘረፈውን ከ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ ለማስመለስ አሁን መጨነቅ የለበትም። መቅደም ያለበት ነገር፤ ገዥውን ፓርቲ ከሥልጣን ማውረድ ነው። ከዚያም ልክ እንደ ቱኒዚያ፣ ግብጽና ሊቢያ መሪዎች ገንዘቡን ለማስመለስ በውጪ የምንገኝ አገርና ወገን ወዳድ ዜጎች ጥረት እናደርጋለን። ለዚህ አቅሙም፤ዝግጁነቱም አለን”ብለዋል።

ዶ/ር አክሎግ በገለፃቸው ማጠቃለያ ህዝቡ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል በአፅንኦት በመግለፅ፤ እርሳቸውም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

“ግመል የሚያሻግሩትን መርቆ እየሸኘ፤ መርፌ በሚወስዱት ላይ ይበረታል” የሚባለው የኢትዮጵያ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፤ ባለፉት አስር ዓመታት ለፍርድ ቤት ባቀረባቸው ከ500 በላይ ክሶች፤ አንድንም የመንግስት ባለስልጣን ለመክሰስ እንዳልደፈረ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።

ኮሚሽኑ በቅርቡ 10ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያቀረቡት ምሁር ”ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የመንግስት ተሿሚዎችን ይፈራል”ማለታቸው ይታወሳል።

ፀረ-ሙስና ኮሚሽኑ መቋቋሙን ተከትሎ ዝርፊያው ተባብሷል የሚሉ ውስጥ አዋቂዎች ደግሞ፤ የቀበሌ ገንዘብ ያዦችን እንዲቀጣ የተቋቋመ የሚመስለው ይህ ኮሚሽን- ይህችን ድሀ አገር እንኳን ከሙስና ሊታደጋት ቀርቶ ይባሱኑ ለታላቅ ዝርፊያዎች ሽፋን በመስጠትና ሙስናን በማስፋፋት የአገሪቱን ድህነት እያባባሰ ነው በማለት ሲከሱ ይደመጣሉ።