ኤርትራዊ ዲፕሎማትን በማጉላላት የህወሃት አገዛዝ የፀጥታ ሃይሎች ወንጀል መፈፀማቸዉን አንድ የኤርትራ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን አስታወቁ

አለም አቀፍ ህግንና የቪየና ስምምነትን በመፃረር የህወሃት የፀጥታ ሃይሎች ባሳለፍነዉ ሳምንት አንድ ኤርትራዊ ዲፕሎማትን በቦሌ አለም አቀፍ አዉሮፕላን ጣቢያ የያዟቸዉን የግል ንብረቶችና ሰነዶች በመንጠቅና በመፈተሽ ወንጀል መፈፀማቸዉን አምባሳደር ፍስሃ ፅዮን ጴጥሮስ በኤርትራ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን ገለጸዋል።

ከአዲስ አበባ በካይሮ በኩል ወደ አስመራ በመሄድ ላይ የነበሩት ዲፕሎማት፣ ተገቢዉን ህጋዊ የኢሚግሬሽን ደንቦችን ያሟሉ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሎቹ የያለመነካት የዲፕሎማቲክ መብታቸዉን በመግፈፍ እንዳንገላቷቸዉና እንዳጉሏሏቸዉ ተናግረዋል።

የዲፕሎማቱን ሻንጣ፤ ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተር ከመፈተሽ አልፎ ተርፎ ከአንድ ሰአት ተኩል በላይ በአዉሮፕላን ጣቢያዉ በእስር እንዳቆዩዋቸዉ እኒሁ የኤርትራ መንግሰት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ገልፀዋል።

አዉሮፕላን እስኪሳፈሩ ድረስ የፀጥታ ሃይሎቹ በኤርትራዊዉ ዲፕሎማት ላይ ከፍተኛ ክትትል ሲያደርጉባቸዉ እንደነበር የገለፁት አምባሳደር ፍስሃፅዮን፣  የህወሃት አገዛዝ በአለም አቀፍ ህግና በቪየናዉ ስምምነት መሰረት ለተፈፀመዉ ወንጀል በህግ እንደሚጠየቅ መግለፃቸዉን ኦል አፍሪካን ኒዉስ የዜና አገልግሎት ገልጿል።

ህወሃቶች በጫካ ካሳለፉት ዕድሜ በላይ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች መናሄሪያ በሆነቺው አድስ አበባ ሚኒሊክ ቤተመንግሥት ውስጥ እየኖሩ ቢሆንም የመንግሥት አስተዳደርና የህግ የበላይነት የመሳሰሉ ኢሴቶች እስከዛሬ እንዳልተዋሃዳቸው ከሚወስዱት እርምጃ መገምገም ይቻላል የሚሉ ዲፕሎማቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። ወያኔ በዱሬ እንስሣ ህግ እንደሚመራ በምርጫ 97 ቅስቀሳ ወቅት በሰፊው ሲገለጽ እንደነበረ አይዘነጋም።