የመጽሐፍ ግምገማ የኢትዮጵያ ባህል መድሐኒት በሳይንሳዊ አቀራረብ

በወርቁ አበበ (ፒኤችዲ በፋርማኮሎጂ)

የመጽሐፉ አርሰት፦ የኢትዮጵያ ባህል መድሐኒት በሳይንሳዊ አቀራረብ- የመድሐኒት እጽዋት

ደራሲ፦ ዶክተር ፈቃዱ ፉላስ

አሳታሚ፦ AJ Phillips Publishing, South Sioux City, NE, USA

የታተመበት ጊዜ፦ 2010 (2002 ዓ.ም.)

የገፅ ብዛት፦ መጽሐፉ 13 በ 20 ሴንቲ ሜትር ሰፋት ያለው ሲሆን 259 ገጾች የያዘ ነው።

ይህ መጽሐፍ በቅርብ የወጣ ነው። ሰለሆነም በትኩሱ የማንበብ እድል አጋጥሞኛል። በመጽሐፉ የሰፈረው ሓሳብ ከማውቀ የሞያ መስክ ጋር ከሞላጎደል የተገናዘበ ሰለሆነ፤ አጭር ግምገማ ለመሰጠት ፈለግሁ።

ከአርሰቱ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያ የእጽዋት መድሐኒቶች ባሕላዊ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ነው። መጽሐፉ ለምን እንደተጻፈ ደራሲው እነደዚህ ሲሉ ግልጸዋል፦

“በኢትዮጵያ ባህል መድሐኒቶች ላይ በአማርኛ የተጻፉ መጽሐፍት ጥቂት ናቸው። ከነዚህም ብዙዎቹ ያተኮሩት በእጽዋቱ ሰሞች፤ የሚበቅሉባቸው አካባቢዎች፤ ለምን ደዌዎች ጥቅም እንደሚዉሉና በአቀማመማቸዉና አወሳሰዳቸዉ ላይ ነው። ነገር ግን በእዕጽዋቱ ላይ የተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶችን አያካትቱም። ይህ መጽሐፍ ይህንን ጉድለት ለማሟላት ይሞክራል። ጥናቱን እንደዚሁ ለይሰሙላ ብቻ ለማንሳት ሳይሆን ወደፊት ባህላዉ መድሐኒቶችን ለማዳበር ለሚደረገው ጥረት እንዲያግዝ የጠቃሚ ጭብጦችን መሠረት ለመጣል ነዉ።”

መጽሐፉን አንብቤ እንደጨረሰኩ በአርግጥ ደራሲው እንደገለጹት ተብሎ የተጻፈ መሆኑን አረጋግጫለሁ። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰፍኖ ባለው ባህላዊ የእጽ መድሐኒቶች አጠቃቀም አኳያ ሲታይ የዚህ አይነቱን መጽሐፍ አዘጋጅቶ ለአንባቢያን ማቅረብ ጠቃሚ ሰለሆነ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው።

መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳቸውን ጉዳይ ሰርአት ባለው መልክ ለማከናወን ደራሲው ዶክተር ፈቃዱ የመጽሐፋቸዉን ዋነኛ ክፍል በአምሰት ምእራፎች በመከፋፈል ሃሳባቸውን አሰፍረዋል። ምእራፍ አንድ ሰለባሕል መድሐኒቶችና የባሕል መድሐኒት አዋቂዎች ትርጉም፤ ሰለእጽዋት መድሐኒቶች ተፈጥሮና ምንጮች፤ እንደዚሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰለሚገኙ የባህል መድሐኒቶች አግልግሎት የሚገልጽ ነው። ምእራፍ ሁለት በተልይ በኢትዮጵያ የባሕል መድሐኒት ታሪክ፤ በባሕል መድሐኒት ቁጥጥር ደንቦች፤ በበሽታ መንሲዎች፡ በባሕል መድሐኒት ጎጂነት፤ በባሕል ህክምና ዘርፎችና በባሕል መድሐኒት አዋቂዎች ስልጠና ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። ምእራፍ ሶሰት ሰለኢትዮጵያ የባሕል መድሐኒቶች እውቀት አሰፈላጊነት፤ በአገሪቱ የባህል መድሐኒቶች ላይ ሰለተደረጉ ምርምሮችና ዓድገቶች፤ በባሕልና በዘመናዊ የሕክምና ዘዴዎች መካከል ሰላለው ግንኙነትና ስለእጽዋት እንክብካቤ ሁኔታ የሚያውሳ ነው። ምእራፍ አራት ያተኮረው በቁጥር 32 በሆኑ የኢትዮጵያ የባሕል መድሐኒት እጾች ላይ ሲሆን በእያንዳንዱ እጽ ሰር የአማርኛና የሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መጥሪያ ስሞች፤ ሳይንሳዊ ሰም፤ የእጹ ስርጭት፤ የእጹ አካላዊ መግለጫ፤ የእጹ መድሐኒትነት/ጥቅም፤ የእጹ አወሳደድ፤ የእጹ ጎጂነትና ሰለቀረቡ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችና ማጠቃለያ ሃሳቦች በዝርዝር ተገልጸዋል። ይህ መእራፍ የመጽሐፉ እንብርት ነው ለማለት ይቻላል። በምእራፍ አምሰት የተካተቱት ከላይ የተጠቀሱትን የ32ቱን እጽዋት ባሕላዊ የመድሐኒት አገልግሎትና አወሳሰድ አሳጥሮ የሚያሳይ ሰንጠረዥ፤ የአማርኛ ቃላት መፍቻና የእንግሊዝኛ አቻዎቻቸውን የሚያመለክት ትንተናና የማጣቀሻ ጽሑፎች ናቸው።

በምእራፎች ተከፋፍለው ከሰፈሩት ገለጻዎች በተጨማሪ ደራሲው መጽሐፋቸውን የጀመሩት በትንሽ የመንደርደሪያ ግጥሞች ሆኖ ለሰራ ዝግጅት ሲያደርጉ ላነሷቸው ልዩ ልዩ ተግባራዊ ጥያቄዎች እራሳቸው የሰጡትን መልሶች በመቅድም መልክ ቀጠል አርገው በማከል ነው። እነዚህን የጥያቄ መልሶች አንብቦ ማወቁ ሰለመጽሐፉ የበለጠ ግንዛቤ ለማግኘት የሚበጅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ባጭሩ ይህ የዶክተር ፈቃዱ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ባሕላዊ የእጽዋት መድሐኒቶችን አሰመልክቶ በማሰረጃ የተደገፈ ሳይንሳዊ ትንተና ቀለል ባለ ሁኔታ የሚሰጥ ነው። እሰካሁን እሰከማውቀው ድረሰ የዚህ አይነቱ ሳይንሳዊ ይዘት ያለው መጽሕፍ በአማርኛ ተጽፎ ሲቀርብ የመጀመሪያው ነው። ይህ ሁኔታ ለአማርኛ አንባቢዎች ሰለአገራቸው መድሐኒቶች የማወቅ እድል ሰጪ ሰለሚሆን ጠቃሚ አሰተዋጽኦ ነው። ጠቀሜታው በእጾች የመድሐኒትነት አገልግሎት ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የአገርንም ቋንቋና ባሕል ለማዳበር የሚረዳ ይሆናል። በመጽሐፉ አንዳንድ አነሰተኛ የሆኑ የአጻጻፍ ግድፈቶች ቢኖሩም በአጠቃላይ በአቀራረቡም ሆነ በያዘው ቁም ነገር መጽሐፉ ደራሲው ያለሙትን ግብ ለመምታት ያሰቻላቸው ነው ለማለት ይቻላል። ሰለዚህ ሰለኢትዮጵያ የባሕል መድሃኒቶች (በተለይም ሰለእጽዋት) አጠቃቀም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማወቅ የሚፈልጉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ሊኖራቸው የሚገባ መጽሕፍ ነው። ይህ ከታመነበት ደራሲውን በኢሜል [email protected] በመገናኘት ሰለመጽሐፉ መጠይቅ ይቻላል።

በመጪው ዓመታት በሳይንሳዊ ምርምር በእጽዋት ላይ ያለው እውቀት ጠቀም ባለ ሁኔታ ሲጨምር ደራሲው እራሳቸውን በዚህ በአሁኑ አሰተዋጽዋቸው ሳይገቱ መጽሐፋቸውን በማደሰና በማሻሻል ወደፊት እንደሚያቀርቡልን ተሰፋ አደርጋለሁ። በዚያን ጊዜ በመጽሐፋቸው ከሚቀርቡት ብዙ ቁም ነገሮች መካከል የእጽዋቱ ፎቶግራፎች/ሰእሎችና አሁን ያልቀርቡ እጽዋት እሰከሚቻል ድረሰ ቢታከሉ የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።