አቶ አባዱላ ገመዳ አፈጉባኤ፣ መለስ ዜናዊ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ
(AddisNegerOnline.com) — በአሁኑ ሰዓት በተወካዬች ምክር ቤት እየተካሄደ ባለው ጉባኤ በኢፌድሪ ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ንግግር የተከፈተ ሲሆን የፕሬዝዳንቱን ንግግር ካደመጠ በኋላ አቶ አባዱላ ገመዳን በአፈ ጉባኤነት አቶ መለስ ዜናዊን በጠቅላይ ሚኒስትርነት መርጦ ለሻይ እረፍት ወጥቷል፡፡
የህዳሴ ሀሳብ በማቅረብ፣ ሀገራችን ባለ ድርብ አሀዝ እድገት ያመጡ ስለሆነ፣ በዓለም አደባባይ ለሀገራቸውና ለአህጉራቸው ኩራት እየሆኑ ስለመጡ ድርጅታችን ኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አገሪቱን እንዲመሩ በድጋሚ መርጧቸዋል ሲሉ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡
አፈ ጉባኤ አባዱላ በበኩላቸው አንቀፅ ጠቅሰው አቶ መለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸውን ካበሰሩ በኋላ ቤቱ ከፍተኛ ጭብጨባ ያሰማ ሲሆን አቶ መለስ ራሳቸውም ሲያጨበጭቡ ታይተዋል፡፡ በኋላም እያጨበጨበ ለነበረው ለምክር ቤቱ አባላት ቆም ብለው እጅ ከነሱ በኋላ ቃለ መሀላ ፈፅመዋል፡፡
በእለቱ በአፈ ጉባኤነት የተመረጡት አቶ አባዱላ ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰሩ በመቆየታቸው በአዳራሹ የተገኘውን ሁሉ ሲያዝናኑ ነበር፡፡ እርሳቸውም በተሳሳቱ ቁጥር ሲስቁ ታይተዋል፡፡