ፍኖት – ስለ ፌደራሊዝሙ እኔም የምለው አለኝ በሰለማኦን ስዮም

“በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ማግኘት የሚገባውን ነገር ከብሔር ክልሉ ውጭ በመኖሩ ብቻ ያጣል፡፡”

በዚህ ጭብጥ አገባብ ላይ እንዳልነው፣ የጋራ ጥቅም ያላቸው እና በራስ ገዝ እና ክልላዊ የመንግሥት የስልጣን ቁጥጥር የተጠመዱ ልሂቃን፣ ወደ ፓርቲነት ሲመነዘሩ `የማዕከላዊ ስርዓት` መንስኤን ያሳያል፡፡ ማለትም ባለው የፓርቲ ስርዓት “ኢህአዴግ [ማለት] ህወሓት የበላይ አገር የሆነበት የብሔር ተኮር ፓርቲዎች ጥምረት ሆ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ደግሞ አጠቃላይ የፌዴራል ስርዓቱን ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም በክልላዊና ንዑስ ክልላዊ መንግስታት አስተዳደር ውስጥ በስፋት ጣልቃ ይገባል፡፡” ደንበኛ (client) ሆኖ ለመቆየት ብቻ የሚውተረተሩ ፓርቲዎች በክልላዊ ጉዳያቸውም ቢሆን ፓትሮኑን ፓርቲ እስካላስደሰቱ ድረስ ደህንነት አይሰማቸውም፡፡” ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው፣ ፌዳራሊዝም ኮሙኒስት ፓርቲው ጥበቃ ቁጥጥር በመያዙ ላይ መሠረት ያደረገው የሶቭየት ሞዳል” መሆኑን ፕ/ር መሳይ ይገልፃሉ….

በመስከረም 16 2004 ዓ.ም የወጣችው ፍኖተ ነፃነት የዶ/ር አይሉ አርአያን “በቅርፅ ፌደራላዊ በተግባር አሃዳዊ” የሚል ፅሑፍ ይዛ ወጣች፡፡ ዶ/ር ሀይሉ እንደፈለጉትም ርዕሱ ሀሳብ ማጫሩ ተሳክቶለት መስከረም 19,2004 ዓ.ም የወጣችው ፍትህ ጋዜጣ የአቶ ቡልቻ ደመቅሳን” እኔም የምለው አለኝ” የሚል ፅሑፍ ይዛ ወጣች፡፡

ታዲያ በኔ ላይም ሐሳብ ጭራ ኑሮ “እኔም ስለ ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የምለው አለኝ” እያልኩ ነው፡፡ ልክ እንደ ዶ/ር ሀይሉ ሁሉ የኔም ፅሑፍ የውይይት መነሻ እንጂ የነገሩ መጨረሻ ያለመሆኑን ከወዲህ ልግለጥ፡፡

በኔ እምነት በኢትዮጵያ ያለው ሰርዓት እውነተኛ ፌዴራሊዝም ነው አይደለም በሚል ሀሳብ መሰናዘር ጉንጭ አልፋ ይመስለኛል፡፡ በመሆኑም ህወሓት /ኢሕአዴግ እንዴት ለአደባባይ ትችት ሳይጋለጥ የፌዴራል መንግሥቱን አህዳዊ በማድረግ ጠቀለለ ለሚለው መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በተግባር አህዳዊ እንደሆነ የተደረገው ህወሐት ከመጀመሪያው የብሔር ሥርዓትን ሁን ብሎ በማበረታታቱ ነው እላለሁ፡፡ ወይም የብሔር ቡድኖቹ የህወሐት የራሱ እጅ ስራ ከመሆናቸው የተነሳ በራስ መተማመን ፈፅሞ ማዳበር እንዳይችሉ ሆነዋል፡፡

በመዳረሻ (end) እየተስማሙ ወደዚያው በሚወስደው መንገድ (means) ያለመስማማት የዴሞክራሲያዊና ሳይንሳዊ አካሄድ ገፅታ ነው፡፡ የብሔር ነፃነትና እኩልነት መረጋገጥ ድል ነው፡፡ ድል መሆኑ የሚቀረው ግን ይህንኑ የሚያረጋግጥ እውነተኛ መንገድ (በዚህ አጋጣሚ ፌዴራሊዝማችን) በሌለበት፣ የፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነት መዳረሻ (end) መሆኑ ሲሰበክ ማየት ነው፡፡ “ለመሆኑ ይህ እንዴት ሆነ?” ማለታችን አይቀሬ ነው፡፡ የብሎርተኝነት አንደኛው ቲዎሪ (theory) በልሂቃን ስልጣን የመቆጣጠር ትግል ውስጥ ያለ አንደኛው ወሳኝ አንጓ (variable) ነው ይላል፡፡

ማለት ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለችው ፌዴራሊዝም ለብሔር ግጭቶች እና ለካድሬዎች የማያልፉ “የድል ስካር” ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህ ያለምክንያት የመጣ አይደለም፡፡ ከዚህ ሴራ ነዳፊ ውጭ ያሉትን የብሔር ኢሊቶች በተጥሮአዊ በሆነ መልኩ ከፌዴራል መንግሥቱ ጉዳይ ለማለቅ የተነደፈ ነው፡፡

ይህን ሀቅ የሚያረጋግጡልን በኦህዮ ደይተን ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር የሆኑት ፕ/ር መሳይ ከበደ ናቸው፡፡ እንደ ፕ/ር መሳይ “የኢትዮጵያ ስርዓት ከአተገባበሩ ባሻገር የብሔር ስርዓትን ለማበረታታት ሆን ተብሎ የተመሰረተ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ በምሳሌ ሲያስቀምጡም “እንደ ናይጄሪያ፣ ህንድ ወዘተ… የመሳሰሉት ሌሎች ሀገራት የብሔር ፌዴራሊዝም ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ በሚጎዳ መልኩ የብሔር ማንነትን ወደ ማጠናከር ያዘምማሉ፡፡” ይላሉ፡፡

የህወሓት ማጠንጠኛ የአማራ ልሂቃንን የበላይነት ማብቃት ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን ግን፣ ሀገሪቷ የጭቁን ብሔር ብሔረሰቦች ማጎሪያ መሆኗን ማስረገጥ ነበረበት፡፡ ህወሓት ያነሳውን አጀንዳ የሚደግፉ ብሔር ተኮር ልሂቃኖች፣ በብሔራቸው ላይ እየተደረገ ያለውን “ጭቆና” በመስበካቸው ከህወሓት ጋር የጋራ ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡ ነገር ግን ተፎካካሪ በመሆን ከቀደምቱ ህወሓት ጋር መሄድ አይችሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ህወሓት የፍላጎታቸው እና ጥያቄያቸው ቀለዒም ጭምር ነውና፡፡ በመጨረሻም የክልል ልሂቃኖቹን ትኩረት “በራስ ገዝ (self-rule) እና ክልላዊ አስተዳደር ቁጥጥር” ላይ ስለሚያደርግ የፌዴራል መንግሥቱን ጉዳይ ለቀደምቱ ህወሓት እንዲታው የሚያስገድድ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡

አቶ ቡልቻ እንደገለፁት ህገ መንግሥታዊ መብቶችና በመሬት ላይ ያለው እውነታ ተቃርኗዊ መሆናቸው እመን ነው፡፡ ይህ የዶ/ር ሀይሉም ሀሳብ ነው፡፡ ፕ/ር መሳይ የዚህን ችግር መንስኤ ሲገልጹ “በንድፈ ሀሳብ እና በአተገባበር መካከል ስላለው ልዩነት የተጠናቀረና ሁሉን ያካተተ ምልከታ መስጠት የሚቻለው ብሔርተኝነት የመንግሥትን ሥልጣን በልሂቅ ቡድኖች ከመቆጣጠር ጋር ሲነፃፀር ለዴሞክራሲ የሚሰጠው ቦታ ያነሰ መሆኑ በታመነ ጊዜ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡

በኔ እምነት ይህ እውነታ የህወሓትን ፕራይሞርዲየሊስት (ብሔርተኝነት የራስን ዕድል በራስ መወሰን አለበት የሚል) መሆን የሚናገር ነው፡፡ ነገር ግን የፕራይሞርዲያስት ተፈጥሮ አንድ ክፉ ተቃርኖ አለበት፤ “በትግበራና በንድፈ ሀሳብ መካከል ያለውን ልዩነት ለማስረዳት ሙሉ በሙሉ ይሳነዋል፡፡” የተቃርኖም ምንጭም የህወሓት ፕራይሞርዲያሊስት መሆን ሆኖ ውሳኔዎቹ ግን የጥቅም ድምር ውጤቶች እንጂ ህወሓት የተመደበበት ፕራይሞርዲያሊዝም ያለመሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የፌዴራሊዝማችን ውጤት ከህወሓት ፕራይሞርዲያሊዝምነት የሚመነጭ ቢሆን ኑሮ የህወሓት “ድል” የትግራይን መገንጠል አሊያም እውነተኛ ፌዴራላዊ እና ራስ ገዝ ሥርዓት እንዲተገበር በፈቀደ ነበር፡፡

እንደሚታወቀው ከሕወሓት በላይ የኤርትራን ነፃነት የሚደግፍ የለም፡፡ በታጋይ መለስ ዜናዊ ከተፃፉት የኤርትራ ህዝብ ትግል ትኩረት ያደረጉ መፃህፍት በተጨማሪ የመገንጠሉን ተግባራዊነት በማስፈፀም ከህወሓት የሚቀድም ኤርትራ ድርጅት አንኳ ያለ አይመስልም፡፡ ህግሓኤም ቢሆን እላለሁ፡፡ ነገር ግን ፕራይሞርዲያሊስቱ ህወሓት እንደ ምን የኤርትራን ነፃነት/ መገንጠል ሲደግፍ የሶማሌና ኦሮሚያ አካባቢ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ክፉኛ ጠላ ለማፈን ተንቀሳቀስ? ይህ ተቃርኖ ግልፅ የሚያደርገው ነገር ቢኖር-“ የኢትዮጵያ ስርዓት የብሔር ክፍፍልን የሚያበረታታ ቢሆንም በጣም ማዕከላዊ ሆኖ መቅረቱን …. ጥቅም” የሚገዛው መሆኑን ያሳያል፡፡

በዚህ ጭብጥ አገባብ ላይ እንዳልነው፣ የጋራ ጥቅም ያላቸው እና በራስ ገዝ እና ክልላዊ የመንግሥት የስልጣን ቁጥጥር የተጠመዱ ልሂቃን፣ ወደ ፓርቲነት ሲመነዘሩ `የማዕከላዊ ስርዓት` መንስኤን ያሳያል፡፡ ማለትም ባለው የፓርቲ ስርዓት “ኢህአዴግ [ማለት] ህወሓት የበላይ አገር የሆነበት የብሔር ተኮር ፓርቲዎች ጥምረት ሆኖ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ደግሞ አጠቃላይ የፌዴራል ስርዓቱን ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም በክልላዊና ንዑስ ክልላዊ መንግስታት አስተዳደር ውስጥ በስፋት ጣልቃ ይገባል፡፡” ደንበኛ (client) ሆኖ ለመቆየት ብቻ የሚውተረተሩ ፓርቲዎች በክልላዊ ጉዳያቸውም ቢሆን ፓትሮኑን ፓርቲ እስካላስደሰቱ ድረስ ደህንነት አይሰማቸውም፡፡” ከዚህም መገንዘብ የሚቻለው፣ ፌዳራሊዝም ኮሙኒስት ፓርቲው ጥበቃ ቁጥጥር በመያዙ ላይ መሠረት ያደረገው የሶቭየት ሞዳል” መሆኑን ፕ/ር መሳይ ይገልፃሉ፡፡

ይህ ግን፣ የክልሎች መብት፣ የውስጥ ጉዳያቸውን በተባለው ልክ ይወስናሉ /ይቆጣጠራሉ ማለት አይደለም፡፡ ይህ እንዲሆን ተፈጥሮአቸው አይፈቅድም፡፡ እንደ ፕ/ር መሳይ አባባል “ይልቁንም መሃል ተቀማጩ በጥገኛ የአካባቢ ልሂቃን አማካኝነት ቁጥጥሩን እንደያዘ እንዲቆይ የሚያመቻቹ ደንበኛ (client) ፓርቲዎችን ስርዓት ይፈጥራል፡፡”

የህወሓት አቋም ይህ እንዲሆን ከሆነ፣ የኤርትራ ከኢትዮጵያ መገንጠል ትክክል ነበር ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ቫዕቢያ ለህወሓት ጥገኛ መሆንን መቀበል ቀርቶ ሕወሓት የእኩልነት ሒሳብ እንኳ አይስማማም፡፡ ይህን ሐቅ ለማረጋገጥ ብዙ ምንጮችን ማገላበጥ የሚቻል ቢሆንም የረዳት ፕ/ር መድኃኔ ታደሰ “የኤርትራና የኢትዮጵያ ጦርነት የግጭቱ መነሻና መድረሻ” መፅሐፍ ብቻ የላቀ ትርጉም አለው፡፡ ህወሓት “…… የትኛውንም ያህል ፖለቲካዊ ብስለትና ወታደራዊ ብቃትን ቢያስመዘግብ ህወሓት የህግ ሃኤን ክብር ለማግኘት አልታደለም ነበር” (መድኃኑ 91) “…….. ኤርትራውያን ህወሓት ያሳየውን ለውጥ ይህን ያክል ክብደት የሚሰጡት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ህግሃኤ በህወሓት ላይ የበላይነት ስሜትን ስለሚንፀባርቅ ነበር፡፡ የፈለገውን ያክል ውጤት ቢያስመዝግቡም ህግሃኤ የትግራዮችን ብቃት ይለካ የነበረው በድሮው የተዛባ መሰፈርቱ ነበር” /መድኃኔ 92) የሚሉ ሌሎችም ናቸው፡፡

ስለዚህ ህወሓት በኢትዮጵያ የዘረጋው ስርዓት እና አተገባበሩ ትርጉም የሚሰጠው በኤርትራ ላይ የነበረው የመገንጠል አቋሙ እና በኢትዮጵያ ደግሞ” የአናሳ ብሔር ቡድን ጥቅሞች” እንዲከበሩ የሚጥር የልሂቃን ቡድን የበላይነቱና እንዲጠብቅ የሚሊዳ ስርዓት መዘርጋቱ ስታወቅ ነው፡፡

ለመሆኑ በምርጫ 2002 የነበሩት 95 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስርዓቱን ዴሞክራሲዊነት ያረጋግጣሉን? በኔ እምነት ፍፁም አይችሉም፡፡ ይህ የህወሓት ፖሊሲ (ስለ) በተዘዋዋሪ ያመጣው የቀውስ ውጤት ነው፡፡ ማለትም ህወሓት በነበረው የብሎር ተኮር እንቅስቃሴ ያተኮረው ይህንኑ ፍላጎት በማንገብ ደንበኛ (client) ለመሆን የሚነሱ የብሔር ቡድኖች በሽ በሽ እንደሚሆኑ በማረጋገጡ ነበር፡፡ ይህ ነው ማለት ነው በተግባር የታየው የ95ቱ ፓቲዎች ጉዳይ፡፡ ህወሓት ፕራሞርዲያሊስት ነው ብዬ ነበር፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና “Ehtiopia competing ethnic nationalism and the qwest for democracy, 1960 -2000” በተባለው መፅሐፋቸው ኤስማን የተባለ ፀሐፊ ጠቅሰው እንደፃፉት “ብሔርተኝነት የጋራ ማንነት ነው፤ በመሆኑም ባለፉት ታሪካዊ ክንዋኔዎች ጠልቆ የሚገባ እይታ ስለሚኖረው የሰዎችን ግንኙነት በሚመለከት እንደ ነባራዊ /ተፈጥሯዊ/ given) መቀመጥ አለበት የሚል ነው” ይላሉ፡፡

በመሆኑም የህወሓት ምደባዬ ሙሉ በሙሉ እንደማይሰራ አሳይቼ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ፕ/ር መሳይ “ብሎርተኝነት እንደ የማንነት ሀሳባዊ ደግሞ ፈጠራ ተደርጎ ሳይተረጎም ኢንስትሩሜንታሊዝም (ብሔርተኝነት ልሂቂን ለመንግሥት ስልጣን በሚያደርጉት ፉክክር በብሔር ማንነት ስም ህዝብን የሚቀሰቀሱበት መንገድ መሆኑን የሚናገረው የት/ት እሳቤ የትግራይን የብሔር ምደባ” አያብራራም ይላሉ፡፡ ትግራይ 3000 ዓመታት ዕድሜ አለው የሚባለው የኢትዮጵያ (አቢሲኒያ) ታሪክ አካል ናት፡፡ ህወሓት ትግራይን ነፃ ሊያወጣ የታገለው፣ ተመሳሳይ የፖለቲካ ስርዓት እና የባህል ስብጥር ካለው ቡድን ነበር ከአማራ ልሂቃን /ገዢዎች፡፡ ይህ የታሪካዊ ሀቆች ድህነት ሕወሓት በቋንቋ ልዩነት ላይ ብቻ በማተኮር የትግራይ ብሔርተኝነትን እንዲገነባ አስገደደው፡፡

ኢትዮጵያ ሊሂቃን የፖለቲካ ግባቸውን ለማሳካት ብሔርተኝነትን መስፈርት ማድረጋቸው የክበቡን ጥልቅ ተቃርኖ የሚፈትን ነው፡፡ የኤርትራንና የትግራይን ጨምሮ አባዛኛዎቹ የብሔር ንቅናቄዎች መነሻ በጠበቀ ማዕከላዊነት አማራን ባህል ስነልቡናና ቁሳዊ ጥቅሞችን ማዕከል አድርጎ ተገበረ ከሞሉት የዘመድ ሥርዓት ጋር አልነበረምን ታዲያ መፍትሄው በተማከለ ዴሞክራሲያዊነት የህወሓት የበላይ አጋርነት የሚታይበት የተማከለ የሥልጣን ሥርዓት ነው? በራስ ገዝና የቡን መብቶች ላይ ማተኮር መፍትሄ ነውን? እኔ የፕ/ር መሳይን “…. ኢትዮጵያ ባለብዙ ብሔር ሀገር ለመሆኗ እውቅና በመስጠት ያልተማከለ የሥልጣን ሥርዓት /decenteralization/” መዘርጋት መፍትሄ እጋራለሁ፡፡

በመሆኑም በአሁኑ አሰራር አንድ የማይታየው ሀቅ የብሔር ቡድኖች የብሔር ብሔረሰቦችን ቦታ የሚተካ ትርጉም እንዲያገኙ በመደረጉ ቦርጫም ካድሬዎች፣ መሬት የሚቸበችቡ ካድሬዎች፣ ሀገር የሚገዙ የሚሸጡ እና የሚወክሉ ካድሬዎች የተጠበቁ (protected) /ባለመብት/ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የነዚህ ቡድኖች መነካት የብሔረሰቦችን መሳካት ሆኖ በመተርጎሙ፡፡ ውጤቱ ደግሞ ብዝሃ ብሔር ላይ የተመሠረተ ስርዓት ለመገንባት ሲባል ሲቃወሙት የነበረውን ብሔረ መንግሥት (nationstate) ደገሙ ማለት ነው፡፡

ኢህአዴግም እንድሜ ዘመኑን ወደ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት ከማይቀየርባቸው ነገሮች አንዱ የብሔር ኮታ ያላቸው ሲነኩ የተገኙበት ብሔር እንደተነካ አድርጎ በማሳየት እራሱን ለመከላከል ነው፡፡ በአጠቃላይ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ትክክለኛና ዴሞክራሲያዊ የህግ ድንጋጌ የሚደግፈው ፌዴራሊዝም ባለመኖሩ አሁን በሚተገብረው የብሔር ፌዴራሊዝም አካሄድ ተጨማሪ የብሔር ቡድኖች እንደ እንጉዳይ እዚያም እዚህም እንዲፈሉ ከማስቻሉም በላይ የበለጠ የአክራሪነት ባህሪ ያላብሳቸዋል፡፡

በመጨረሻም ለብዙ ጊዜያት ስለ ብሔራዊ ዕርቅ ተጠይቆ ብዙ ጊዜ የአሉታ መልስ የሰጠው ኢህአዴግ የመጨረሻውን የእንቢታ ዲስኩር ያካሄደው በአንደኛ የዚውኑ ብሔርተኝነትን ባቀነቀነው አቶ ፊዲዋን ሁሴን በ2001 ዓ.ም የክረምት ወቅት ለመምህኖ በተደረገው የፕላዝማ ጠመቃ ወቅት ነበር፡፡

በመጨረሻም ሌላው ቀርቶ የህገ-መንግሥቱ አንቀፅ 32.1 ን በአግባቡ የሚረዳ የለም፡፡ የክልሎች ሀብት፣ ንብረት እና ቁሳዊ ቦታው ለክልሉ ተገቢነቱ ቴክኒካዊ አገላለፅ መሆኑን የሚረሱ አሉ በተለይ በታችኛው ጥቃቅን አነስተኛ አባላት ዘንድ በፍፁምና በመውሰዳቸው የዜጎች ከክልል ክልል በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመኖር እና ሀብት ማፍራት እንደሚገደብ ገልጫለሁ፡፡ አሊያም በኢትዮጵያዊነቱ ብቻ ማግኘት የሚገባውን ነገር ከብሔር ክልሉ ውጭ በመኖሩ ብቻ ያጣል፡፡ በኔ አስተሳሰብ በኦሮሚያ ክልል /ሌላም ሊሆን ይችላል/ ከ5ኛ ክፍል `ሀ` ብሎ የሚጀምረው የአማራኛ ት/ት የኦሮሞ ኤሊቶች በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ቀስበቀስ ይቀንሳል፡፡ ቋንቋ መግባቢያ ነው፡፡ አማርኛ የፌዴራል መንግሥት መግባቢያ ነው፡፡ በመሆኑም አቋማቸውን መግለፅ የማይችሉ ነገር ግን በኮታ ቢቻ የሚወክሉ ግዑዝ ፓለቲከኞች ይሞሏታል፡፡

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።

የፍኖት እትም አሥርን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ