[አንድ ለቅዳሜ!] ይቅርታ ለብርቱካን ወይስ ይቅርታ ከብርቱካን? ይቅር ባዩ ማነው?
ብርቱካን ለዳግም እስራት ከተዳረገች ጀምሮ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዳች ዓይነት ለውጥ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል የገመቱ ጥቂቶች ሳይሆኑ አይቀሩም። ለውጡ እጅግ ለስላሳና ገር የሚመስል ነገር ግን ብዙ ዜጎች የሞራል እና የፖለቲካ ጥያቄዎችን መላልሰው እንዲያስቡ የሚያደርግ ለስላሳ አብዮት መሆኑን እየቆየም ቢሆን መረዳት አዳጋች አልሆነም። አንድ ነገር ግን እርግጥ ነው፤ ለራሷ ለብርቱካን ጭምር መታሰሯ የሚፈጥረው ውጤት ይህ ይሆናል ብሎ መረዳት እጅግ አስቸጋሪ ነበር፤ የቀደመ ተሞክሮ ቀርቶ የበሰለ ንግግር እንኳን ያልተደረገበት የትግል ስልት በመሆኑ።
አለመታደል ሆኖ አቶ መለስ እና ብዙዎቹ ተከታዮቻቸው አንድ የማይወዱት የአብዮት አይነትና ቀለም አለ፤ ብርቱካናማ አብዮት። ለክፋቱ ደግሞ ልጅቷ (እንዲህ እንድጠራት ይፈቀድልኝ) ስሟ ብርቱካን ሆኖ ተገኘ። በሌላ ኢሕአዴግ ፈጽሞ ባልገመተው ምክንያትም ልጅቷ የአንድ ዝምተኛ አብዮት ተምሳሌት ለመሆን በቃች። የሞራል ልዕልና፣ የሰብአዊ ማንነት ክብር ፖለቲካ ውስጥ ዋጋ ያለው የአመለካከት መሠረት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ትግል መሣሪያ ሊሆን እንደሚቸል በተግባር ለማሳየት የሞከረ ፖለቲከኛ ሲያጋጥመን ቢያንስ ለእኔ ትውልድ የመጀመሪያችን ነው። ይህን የምታደርገው አንዲት ወጣት እና የተማረች ሴት መሆኗ ደግሞ ነገሩን የበለጠ ያጎላዋል። ከዚያም በፊት በሞራልና በሰብአዊ ክብር መነሻነት መንግሥትን የተቹ፣ ሹመኞችን የሞገቱ ሰዎች ቢኖሩም እነዚህ ሰዎች በአብዛኛው የፖለቲካ ስልጣንን የሚፈልጉ አልነበሩም። ፖለቲከኞቹ ደግሞ የብርቱካንን እጣ ለመጋፈጥ አልፈቀዱ ይሆናል።
ብርቱካን ዳግም የታሰረችበት ሁኔታ ለብዙ ኢትዮጵያውያን አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ጭምር እንደሚሆን አምናለሁ። ሐዘኑም ሆነ እፍረቱ ድርጊቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እና ወቅታዊ ዳራ ውስጥ ከሚኖረው ትርጉም የሚመነጭ ነው። ብርቱካንን ማሰር ለኢህአዴግ የሚያስገኝለት ፖለቲካዊ ጥቅም ከደረሰበት ፖለቲካዊ ኪሳራ ጋራ ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ ነው። በግሌ ብርቱካን ባትታሰር ኖሮ በ2002 ምርጫ ላይ ሊኖር ይችል የነበረው ለውጥ ኢሕአዴግን ሊያርበተብተው ከሚችልበት ደረጃ ስለመድረሱ እጠራጠራለሁ። በአንጻሩ ግን ብርቱካንን በማሰሩ ኢሕአዴግ ከራሱ አባላት ጭምር ተቃውሞ እንደሚነሳበት ያልሰሙት ብርቱካንን ለወራት ለብቻዋ እንድትታሰር፣ ሰው እንዳይጠይቃት የወሰኑት “ፍጥረታት” ብቻ ናቸው።
ከአገራችን ባህል አንጻርም ቢታይ ብርቱካንን ማሰር የፈሪ እና የጨካኝ ሰው ተግባር ነው። በቀድሞው እስራት የተለየቻትን ሕጻን ልጇን እና የምትረዳቸውን እናቷን እንኳን የሚያስብ ማንኛውም ሰው ፍትሕ የመስጠት ሸክሙን የሚጥለው በኢሕአዴግ/መለስ ላይ እንጂ በብርቱካን ላይ አይደለም። አንድ ሰሞን ብርቱካን መታሰሯ ሕጋዊ እና ተገቢ መሆኑን ለማስረዳት በየመስሪያ ቤቱ ጭምር ሰበካ ተጀምሮ ነበር። ሕዝብ ጉም ጉም ስላበዛ ዝም ለማሰኘት ነበር። የሕዝቡ ጥያቄ የተነሳው የአንቀጹን ቁጥር ባለማወቁ ይመስል ውይይቱ የጥናት ክበብ መስሎ ነበር።
ብርቱካን የታሰረችበት ወቅትም ቢሆን ክርክሩን ሁሉ ያለጥርጥር ለእርሷ የሚያጋድል ያደርገዋል። ሲጀመር ብርቱካን አልዋሸችም፤ ስለዚህ የምታስተባብለው ነገር የለም። ንግግሩ ውሸት ነበር ከተባለም “የዋሸችው” ብርቱካን ብቻ አልነበረችም። በወቅቱ የአገሪቱ ፖለቲካ ከምርጫ 97 ሕመሙ ገና ማገገም እንኳን አልጀመረም። ለዚህ ሒደት በጎ አስተዋጽኦ ለማድረግ ከሚችሉት አንዷን ለዚያውም ብቸኛዋን ሴት ነጥሎ ማሰር ስሙ ምን ይባለል? አመክንዮ ኢሕአድግኛ። መቼም ብርቱካንን ከታሰረች በኋላ እንዳትጎበኝ፣ ጠበቃዋን እንዳታናግር ወዘተ ስላደረገው ሕግ እና የሕግ የበላይነት መነጋገሩ ድካም ነው። ኢሕአዴግን እንደጎዳው ግን እውነት ነው።
የብርቱካንን መታሰር የሚቃወሙ ሰዎች ሌላው ቀርቶ በበሽተኛው የኢትዮጵያ የኢንተርኔት መረብ እንኳን ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። የኢትዮጵያውያንን የፌስቡክን ገጾች የብርቱካን ፎቶዎች ሞልተውታል። በስሟ የተከፈቱ ድረ ገጾች እና የፌስቢክ ገጾችደጋፊዎች እየበዙ ነው…
ከዚህ ሁሉ ነገር በኋላ ብርቱካን በመታሰሯ ኢትዮጵያ እና ፖለቲካችን ምን እንደሚያተርፉ፣ ኢህአዴግ ምን እንደሚጠቀም የሚያውቁት አንድዬ ናቸው፤ ለልማዱ “አቡዬ ናቸው ወይም ሥላሴዎች ናቸው” ነበር የሚባለው። “እኛም አለን ሙዚቃ፣ ስሜት የሚያነቃ” መሆኑ ነው።
በመጨረሻ የማነሳው አቶ መለስ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲው ንግግራቸው ወቅት ስለብርቱካን ዳግም መለቀቅ ያቀረቡትን “የመፍትሔ አቅጣጫ” ነው። በአጭሩ አቶ መለስ ብርቱካን “ድጋሚ ይቅርታ ትጠይቅና እንለቃታለን” እያሉን ነው። መለስ “ካለፈው ታሪኳ አንጻር ድጋሚ ይቅርታ ብትጠይቅ አይገርመኝም፤ መንግሥትም ከልምዱ አኳያ ይቅርታ ቢያደርግላት አይደኝቀንም” ብለዋል። ትርጉም ግልጽ መሰለኝ።እንዲያውም አይጋ ፎረም ላይ እንዳነበብኩት ከሆነ እርሷ ብቻ ሳትሆን ቤተሰብም፣ ጠበቃም…ስለእርሷ ተገብቶ ይቅርታ ሊጠይቅላት እንደሚችል አንቀጽ ተጠቅሶ “አቅጣጫው” ተብራርቷል። በአጭሩ ጥሪው “እርሷ እምቢ ማለቷ ስለማይቀር እባካችሁ አንዳችሁ ይቅርታ ጠይቁላትና እንገላገል” ይመስላል። በቀዳሚው የቅንጅት አመራሮች እስር ወቅት ፕሮፌሰር መንስፍ ወልደ ማርያም “ለኢሕአዴግ የማርያም መንገድ እንስጠው” በማለት ታሳሪዎቹ እንዲፈርሙ ሐሳብ አቅርበው ነበር ይባላል። ይህም ሌላ “የማርያም መንገድ” ጥያቄ ይሆን?
ሞራል በፖለቲካ ውስጥ ያለውን ቦታ ባስታወስኩ ቁጥር የዛሬዎቹ ይቅርታ ጠያቂ እና ሰጪዎች ልዩነት አብሮ ይመጣብኛል። ብርቱካ እና መለስ የሁለት ትውልድ ብቻ ሳይሆን የሁለት ዓለምም ሰዎች ናቸው (“መለስ” ስል አቶ መለስን ብቻ ማለቴ አይደለም፤ “ብርቱካን” ስል የእርሷን ሐሳብ የሚጋሩ በተለይም የትውልድ አቻዎቿን ማለቴ እንደሆነ ሁሉ)። በዚህ ጉዳይ ላይ በሌላ ጽሑፍ እመለስበት ይሆናል፤ መለስ፣ ብርቱካንን እና ቴዲን ሊረዷቸው ያልቻሉበትን ምክንያት ፍለጋ። ለመሆኑ አሁን ይቅርታ ጠያቂው ማነው? ይቅርታ ሰጪውስ? ብርቱካን የእነአቶ መለስን ይቅርታ ትፈልጋለች ወይስ እነአቶ መለስ የእርሷ ይቅርታ ይገባቸዋል? ዓለም ይህን አትፈቅድ ይሆናል እንጂ ለነገሩስ በአደባባይ ብርቱካንንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቅ የነበረባቸው አሳሪዎቿ ነበሩ። “ለፕሮቶኮል” ሲባል ይህ ቢቀር እንኳን በአደባባይ ወጥቶ “ይቅርታ ትጠይቀን” እያሉ አለመመጻደቅ እንዴት ጨዋነት ነበር?
እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሁሉ ብርቱካን ተፈታ ማየትን እናፈቃለሁ። የምትፈታበትን ሒደት ከአቶ መለስም ሆነ ከደጋፊዎቿ በበለጠ ሁኔታ የምትወስነው እርሷው ራሷ ብቻ እንደሆነች እረዳለሁ። በማንኛውም እርሷ በምትፈቅደው ምክንያትና መንገድ ብትፈታ እወዳለሁ። የምትፈታበት መንገድ እርሷ በወከለችው ዝምተኛ አብዮት ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ምን ሊሆን እንደሚቸልም ለማየት እጓጓለሁ።
ከዚህ በተረፈ ግን ይቅርታ መጠይቅም ሆነ ይቅርታ መስጠት በሁሉም የአገራችን ባህሎች የተከበረ አስተሳሰብ እና የአኗኗር ዘይቤ በመሆኑ መሠረታዊ ባህርይው የፖለቲከኞች መቀለጃ እንዳይሆን መከላከል ያለብን ይመስለኛል። ይቅርታ በሕግም ሆነ በፍልስፍና ዘርፍ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ረቂቅ እሴት ነው። በሕግ፣ በትምህርት፣ በቅጣት፣ በሽልማት ወዘተ ታግዞ እንኳን ቢሆን ፍጽም መሆን የማይችለውን የሰው ግላዊና ማኅበራዊ ሕይወት ከፍጹም ክስረት፣ ከማያባራ መፈራረስ የሚታደገው አንዱ መሣሪያ ይቅርታ ነው። አሁን እንደሚባለው ግን ይቅርታ ተራ የጠላት ማዋረጃ መሣሪያ መሆኑ አዲስ የፖለቲካ ባህላችን እየሆነ ይመስላል። ይቅርታ ጠያቂም እየዋሸ፣ ይቅርታ ሰጪም እየዋሸ፣ ሁለቱም መዋሸታቸውን እየተዋወቁ የሚደረግ ይቅርታ በአረም ያስመልሳል፤ ሁለቱም በይቅርታው አይማሩና። አልተማሩምና።
በነገራችን ላይ
(“በነገራችን ላይ’ ራሷ ሌላ በነገራችን ላይ ሳይስፈልጋት አልቀረም። አንዳንድ አንባቢዎች “በነገራችን ላይ” የዋናው ጽሑፍ አካል እየመሰላቸው ሁለቱ ክፍሎች የተዘበራረቁ ሐሳቦች የቀረቡባቸው እንደመሰላቸው መረዳት ችያለሁ። “በነገራችን ላይ” ተብሎ የሚቀጠለው ጉዳይ ከፍ ሲል ከተወሳው ጉዳይ የተለየ መሆኑን በድጋሚ ላስታውስ። ፈረንጆቹ “ፖስት ስክሪፕት” እንደሚሉት መሆኑ ነው፤ በኋላ የተጨመረ፤ ከቀዳሚው ጋራ የግድ ተፈጥሯዊ ግንኙነት የሌለው፤ ነገር ግን ሊጠቀስ የሚገባው።)
በአዲሱ ዓመት የመንግሥት ሹመኞች ሀብትና ንብረታቸውን ማስመዝገብ እንደሚጀምሩ ከወዲሁ ቃል እየተገባ ነው። የጸረ ሙስና ኮሚሽን በየቀኑ በኢቲቪ “አደራ ተባበሩኝ” እያለ ተማጽኖውን ከወዲሁ ጀምሯል። እኔን የናፈቀኝ ግን ሁለት ነገር ነው። አንደኛ፤ ምዝገባው የሚጀምረው ከየት ነው፤ ከላይ ነው ከታች? መቼም ድሮ ድሮ ሁሏም ነገር በስራ አስፈጻሚና በማእከላዊ ኮሚቴ ተወስና ነበር “ወደ ታች” የሚትወርደው። አሁንስ? ከታች ይጀመር ከተባለ ተራው እላይ እስኪደርስ የአመራር ለውጡ እንዲዘገይ በሰላማዊ ሰልፍ እንጠይቃለን። ሁለተኛ፤ በቡድን ደረጃ ሀብታም አመራሮች ያሉት የኢህአዴግ ፓርቲ የትኛው ይሆን? ህወሓት ወይስ ኦሕዴድ? ታዳጊውስ? ወደ ኋላ የቀረውስ? በውጤት ተኮር ተሸላሚው ባለስልጣን ማን ይሆን? ከአጋር ፓርቲዎችስ ማን ይመራል? ስም የማዛወር ስራው ተጧጡፏል የሚባለው እውነት ነው እንዴ?
የሕጉን ቅጂ ስላላገኘሁት ዝርዝሩን አላነበብኩትም። ነገር ግን የንብረት ምዝገባው ተቃዋሚዎችንም ቢያንስ ከፍተኛ አመራሮቹን ማካተት ይኖርበታል። የንብረት ምዝገባ ጽንሰ ሐሳቡ የመንግሥት ገንዘብ እንዳይመዘበር ቢሆንም በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጥ የሚዘረፈው ገንዘብ የሕዝብ ነው። ምናልባት እነርሱ በኦዲት ሪፖርት ምርጫ ቦርድ ይቆጣጠራቸዋል ይባል ይሆናል፤ ግር እርሱ መንገድ አይሰራም። ስንት ገንዘብ ተበላ? ተዋዋሚ ፓርቲዎችን ከቡችላ ተስፈኛ መዝባሪዎች ለማጽዳት ንብረት ቢያስመዘግቡ ምንኛ ድንቅ ነበር። እስቲ ለማንኛውም ከመንግሥት ተሿሚዎች እንደጀምርና በሒደት እንደርስበታለን። የምዝገባው ውጤት መቼ ይፋ እንሚደረግ ይታወቃል?