ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ተጨማሪ የመንግስት ሰራተኞችን በግፍ ለማባረር በስንድት ላይ ነው

የወያኔ አገዛዝ ቢ.ፒ.አር. (ወይም ቢዝነስ ፕሮሰስ ሪኢንጂነሪንግ) የተባለውን እና በሌላ አገራት የስራ ብቃትን ለማሻሻል ጥቅም ላይ የሚውለውን ሂደት ተጠቅሞ የፖለቲካ ድጋፍ የማይሰጡትን የመንግስት ሰራተኞች በግፍ ማባረሩ ይታወሳል።

የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ያስተላለፈው ዘገባ እንደሚያሳየው፥ አሁን ደግሞ “ባላንስድ ስኮር ካርድ” (ወይም ቢ.ኤስ.ሲ.) የተባለውን ሂደት በስራ ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ ይገኛል። ቢ.ኤስ.ሲ. በሌሎች አገሮች የሰራተኞችን የስራ አፈፃጸም ለመከታተል እና ያስገኙትን ውጤት ለመመርመር በጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፤ ዋና አላማው የሚሰራው ስራ ከተቋሙ ራእይ እና ስትራቴጂ ጋር የሚሄድ መሆኑን ማረጋገጥ እና አሰራርንም ማሻሻል ነው።

ይሁን እንጂ የወያኔ አገዛዝ ይህንን አሰራር በስራ ላይ ለማዋል መነሳቱ ጉዳዩን በሚከታተሉ የመንግስት ሰራተኞች ዘንድ ስጋትን መፍጠሩን ዘጋቢያችን የላከው መረጃ አሳይቷል። አዲሱን አሰራር በሚመለከት ስልጠና የተሰጣቸው የመንግስት ሰራተኞች ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት፥ የወያኔ አገዛዝ ይህንን ሂደት ከፖለቲካ ጥቅም ውጪ ለእውነተኛ መሻሻል የማዋል አላማ እንደሌለው ተናግረዋል። እነዚሁ ምንጮች፥ አገዛዙ በቢ.ፒ.አር. አማካኝነት አይደግፉኝም ብሎ የፈረጃቸውን በርካታ ሰራተኞች በግፍ እንዳባረረው ሁሉ፤ ቢ.ኤስ.ሲ.ንም ተጠቅሞ ከአገዛዙ ፖለቲካ ጋር የማይሰለፉትን ከስራ ለማገድ እየተሰናዳ ነው ብለዋል።