ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ ለተማሪዎች ክፉ ከሆኑ ሃገሮች ተርታ መመደቧ ‘የወያኔን የትምህርት ፖሊሲ ውድቀት’ አመላክቷል
“አለማቀፍ ዘመቻ ለትምህርት” የተባለው የተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ቅንጅት በዚህ ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ላይ ኢትዮጵያን በአለማችን ለተማሪዎች እጅጉን ክፉ ናቸው ካላቸው አገሮች ተርታ መድቧታል።
ደሃ አገሮች ‘በትምህርት ቀውስ ጫፍ ላይ ይገኛሉ’ ያለው ሪፖርት፤ በከፍተኛ ችግር ውስጥ አሉ ካላቸው አምስት አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እና ከሃይቲ ጎን ተቀምጣለች። ሪፖርቱ የመሰረተ ትምህርት ሽፋንን፣ የአስተማሪ ለተማሪ ሬሾን እና ለሴቶች የሚደርሰውን የትምህርት አቅርቦት እንደ መስፈርት መጠቀሙ ተገልጿል። በዚህም አኳኋን ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ውጤት ካገኙት አምስት አገሮች ውስጥ አንዷ ሆናለች።
ጉዳዩን በሚመለከት አስተያየት የጠየቅናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፥ ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ልክ እንደሌሎች ጉዳዮች ሁሉ የትምህርትን ጉዳይ የሚመለከተው ከፕሮፓጋንዳ ጥቅም አኳያ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። አገዛዙ በትምህርት ስም ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ከውጭ አገራት መሰብሰብ መቻሉ ደግሞ እንደተጨማሪ ቦነስ ነው ብለዋል። እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ገለፃ፥ ይህ አዲስ ሪፖርት የወያኔን የምህርት ፖሊሲ ውድቀት አመላካች ነው።
በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ምሁራን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስደተኞች በመሆን አገሪቱን ጥለው እንደሚሄዱ ይታወቃል። ይህም በአገሪቱ ውስጥ ላለው የመምህራን እጥረት አንዱና ዋናው መንስኤ እንደሆነ ብዙዎች ግምታቸውን ይገልጻሉ።