የቀድሞ የወያኔ ባለስልጣናት በጦር መሳሪያ ደላላነት ስራ መክበራቸው ተዘገበ
የቀድሞ የወያኔ ባለስልጣናት በአፍሪካ አገራት የጦር መሳሪያ ደላላነት ስራ እየሰሩ መክበራቸውን ለዲፕሎማቶች ቅርበት ያላቸው የውስጥ ምንጮቻችን ገለጹ።
አቶ የማነ ኪዳኔ (ወይም በጫካ የቅጽል ስማቸው “ጀማይካ”)፣ በደቡብ ሱዳን ውስጥ በከፍተኛ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ድለላ ስራ ተጠምዶ እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ ገልጿል። አቶ የማነ ኪዳኔ ከወያኔ የትግል ዘመን ጀምሮ ከገዢው ቡድን ጋር የነበረ ሲሆን፣ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ወቅት የአገዛዙ አፈቀላጤ እንደነበረም ይታወሳል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የነበረውን ስልጣን በገዛ ፈቃዱ እንደለቀቀ የሚነገርለት አቶ የማነ፤ ኢትዮጵያን ጥሎ መኖሪያውን እንግሊዝ ቢያደርግም ከወያኔ አገዛዝ ጋር ያለው ትስስር ግን ስለመቋረጡ መረጃ የለም። ወያኔ በትግሉ ወቅት በትግራይ ህዝብ ስም የሰበሰበውን እርዳታ እንደዘረፈ ያጋለጡት አቶ ገብረመድህን አርአያ ከበርካታ ወራት በፊት ባወጡት ጽሁፍ፤ አቶ የማነ ኪዳኔ ለእርዳታ የመጣን እህል ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት አሻግረው በመሸጥ ይሳተፉ ከነበሩት የወያኔ ታጋዮች ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የውስጥ መረጃ ምንጮቻችን ዘገባ እንደሚያሳየው ከአቶ የማነ በተጨማሪ የህወሃት መከፋፈልን ተከትሎ ከድርጅቱ የተባረረ አንድ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል፤ እንዲሁም በርካታ የቀድሞ የወያኔ ሹሞች በዚህ የድለላ ስራ የሚሳተፉ መሆኑ ታውቋል። የደቡብ ሱዳን ጊዜያዊ መንግስት በድምር ከ76 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚያወጡ 10 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችን ከሩሲያ ለመግዛት ባደረገው ድርድር ውስጥ እጃቸው እንዳለበት እና ለዚህም ውለታቸው ከፍተኛ ጉርሻ መቀበላቸውን ዘገባው ገልጿል። ግለሰቦቹ በዚህ ስራቸው ሃብታም ከሆኑ የዘመኑ አለማቀፍ አየር ባየር ነጋዴዎች ተርታ ለመመደብ መብቃታቸውን የደረሰን መረጃ ገልጿል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም፥ እነዚሁ የወያኔ የቀድሞ ባለስልጣናት ደቡብ ሱዳን በሚቀጥለው አመት በምታደርገው ውሳኔ-ህዝብ ዜጎቿ ነፃነትን ካወጁ፤ በነፃ መንግስትነት መቀጠል በምትችልበት መንገድ ላይ ስልጠና ለመስጠት ከምእራባውያን አገራት በሚሰጣቸው ከፍተኛ ወርሃዊ ደሞዝ እየሰሩ እንደሆነ ምንጮቻችን ዘግበዋል።