የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና አንዳንድ አካላት

የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ አንድ ዓመቱንጨርሷል፡፡ ኢትዮጵያ እንደተጠበቀው በዓመት ከ11 እስከ 15 በመቶ የማደግ ሕልሟን አሳካች ወይስ ችግር አለ? በቅርቡየምንሰማው ይሆናል፡፡ በርግጥ ‹‹ከዕቅዱ በታች ፈፅሞ የማያውቀው መንግስታችን›› ዘንድሮም የሁለት ዲጂት እንደሚያስመዘግብመጠራጠር ከአሸባሪነት ያልተናነሰ ሃጢያት ነው የሚሆነው፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና UNECA
ስለትራንስፎርሜሽኑ የመጀመሪያ የስኬት ዓመት ከሰሞኑ የኢትዮጵያቴሌቪዥን ቀብድ ቢጤ መስጠት ጀማምሯል፡፡ ሰሞኑን የምዕራባውያን ኢኮኖሚ እየፈረሰ ለቻይናዎች እጁን መስጠቱን የሚያትት ወሬካወሩልን በኋላ እንደ UNECA የአገሪቱ ዳይሬክተር ከሆነ ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት 10 በመቶ ታድጋለች፡፡ የUNECA ባለስልጣንእንዲህ ለማለት ከደፈሩ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንማ ኢትዮጵያን በሦስት ዲጂትም ሊያሳድጋት ይችላል የሚል ሐሳብ ያዘኝና ተውኩት፤ምክንያቱም UNECA የሚጠቀምበት መረጃ ለካስ ከኢትዮጵያ መንግስት የተገኘ ነው፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና መለስ ዜናዊ

ብዙ የተወራለት የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና መለስ ዜናዊዝምድና ይኖራቸው ይሆን ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ፡፡ እኔን ግን እያደር ዝምድናቸው እየገባኝ ነው፡፡ መለስ በፓርቲያቸውውስጥ ከሙገሳ በላይ ይመለካሉ ማለት ይቀላል፡፡ ገጣሚው ቴዎድሮስ ፀጋዬ ካላወቁበት ‹‹ዝና ዘነዘና ነው ራስን የሚገሉበት››እንዳለው እርሳቸውም ልዕለ-ሰብ እንደሆኑ ይታሰባቸው ጀምሯል መሰለኝ፡፡ ‹‹ያልተማከለው ብሔራዊ አስተዳደር›› ወደእርሳቸውየተማከለው በዚሁ ሳቢያ ነው – ከሳቸው ወዲያ ማን አዋቂ አለ እና የአመራሩ ስራ ወደ ሌሎች ይሄዳል? ወዳጆቻቸውም ቢሆን ሹመቱስለሚያጓጓቸው ይመስለኛል ድክመታቸውንና ለ20 ዓመታት ሞክረው ያልተሳኩላቸውን አይነግሯቸውም፡፡ ስለዚህ አይፈረድባቸውም፡፡
እናም ጠቅላይ ሚነስቴሩ (እርግጥ ባይሆንም፤ እንደ‹‹አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በሚዲያ ሳልሰማ›› ቀርቼ ሳይሆን፣ ስላላመንኩበት) በአምስት ዓመቱ መጨረሻ ከስልጣን ይወርዳሉ ስለተባለ፤አገሪቷ በሁለት እግሯ ሳትቆም መውረድ ከ‹‹አዋቂ›› የሚጠበቅ ስላልሆነ ደፋር እርምጃ ወሰዱ፡፡ ይኸውም በ19 ዓመታትያልተሳካላቸውን አገሪቷን ወደመካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ በአምስት ዓመት ማሸጋገር፡፡ በአንድ በኩል የእሳቸውን ችሎታ በመጠራጠርስንተቻቸው የከረምነውን አፋችንን ለማስያዝ በሌላ በኩል ደግሞ ከመንበረ ስልጣናቸው ሲወርዱ ሃገሪቱ በትክክለኛው ትራክ ላይከተቀመጠች ተኪዎቻቸው መሪውን ጨብጠው ለማሽከርከር ብዙም አይቸገሩም፡፡
(እኔ ግን እዚህች ጋር ትንሽ መስመር ካዋሳችሁኝየምናገረው አለኝ፡፡ እርሳቸውን የሚተካ ሰው የማግኘት ጉዳይ ለኢሕአዴግ የራስ ምታት የሆነበት ከእርሳቸው አመራር ችግር ነውባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ መሪ – መሪ እንጂ ተከታይ አያፈራምና፡፡)
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድናለጋሽ ሃገራት
ለጋሽሃገራት በተለይም ‹‹ኒዮ ሊበራሊስቶቹ›› በሚወረውሩልን ሳንቲም እና ስንዴ እጃችንን ለመጠምዘዝ ይሞክራሉ፤ ምንጭ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንናመለስ ዜናዊ፡፡ እናም ይህንን የእጅ ጥምዘዛቸውን፣ ይህንን የሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ የፍትሃዊ ምርጫ፣ የመናገር ነፃነት እያሉ የሚመፃደቁበትንእርዳታቸውን እንዳንጠብቅ ከተፈለገ፣ በዚሁ በትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ኢትዮጵያ የራሷን በጀት በራሷ እንድትሸፍን ታቅዷል፡፡ ምዕራባውያንፖለቲካዊ ጫና አያደርጉም አይባልም፣ አገሪቷ የራሷን በጀት መሸፈኗም ፅድቅ ነው፡፡ ግን ከራሳችሁ ስጋ እየቆረጣችሁ ተመገቡ ዓይነትታክስ እየሰበሰቡ ራስን መቻል አለ፡፡ ታክሱ ቅጥ አጥቷል፡፡
(አሁንምጥቂት መስመር ካዋሳችሁኝ ይሄ ራስን የመቻል ጥያቄ እውን ከኒዮ ሊበራሎች እጅ ጥምዘዛ ለመዳን ነው፤ ወይስ የኢትዮጵያውያንን እጅያለማንም አለብኝነት ለመጠምዘዝ? ቢብራራልኝ፡፡)
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና ዕድሜው
በትራንስፎርሜሽኑ የመጀመሪያ ዓመት ውስጥ የኢቴቪን ሰዓትበመቆጣጠር ከፍተኛ ሪከርድ ያስመዘገበው የሕዳሴው ግድብ አንዱ ነው፡፡ የሕዳሴው ግድብ መጀመሪያ ሲተዋወቅ አራት ዓመት ይፈጃልተብሎ የተነገረ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ተከልሶ ሰባት ዓመት ሆኗል አሉ፡፡ (ማብራሪያው የለኝም!  ምክንያቱም ኢቴቪ እንዲህ ያሉትን መርዶዎች የሚያብራራበት አሰራር የለውም፡፡)
እኔየፈራሁት ግን ለሕዳሴው ግድብ ብቻ አይደለም፡፡ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድም በአምስት ዓመት ሊደረስበት የማይችል ስለሆነወደ….. ዓመት ተሸጋግሯል እንዳይባል ነው፡፡
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድና የኢትዮጵያ ሕዝቦች
የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ከአንድ ዓመት በኋላም ቢሆንለኢትዮጵያ ሕዝብ አልተዋጠለትም፡፡ የአምናው ቁምስቅል ትራንስፎርሜሽን ወዴት የሚያስብል እንጂ የሚያኮራ ሁኖ የታየው ሰው የለም- የኢሕአዴግ አመራሮችና የኢቴቪ ጋዜጠኞች ካልሆኑ በቀር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አምሮት አጓጊ ዕቅድ (ambitious plan) መስማት አይደለም፤ አመርቂ ለውጥ ማየት ነው፡፡ (ጠቅላይሚኒስትሩ ትራንስፎርሜሽንን ስርነቀል ለውጥ ሲሉ ተርጉመውታል) በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹እኔ አውቅልሃለው›› ከሚሉመሪዎቹ የሚገላገልበትንና ለሕዝብ በሕዝብ ፈቃድ የሚሰሩ ሹመኞችን እንዲያይ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፤ ይገባዋልም፡፡
ስለዚህ ያነሳሁትን ጥያቄ ጮክ ብዬ እደግመዋለሁ፡-

       ትራንስፎርሜሽኑ ወዴት፤ ወደፊት ወይስ ወደኋላ?