አምባገነንነት እና ዘረኝነት በኢትዮጵያ
አምባገነንነት በተለያዩ ዘመናት የተለያዩ ቅርጾችን እየያዘ እስካሁን ዘልቋል። በዘመናችን ያሉ አምባገነን ሥርዓቶች እንደቀድሞዎቹ ሁሉ የህግ ሳይሆን የአንድ ሰው አሊያም የአንድ ቡድን የበላይነት የሰፈነባቸው አገዛዞች ናቸው። ሆኖም ዛሬ በድሮዎቹ አምባገነን አገዛዞች እምብዛም ያልተለመዱ አዳዲስ ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ በዛሬ ዘመን አምባገነን አገዛዞች ውስጥ:
- የውሸት ምርጫዎች ይደረጋሉ፤ ሆኖም በምርጫዎቹ አምባነኖቹን መሾምና እንደገና መምረጥ እንጂ መሻር አይቻልም፤
- ከትንሽ እስከ ትልቅ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች የሚሰጡት ጥቂት ሰዎች ቢሆኑም የተወሰነውን ነገር በጋራ የተወሰነ ለማስመሰል ጉባኤዎችና ሸንጎዎች ይሰበሰባሉ፤
- በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚደረግ አንዳችም ቁጥጥር የለም። መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሁሉ እንዲዳከሙ በማድረግ መላውን ህብረተሰብ የአምባገነኑ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች፣ የስለላ ተቋማትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲቆጣጠሩት ይደረጋል።
ኢትዮጵያዊያን ለአምባገነን አገዛዝ አዲስ አይደለንም። አዲሱ አይነት አምባገነን አገዛዝም ከላቀ መሠሪነቱ ሌላ ከድሮው የሚለየው የለም።
ዘረኝነት ግን ለኢትዮጵያችን አዲስ ክስተት ነው። እስከ ወያኔ ድረስ በነበሩት የአገዛዝ ሥርዓቶች ውስጥ ሁሉም የማኅበረሰባችን አካላት እኩል የሥርዓቱ ተጠቃሚዎች ነበሩ ማለት ባይቻልም ሆነ ተብሎ አንዱን ዘውግ /ዘር/ ከሌሎቹ ለማስበለጥ የተዘረጋ መዋቅር አልነበረም።
ወያኔ የተከለብን ሥርዓት ግን አምባገነንነት ብቻ ሳይሆን መዋቅራዊ ዘረኝነትንም አስፍኗል። ትግራይን ነፃ በማውጣት ሰበብ ተነስቶ ሌሎችን ዘውጎችን የወረረው የክፋት ሠራዊት በረሃ ከነበረት ጊዜ ጅምሮ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት ውስጥ የሚከተሉትን የዘረኝነት መሠረቶችን ተክሏል።
- ትግራይን ራሱን የቻለ የማንነት መታወቂያ አድርጎ በማስተዋወቅ ትግራዋይ ሆኖ መወለድ መታደል እንደሆነ በመስበክ “እኛ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን የተሻልን ነን” የሚል መልዕክት በድብቅም በግልጽም በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽ አድርጓል፤ እያደረገም ነው።
- በመንፈስ የረከሱ በሥራ የኮሰሱ፣ በትዕቢት የተወጠሩ፤ በዘረፋ የተካኑ እና እነሱ ያገኙትን ምቾች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር መጋራት ውርደት የሚመስላቸውን ያሰባሰበ በሥጋና በጋብቻ ዝምድና የተሳሰሩ አዲስ የትግራይ ገዥዎች ስብስብ – ኦሊጋርኪ (ፍጹም ሥልጣን ያለው የጥቂቶች ቡድን) – ፈጥሮዓል። ከቤተመንግሥት እስከ ቤተክህነት፤ ከዩኒቨርስቲ እስከ ችርቻሮ ንግድ ቁልፍ የሆነው ቦታ በሙሉ የተያዘው በዚህ ስብስብ አባላት ነው።
- ይህ የትግራይ ኦሊጋርኪ ሌሎች ማኅበረሰቦችን ለማስገበር ምስለኔዎችን በከፍተኛ ገንዘብና ሽልማት የሚገዛ በመሆኑ ጌቶቻቸውን አስደስተው ጠቀም ያለ ጉርሻ ለማግኘት ሲሉ ቤሰቦቻቸውን ከማስገደል የማይመለሱ አድርባዮችን በየአካባቢው አፍርቷዋል። እነዚህ ምስለኔዎች አንዳች ነገር የመወሰን ሥልጣን የላቸውም፤ አቅመ-ቢስነታቸውን የመገንዘብ አቅምም የላቸውም።
በዚህም ምክንያት ዛሬ ኢትዮጵያ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ዜጎች ያሏት አገር ናት። እ.ኤ.አ 1965 ወጥቶ ከ1969 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው የተባበሩት መንግሥታት የሁሉም ዓይነት የዘር-መድሎዎች ማስወገጃ ኮንቬንሽን ‹‹የዘር- መድሎን” በሚከተለው አኳኋን ይተረጉመዋል፡፡
የዘር-መድልዎ “….ዓላማው ወይም ውጤቱ ሰብዓዊ መብቶችንና መሠረታዊ ነፃነቶችን በፓለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በባህላዊ ወይም በሌላ ማናቸውም የማኅበራዊ ህይወት ዘርፍ ውስጥ በእኩል መጠቀምን የሚያጠፋ ወይም የሚያሰናከል፤ በዘር፣ በቆዳ ቀለም፣ በአስተሳሰብ፣ በትውልድ ሃረግ፣ በጎሳም ይሁን በብሄር መነሻነት የሚደረግ አድልዖ፣ ማግለል፣ መከልከል ወይም የተለየ አሰራርን መጠቀም ነው።”
በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ውስጥ “በፓለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በባህላዊ ወይም በሌላ ማናቸውም የማኅበራዊ ህይወት ዘርፍ ውስጥ በእኩል መጠቀም” የሚባለው ነገር ከሥር መሰረቱ ተናግቷል። ጥቅም ያለበትን ቦታ ሁሉ የትግራዩ ኦሊጋርኪ ተቆጣጥሮታል። ከጄነራልነት እስከ ወህኒ ቤቶች አስተዳዳሪነት፤ ከመንግሥት ስልጣን ክፍፍል እስከ ትምህርት እድል፤ ከባንክ ብድር እስከ እርዳታ እህል እደላ በሁሉም ቦታ ዘር ዋነኛው መስፈርት ሆኗል። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ጉራጌ፣ ሲዳሞ፣ አኝዋክ፣ አፋር … ወዘተ ሆኖ መገኘት ብቻውን ለጥርጣሬ በቂ ነው። በዚህ ምክንያት ከእነዚህ ወገኖች የሚወጡ ምስለኔዎች ለትግራዩ ኦሊጋርኪ ያላቸውን ታማኝነት “በተግባር የማስመስከር” ተጨማሪ ሸክም አለባቸው። ይህ “ታማኝነትን የማስመስከር” ሸክም፤ ከተወራሪዎቹ የሚወጡት ጉዳይ አስፈፃሚዎች ከወራሪዎቹ የባሱ ግፈኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ እነሱም እጅ ውስጥ አንዳችም ሥልጣን የለም። ካስፈለገ ራሳቸውን እንዲፐውዙ ወይም ራሳቸውን እንዲያገሉ ይደረጋል። የገዢዎቹ ስብስብ ብቻ ነው ተደላድሎና ተመቻችቶ የመኖር መብት ያለው። ይህ “የትግራይ ኦሊጋርኪ” ብለን የገለጽነው ስብስብ አድማሱን እያጠበበ መጥቶ ወደ አንድ ቤተዘመድ ውስጥ እየገባ፤ ራሷን ትግራይንም ጭምር እያገለላት ነው።
የወያኔ እስር ቤቶች የሥርዓቱን ገበና ዓይነተኛ ገላጭ ናቸው። በሁሉም የአገሪቷ እስር ቤቶች ውስጥ አሳሪዎችና ገራፊዎች የትግራይ ኦሊጋርኪ አባላት ሲሆኑ ታሳሪውና ተደብዳቢው ግን ሌላው ኢትዮጵያዊ ነው።
ይህ እስከ መቼ ይቀጥላል? ወደየትስ ይመራናል? ትግሉ እየመረረ ነው። የዘረኝነት አራማጆች ወደአንድ ቤተዘመድ ተጠቃለው በተቀረነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ ላይ ሲዝናኑ እያዩ መታገስ አይቻልም።
በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ውስጥ ያለን ኢትዮጵያዊያን ዘረኝነት አንገሽግሾናል። እኛ ዘረኝነትና አምባነንነት በቃን ብለናል። የዚህ አዋራጅ ሥርዓት ፍፃሜን ለማፋጠን ተግተን እየሰራን ነው። ከተናቀውና ከተገፋው ህዝባችን ጋር ሆነን የትግራዩን ኦሊጋርኪ እንደምናበረክክ ጥርጣሪ የለንም።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!