ፍኖት – የእስር ዘመቻው የፖለቲካ አቅጣጫን

ባሣለፍነው ክረምት ሰኔ ወር ጀምሮ ህዝብ የሚያውቋቸው ሰዎች ዘብጥያ መውረዳቸውን የዓለም አቀፍም ሆነ ኢትዮጵያ የዜና ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

በአዲሱ የሽብርተኝነት አዋጅ ህግ መሠረት በመጀመሪያ ዘብጥያ የተወረወሩት ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና በሀገሯ ጉዳይ ላይ ፊት ለፊት የምትፅፈው ጋዜጠኛና መምህርት ርእዮት አለሙ ሲሆኑ ቀጥሎም ጋዜጠኛ ስለሺ ሐጐስ ታስሯል፡፡ ከዚያም እነርሱን ተከትሎ ደግሞ በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አባላት መታሰራቸው ፀሐይ የሞቀው መራር እውነት ነው፡፡
የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ድርጅት አምንስቲን ኢንተርናሽናል ተወካዮች ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥተው ጉዳያቸውን ሣይጨርሱ በመጡበት እግራቸው ከተመለሱ በኋላ ሁለት ከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በተመሣሣይ መልኩ የእስር ገፈት መቅመሣቸውን ሠምተናል፡፡ እስሩም እንደቀጠለ ነው፡፡

2003 ዓ.ም ሊያበቃ ሲል በወርሃ ጳጉሜ ዝንኛው የማእከላዊ ምርመራ እስር ቤት ደንበኛውን ጋሼ ደበበ እሸቱን በእንግድነት ተቀብሎታል፡፡

“ሻፍት ኢን አፍሪካ” በተሰኘው ቆየት ያለ ፊልም ላይ ተካፍሎ የነበረው፣ የቀድሞው ቅንጅት የቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊና “የመንፈሴ ፅናት” መፅሐፍ ደራሲ የ60 አመቱ አዛውንት ደበበ እሸቱን ተከትለው ደግሞ መስከረም 3/2004 ዓ.ም ሞትን ፊት ለፊት ለመግጠም የቆረጠው ትንታጉ ብእረኛና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጨቅላ ልጁን ከትምህርት ቤት ወደ ቤቱ በማድረስ ላይ እያለ እራስ መኮንን ድልድይ አካባቢ ይጠብቁት የነበሩት ነፍጠኞች እጁ ላይ ካቴና በማጥለቅ ወደ ፈለጉት ቦታ ወስደውታል፡፡ በዚሁ ዕለት ሌላው የእስር ገፈት ቀማሽ መንፈሰ ጠንካራው ወጣት የፓርቲ መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ ነው፡፡ ያሣዝናል! መንፈስንም ይረብሻል! ሕሊናንም ያደማል! በዚህ እለት የታሰሩት የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም፡፡ በዚች ሀገር ላይ በርካታ የፖለቲካ (ህሊና) እስረኞች መኖራቸውን ከአለም አቀፍ የሠብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት መግለጫዎች በየጊዜው ማድመጥ እንግዳ ነገር መሆኑ እየቀረ ነው፡፡

ለማንኛውም የአገዛዝ ስርዓቱ የያዘው መንገድ ከእርሱ በፊት የነበሩት ሁለት የአገዛዝ ስርዓቶች ሞክረው ኢትዮጵያን እንዴት እንዳደሟት እና እነርሱም መጨረሻቸው እንዴት አሣዛኝ ሊሆን እንደቻለ በወፍ በረር እንኳን ለማስታወስ ተስኖቸዋል፡፡ ወይም ሥልጣንና ፍቅረ ንዋይ አሣብዷቸዋል፡፡ ለማንኛውም እኔ ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡

የ53ቱ መንፈቅለ መንግሥት ጥላ

የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከጨነገፈ በኋላ ለ13 አመታት አመፁ ተዳፍኖ ቆይቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ማለትም ታህሣስ 5 ቀን 1953 ዓ.ም የአዲስ አበባ ሬዲዮ ጣቢያ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በምንም አይነት መልኩ እስማዋለሁ ብሎ አስቦትና አልሞት የማያውቀውን ታሪካዊ ዜና ነበር ያስተላለፈው፡፡ ዘጋቢው ጋዜጠኛ አለም መዝገበ እጅግ ደማቅና ቆራጥ በሆነ ድምፅ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የዘውድ መንግስት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተገለበጠ መሆኑን ተናገረ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍና ጭቆናም በዝርዝር ከገለፀ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመሰረታዊ መብቱ እንዲነሳ ከወቅቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ጥሪ መተላለፉን ደጋግሞ ማስረዳቱን ከታሪክ ተምረናል፡፡ ሆኖም ግን ይህ የትግል ጥሪ ፍፃሜ አሣዛኝ ነበር፡፡

ጄኔራል መንግስቱ እና ወንድማቸው እንዲሁም ሌሎች በአደባባይ ተሰቀሉ፡፡ በነገራችን ላይ ከ1953ቱ አመፅ በፊትና በኋላ በርካታ የአፄው ተቃዋሚዎች ታስረዋል፡፡ (ተግዘዋል)፡፡ ይሁን እንጂ ተቃዋሚን ማሰር እና ማንገላታት የአፄውን እድሜ ዘላለማዊ እንዲሆን አረዳም፡፡ በአንፃሩ በእጃቸው የጎረሱ ሁሉ ተነሱባቸው፡፡

ይሄን ተከትሎ ለአያሌ አመታት በፊውዳል አገዛዝ ሥርዓት ሥር ሲማቅቅ የኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መብቱን እና ሠብአዊ ክብሩን ለማስከበር የካቲት 1966 ዓ.ም በህብረት አመፀ፤ ከዳር እስከዳርም ተንቀሣቀሰ፡፡ በጠቅላላ ወጣቱ አስተማሪውና ገበሬው ወዛደሩ የመንግስትና የግል ሠራተኞች ሁሉ ህብረታቸውን አስተባብረውና አጠናክረው በአንድ ድምፅ ለመሠረታዊ መብቶች ተነሱ፡፡ በተለይ በነፃነትና ለፍትህ ጮሁ፡፡ የዩኒቨርስቲ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎችና አስተማሪዎች እንዲሁም ጠቅላላ ሠራተኛ ሁሉ ሙሉ ኃይላቸውንና እውቀታቸውን በማስተባበር ወርቃማ የሆነውን የኢትዮጵያን ጥንታዊ ስልጣኔን አኩሪ የነፃነት ታሪክ በብዕራቸው አሣምረው በየጋዜጣዎች አደመቁት፡፡

የፖለቲካ ሂደት ተንታኞች የዚህን ሃያል የሕዝብ አብዮት የሚመራ ማን ነው ? የሚለውን ወሣኝ ጥያቄ መልስ ለማወቅ ሩጫቸው ፈጣን ነበር፡፡ ሆኖም ግን የህዝብ ፍላጎት ሣይከበር ቀረ፡፡ የኢትዮጵያን ግዛት ወሰን ለማስከበር በየበረሀው በቀን ሀሩርና በሌሊት ቁር የጦር ግዳጁን ለመፈፀም ቃል ኪዳን ከገባው ጦር የተውጣጡ 120 ወታደሮች “ደርግ” በሚል ስያሜ የስልጣን አክሊል ደፋና ስልጣኑን ጨበጡ፡፡

ደርጎቹ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት እውን መሆን፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለነፃ ፕሬስ መሠረት መጣል ሁኔታዎች መመቻቸት መሥራት ሲገባቸው የተቃራኒውን መንገድ መረጡ፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በደም አበላ እንድትታጠብ ግድ ሆነ፡፡ በሀገሪቱ ወታደራዊ ካምፓች ሣይቀሩ የእስረኞች ማጎሪያ ሆኑ፡፡ እዚህ ላይ የመፃፍ መብት እስከ 1967 ዓ.ም መጀመሪያ ድረስ እንደነበር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአንድ የኢትዮጵያ ልጆች እኔ መኢሶን፣ ኢህአፓ ወዝ ሊግ፣ ማሌሬድ ኢጭአት በሠሜን በኩል ያሉት ደግሞ ኢዲዩ፣ ወያኔ፣ ሻቢያ በሚባሉ ድርጅቶች ውስጥ ታቅፈው እርስ በርስ ተፋጁ፡፡ የብሔራዊ አንድነት ፓርቲ መስርተው መተባበር ሲገባቸው በራሳቸው መንገድ ተጓዙ፡፡ ደርጎች ይሄንን ቀዳዳ ተጠቅመው የኢትዮጵያን ወጣቶች ረሸኑ! ቀሪውንም ሰብስበው አሰሩ፡፡ በተለይ በኢህአፖ ስር የነበሩት ወጣቶች በአብዛኛው ሰለባ ሆኑ፡፡
እርግጥ ነው ነጭ ሽብር በሚባለው የመልስ ምት የወታደራዊው ጁንታ መንግስት ሹሞች እና ደጋፊዎች ወድቀዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ትርምስ ዋነኛ ተጠያቂው ማእከላዊውን መንግስት የተቆጣጠረው ቡድን (ደርግ ነው)፡፡ ሰዎቹ የስልጣን ጥመኞች ባይሆኑ ኑሮ ቢያንስ እርስ በርስ መጠፋፋቱ ይቀንስ ነበር ባይ ነኝ፡፡ ቁጭ ብሎ በመነጋገር እና ሆደ ሰፊ በመሆን ኢትዮጵያን ወደ እድገት ጐዳና መውሰድ ሲቻል ለዚህ ያልታደሉት ከእኔ በላይ ላሳር በማለት የእውር ድንበር ጉዛአቸውን ቀጠሉ፡፡

በተለይ 60ዎቹ ታላላቅ ሰዎች ርሸና በእግዚአብሄር ቀጥሎ በሕግ የሚተማመነውን ዜጋ አስደነገጠው፡፡ ፍርድ ያዋጣኛል የሚለውን የሰዎች እምነት ድምጥማጡን አጠፋው፡፡ ሰው የሚኖረው በሕግ ተማምኖ ሣይሆን በደርግ በጎ ፈቃድ መሆኑን ተገነዘበ፡፡ በመሆኑም የቻለ ማምለጥ ያልቻለ በጭንቀት መኖር ጀመረ፡፡ የጀገነው ደግሞ ነፍጥ ይዘው ከሚፋለሙት ኃይሎች ተቀላቀለ፡፡ በሕግ ላይ እምነት ጠፋ፡፡ የደህንነት ስሜት ተሟጠጠ፡፡ በእነኚህና በተለያዩ ምክንያቶች ስርዓቱ እየተሸረሸረ የነበረው ገና ከጠዋቱ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ “አብዮት የራሷን ልጆች መልሳ ትባላለች” እንዲሉ ታማኝ አገልጋዮችን ሣይቀር አስሯል፤ ገሏል፡፡ በጦር ሜዳ የገጠሙት ተቀናቃኞቹ ድል ሊነሱ ከቻሉበት ዋናው ምክንያት ደርግ በውሃ ቀጠነ የሠራዊቱን አንዳንድ አዛዦች (የጦሩን አባላት) በየጊዜው በማሰሩና በመረሸኑ ነበር፡፡ በሠራዊቱ ፊት ተዋርደው ማእረጋቸው የተገፈፈው ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ጋሼ እና በሸፍጥ እንዲረሸኑ የተፈረደባቸው ታሪኩ አይኔ ይጠቀሳሉ፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ አስራ ሰባት አመት ሙሉ ተቀናቃኞቹን ሲያስር እና ሲፈታ የነበረው ደርግ ዋነኛ የጦር ተፈላሚዎቹ በነበሩት ሻቢያና ወያኔ ተገርስሶ ሊወድቅ ችሏል፡፡ ደርግ የራሱ የሆነ ችግር ቢኖርበትም በአገር ፍቅርና በሉዓላዊነት ድርድር አልነበረውም፡፡ ለሁለት ዓመት የነበረውን የቀይ ሽብር ዘመቻ እንዳለ ሆኖ በቀሩት ዓመታት ለህዝብ የተሻለ ክብር ነበረው፡፡

የደርግ ውድቀት ኢትዮጵያ ለብዙ ሺህ አመታት ስትጠቀምበት የነበረውን የባህር በሯን አሣጥቷታል፡፡ ይሄ ከባድ ችግር ይመስለኛል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን ያለው ትውልድ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡ እንደ ዶክተር ያቆብ ሀ/ማርያም የጥናት መፅሐፍ ከሆነ ይቺ ደሀ ሀገራችን በቀን 3 ሚሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይ እየከሰከሰች ነው፡፡ ቀደም ባሉት አመታት ዶሮ ወጥ ሣይቀር እየተሰራ ከድሬደዋ ይጫንላት የነበረችው ሚጢጢዋ ጅቡቲ እኛን ቁልቁል ለማየት የበቃችበት አሣፋሪ እና አንገት የሚያስደፋ ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

ይህንን ሀቅ የሚክዱ ካሉ እነሱ ተዋንያኖችና የሥርዓቱ ወንጀለኞች ብቻ ናቸው፡፡ የቀድሞ ሁለት የጦር ሸሪኮች አንደኛው የአስመራን ቤተ መንግስት በመቆጣጠር አዲስ ሀገር ሲመስርት ሌላው ደግሞ የምኒልክ ቤተ መንግስትን በመረከብ ቀሪዋን ኢትዮጵያን መግዛት ጀመረ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ገዢዎቻችን ምን አዲስ ነገር አመጡልን ? ምንስ በጐ ነገር አስገኙልን? የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው በሠላማዊ እና በህጋዊ መንገድ እንዲንቀሣቀሱ ከመፍቀድ ጀምሮ ፕሬስ እንዴት ማስተናገድ ተቻለ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ አልጠፋም፤ አለማም፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው በወርሀ ግንቦት 1983 በአሜሪካዊው የፖለቲካ ሰው ኸርማን ኮኸን ቡራኬ ኦነግ የሽግግር መንግስት ከተወሰኑ ድርጅቶች ጋር በማበር ቢመሠርትም በአጭር ጊዜ ውስጥ የጠብ ክብሪት በመጫሩ አመራሮቻቸውን በቦሌ ከሸኙ በኋላ ተራ አባላቶቻቸውን ደግሞ በተለያዩ የጦር ካምፖች ውስጥ አስሯቸው እንደነበር እናስታውሣለን፡፡

በጣም አስገራሚው ነገር ግን በኢትዮጵያ ምድር እንቅስቃሴው አክትሞለታል የተባለው ድርጅት ኦነግ ዛሬ ለብዙዎቹ ለኦሮሞ ልጆች ስቃይ ሆኗል፡፡ አባል ነበሩ እየተባሉ ብዙ ሰዎች መታሰራቸውን ከዜና ምንጮች እናዳምጣለን፡፡ በእኔ በኩል የኦነግ የፖለቲካ አላማ ለኢትዮጵያ ይበጃታል ወይንም ይጐዳታል የሚል ክርክር ለማንሣት ፈልጌ እንዳልሆነ እዚህ ላይ አንባቢን ማስታወስ እሻለሁ፡፡ ሆኖም ግን አንደኛው የአገዛዝ ከበፊቶቹ አገዛዞች ስህተቶች መማር አለመቻሉን መመልከት ግን የሚቻል ይመስለኛል፡፡

እኛ ግን ለምንድን ነው ችግሮቻችን ቁጭ ብለን መፍታት ያቃተን? እርግማን ይሆን? እስከ መቼ ነው ሀገሬ ኢትዮጵያ የጉልበተኞች (ጡንቸኞች) እና የተጨቋኞች ሀገር ሆና የምትቀጥለው? አረ ጎበዝ አለም ጥሎን ሄደ፡፡ እኛ ዝንተ አለም ሰለ ዲሞክራሲ እና ሠብአዊ መብቶች ጥበቃ እውን መሆን ስንጮህ ሌላው አለም የምድርን ሚስጥር በርብሮ ጨርሶ ወደ ሰማይ ነጎደ፡፡ በእውነት እናሣዝናለን፡፡

ትላንት በቅኝ የተገዙት አፍንጫችን ስር ያሉት ኡጋንዳና ኬንያ ሣይቀሩ ብዙ ጥለውን ከሄዱ ውለው አድረዋል፡፡ በሩጫው እንኳን በዚህ ዓመቱ የድል ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ እኛ ግን ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአሣሪ እና ታሣሪ ልጆች ሆነናል፡፡ የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት በብዙዎች የሚሞካሽበትና እርሱም ቢሆን የሚመፃደቅበት ቁም ነገር ቢኖር የመድበለ ፓርቲ ስርአትና የነፃው ፕሬስ እውን መሆን እንዲችሉ በህግ ሣይቀር ማፅደቁ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱም ቢሆኑ ብልጭ ድርግም እያሉ አሁን የደረሰንበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለማንኛውም ሁለቱም ያለፉበትን ወጣ ገባ መንገድ በወፍ በረር ላስታውሣችሁ፡፡

ስርዓቱ የምእራባውያንን ውዳሴ ለማግኘት ሲል የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ቢፈቅድም ገና ከጠዋቱ ወከባና እስራት ያካሂድ ነበር፡፡ አዛውንቱ ፊት አውራሪ መኮንን ዶሪ በስርአቱ የፀጥታ ሀይሎች ወከባና እንግልት ከደረሰባቸው አንዱ እና ዋነኛው ነበሩ፡፡

በጊዮኑ የእርቅ ጉባኤ ለመካፈል ከአውሮፓ ወደ ሀገሩ የመጣውን ጋሼ አበራ የማነአብን ዛሬ የት እንዳደረሱት የሚያውቁት አሣሪዎቹ ብቻ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ቀዶ ህክምና ሐኪም በሙያቸው እናት አገራቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማገልገል ላይ እያሉ የሰዎች ሠብአዊ መብቶች በመደፈራቸው ለህዝባቸው አንድነትና ሰብአዊ መከበር በመታገል ህይወታቸውን የሰውት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሌላው የእስር ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን በሀዘን እናስታውሳቸዋለን፡፡

የተፈጥሮ ህግ ነውና የተወለደ ሁሉ ይሞታል፡፡ ሰው ግን በስራው ህያው ይሆናል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው እና ሌሎች ለሀገራቸው ቤዛ የሆኑት እንዲህ አይነት ሰዎች የነበሩ ናቸው፡፡

በአንድ ወቅት በዚች ሀገር ላይ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ (ለምን ይኼ ሆነ) እያሉ የአዞ እንባ ሲያነቡ የነበሩት ገዢዎቻችን ቅንጅትን የመሰለ መቅሰፍት አሣያቸው፡፡ እነርሱም ከግንቦት 1997 ዓ.ም የምርጫ ፌሽታ በፊት ነፃ ሚዲያውን እና በራሣቸው ቁጥጥር ስር የወደቁትን መገናኛ ብዙሀን ሣይቀር የክርክር መድረክ እንዲሆኑ ፈቀዱ፡፡ እድሉን ያገኙት ተቃዋሚዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ መፃኢ እድል እጅግ ጠቃሚ ግሩም ሀሣቦችን ለህዝብ አቀረቡ፡፡ በእውነቱ ለመናገር ከአገዛዙ ሰዎች ባሻገር ሀገርን በደንብ መምራት የሚችል ጭንቅላት በተቃዋሚው ጐራ እንደተሰባሰበ ያሣየ ትእይንት ነበር፡፡ የግንቦት 1997 የምርጫ ውድድር ግን ምን ያደርጋል ፈረሱም ሜዳው ይሄው ሲሉን የነበሩት ገዢዎቻችን የምርጫው ውጤት ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ እውነተኛ ምስላቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሣዩት፡፡ ያ በዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶች እውን መሆን ተስፋ ያደረገ፡፡ እንዲሁም ጨዋነቱን እና አዋቂነቱን ሚያዚያ 30,1997 ዓ.ም ለወዳጅም ለጠላትም አሣየ፡፡ ያ ታላቅ ህዝብ ኢትዮጵያ ሊያልፍላት ነው፡፡ በማለት በደስታ እንባ በእንባ የተራጨ ህዝብ ድምጹ ተቀማ፡፡ ውጤቱም የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ ያሣዝናል! ማሳዘን ብቻ አይደለም ልብ ያቆስላል፡፡ ህሊናን ያደማል፤ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

ጨዋታው ፈረሠ ዳቦው (ኬኩ) ተቆረሰ እንዲሉ ያ ብዙ የተደከመበት ታላቅ ቁም ነገር ውጤቱ ከንቱ ሆኖ ቀረ፡፡ በተለይ በአገዛዙ እርምጃ የተነሣ ሁላችንም እንደምናስታውሰው አገዛዙ ከ60 በላይ የቅንጅት ፓርቲ ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ በርካታ የነፃው ፕሬስ አረበኞችን በዝነኛው የቃሊቲ እስር ቤት ለሁለት አመት ካቆያቸው በኋላ በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ውትወታ ውጪ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያልተቋረጠ ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት የተነሳ በመጨረሻ ላይ ደግሞ በሽምግልና ተለቀቁ፡፡ ሰዎቹ ከጨለማ ከወጡ በኋላ ግን የነበራቸው ህብረትና መንፈሣዊ ጥንካሬ አብሯቸው አልነበረም፡፡ በአጭሩ አንድ የነበሩት ብዙ ቦታ ተከፋፈሉና ተዳከሙ፡፡ እዚህ ላይ መኢአድ አሁን የሚገኝበትን አሳዛኝ ገፅታ ማስተዋል ተገቢ ነው ባይ ነኝ፡፡

አገዛዙም የልቡ ደርሷልና፡፡ ከበሮውን መደለቅና መዝፈንም አማረው፡፡ ሆኖም ግን ደስታው በእውነት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ተገኘ የተባለው ውጤት አሁን አሁን የእንቧይ ካብነቱን እያሣየን ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትን የቅንጅት ፓርቲ ደጋፊ የነበሩትን ሰዎች በተለያዩ ማጎሪያዎች ማሰሩን እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ አገዛዙ ብዙ ሺዎችን ቢያስርም የሰውን መንፈስ ማሰር ባለመቻሉ ዛሬም ቢሆን የሰላማዊ ትግሉ ሞቶ የተቀበረ አይመስለኝም፡፡

የአገዛዝ ስርዓት ምን ጊዜም ቢሆን ካለፈው ስህተቱ ወይንም ካለፉት መሰል ስርዓቶች ለመማር ተፈጥሮው አይፈቅድለትምና ዛሬም በተሣሣተ ጐዳና ላይ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡

ይቅንጅትን አካል ከፋፍዬዋለሁ በማለት ሲኩራራ የነበረው ስርዓት (በነገራችን ላይ ለቅንጅት መፈረካከስ ዋነኛው ተጠያቂ መንግስት ብቻ ሳይሆን በውስጡ የበቀሉ የስልጣን ጥመኞችም ጭምር እንደሆኑ መታወቅ ይኖርበታል) የሰውን መንፈስ ማሸነፍ ስለማይሆንለት ዛሬም ቢሆን በሠላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ለመሆን ከተዘጋጁ ሰዎች ጋር ፊት ለፊት መግጠም ግድ ሆኖበታል፡፡

ከግንቦት 1997 ዓ.ም ወዲህ ቦግ እልም እያለ የመጣው የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን የማሣደድ ዘመቻው ካለፈው ሰኔ 2003ዓ.ም ወዲህ አገርሽቶበት ጋዜጠኞች እና ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችን “አሸባሪ” የሚል ታፔላ በመለጠፍ ሰለባ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሄ ድርጊት የኢትዮጵያን ፖለቲካ አቅጣጫ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይዶለው ብዙዎችን አስግቷል፡፡

የነፃው ፕሬስ ከተወለደ ወዲህ አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች በደረሰባቸው መንገላታትና እስር ምክንያት ወይ ሀገሪቱን ጥለውላቸው ሄደዋል አሊያም ብእርቸውን አስቀምጠው በአርምሞ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዛሬ በብእሩ ታአምር ሲሰራ የነበረው ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ የጦቢያው ፖለቲካ ተንታኝ ሀሰን አብደላ፣ ጋሼ ክፍሌ ሙላት፣ ከፍያለው ማሞ፣ አንተነህ መርእድ፣ ሲሳይ አጌና ወዘተ…. የሚወዷትን ሀገራቸውን ጥለው ሲሰደዱ አንጋፋው ጋዜጠኛ ጎሹ ሞገስ፣ አረጋ ወ/ቂርቆስ፣ ታዬ በላቸው ትእግስት አብርሀም ወዘተ ብእራቸውን አስቀምጠዋል ወይንም በሌላ ሥራ ተሠማርተዋል፡፡ ልበ ሙሉው እስክንድር ግን ከጋዜጠኝነት ህይወት ውጭ ሌላ ሕይወት የለኝም በማለት አሁን ድረስ ሀሣቡን በአደባባይ በመግለጡ ለጨለማ ሕይወትና ብዕር የጨበጠባቸው እጆቹ ለካቴና ተዳርገዋል፡፡ እዚህ ላይ እስክንድር የታሰረበት ምክንያት ትክክለኛ ነው አይደለም በማለት አሣሪውን ክፍል ለመሞገት ብእሬን ያነሣሁ አለመሆኔን አንባቢ እንዲረዳልኝ፡፡ የአንድን ሀገር ፖለቲካዊ ችግር ለመፍታት የፖሊስ እስር ችግር ለመፍታት የፖሊስ እስር መፍትሄ መሆን እንደማይችል ግን መጠቆም እሻለሁ፡፡ የሚያቀርቡባቸውን ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን (አባላትን) በሰበብ አስባቡ ወደ ወህኒ አምባ ማስገባት እንደማያዋጣቸው ቀድመው ቢረዱት መልካም ይመስለኛል፡፡

እንደ መደምደሚያ

በፅሁፌ ውስጥ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በዚች ሀገር ላይ መድበለ ፓርቲ ስርዓት እውን እንዲሆን ገዢዎቻችን መፍቀዳቸው በጎ ተግባር ሆኖ ሣለ አንገታቸውን ቀና አድርገው ተግባራቸውን እንዳያከናውኑ ጋሬጣዎችን ማብዛት አሣዛኙ ገፅታ ነው፡፡ አባቶች ስጋ አቅርቦ ቢለዋ መንሳት ነው የሚሉት?

በእውነቱ ለመናገር አሁን እንደ ትሮይ ፈረስ የሚጋልቡንን ካለፉት ገዢዎች ጋር ማነፃፀሩ እድለኞች ይመስሉኛል፡፡ ምክንያቱም እራሳቸውን ለማሻሻል (ፖሊሲያቸውን ለመከለስ) ብዙ አጋጣሚዎችን ያገኙ በመሆኑ ነው፡፡

ታላላቅ ሊቃውንት ምርጥ የፖለቲካ ሀያሲና ተንታኞች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች (በተለይ በሀገር ቤት የሚንቀሳቀሱት) በርካታ ምክሮችን ለግሰዋቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ በማለት እዚህ ደርሰዋል፡፡ እውን “ውሾቹ ይጮሀሉ ግመሉ ጉዞውን ይቀጥላል” የሚለው መራር ቀልድ እየተነገረን እና የፖለቲካ ሂስ ተቺዎችና መካሪዎችን እስር ቤት በመወር ወር የስልጣን እድሜን ማራዘም የሚቻል አይመስለኝም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ያለበት ችግር የዳቦ ርሀብ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አከባበር ጥማት አድሮበታል፡፡ ስለሆነም የህዝቡ ፍላጐት ቢጠና መልካም ነው ባይ ነኝ፡፡ በአንፃሩ በፖለቲካ ፓርቲ ፊት አውራሪዎችና በተቺ ጋዜጠኞች ላይ ታፔላ እየለጠፉ ዘብጥያ መወርወር ለጊዜው የጠቀመቢመስልም (የታሣሪዎችን ልብ መስበር ያስችላል ተብሎ ቢታሰብም) መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በመጀመሪያ ነገር ገዥውን ፓርቲ የዲሞከራሲ ፀር ተብሎ የሚያስተችና የሚያስወቅስ ይሆናል፡፡ በመቀጠልም በታሪክም በህሊናም፣ በእምነትም በህግም ከተጠያቂነት አያድንም፡፡ ጡንቻም እብሪትም ጊዜው ሲደርስ ይከስማል፡፡

መፍትሄው ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን፡፡ ያለችን አንድ ሀገር ናት፡፡ ሌላ የለንም፡፡ በአንድ ሀገር የሚኖሩ ሰዎች የተለያየ ፍላጐት ሊኖራቸው ይችላልና ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ መፍታት አስፈላጊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከእኛ የባቡር ሀዲድ ውጭ የሚጓዝ ሁሉ አሸባሪ ነው ብሎ የክስ ዶሴ መምዘዝ ለሰሚው ግራ ነው፡፡ “ፍርድ አያውቅ ዳኛ ተገን አያውቅ እረኛ” የሚለውን ተረትም ሊያስታውሰን ይችላል፡፡ በቦርሳው ውስጥ ወረቀትና መፅሐፍ አጭቆ ዘወትር ከቦታ ወደ ቦታ የሚንቀሳቀሰውን እስክንድር እና መሰሎቹን በዚህ አደገኛ ወንጀል መክሰስና ለፍርድ ማቅረብ በእውነቱ ቦግ እልም የሚለውን የነፃውን ፕሬስ ጨርሶ እንዳይጠፋ መንግሥት ደጋግሞ ቢያስብ ይገባዋል፡፡ የዴሞክራሲ ፋና ወጊ ማስረጃዎች “ንጉሱ ከስልጣን ከወረዱ ፀሐይ አትጠልቅም” ይባል ነበር፡፡ የነፃው ፕሬስ ዛሬ ንጉሡ የሉም፡፡ ፀሐይ ግን ትጠልቃለች፤ መልሳ ትወጣለች፡፡ ደርጎችም ቢሆኑ በራሳቸው ፕሮፓጋንዳ ናላችንን ሲያዞሩ ቆይተው የታሪክ ትቢያ ሆነው ቀርተዋል፡፡ የዛሬዎቹ ቅምጥል ገዢዎቻችን ደግሞ እኛ ከሌለን ቀሪዋ ኢትዮጵያ እንደ ዶሮ ሥጋ ትገነጣጠላለች፣ ልጆቿም እርስ በርሳቸው ይጣላሉ (ይዋጋሉ) እያሉ ዘወትር ይነግሩናል፡፡ እነሱን ከምንገምታቸው በስተቀር ይኸም አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያ እኮ አፈጣጠሯ ልዩ እና ህብረ ብሔራዊ ሀገር ናት፡፡ የዛሬዎቹም ሆኑ የትላንትናዎቹ አምባገነን ገዢዎቻችን ጠፍጥፈው አልሰሯትም፡፡ ለማንኛውም የሚያዋጣው መንገድ ሆደ ሰፊ በመሆን ወደ ብሄራዊ እርቅ መምጣት ይመስለኛል፡፡ ታሰሩ የተባሉትም ሰዎች በነፃ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው መታየት ይኖርበታል፡፡ ፍ/ቤቱ በስም ብቻ ሳይሆን በተግባር ነፃ ሊሆን ይገባል፡፡ በችሎቱ ወንበር ላይ የተሰየሙት ዳኞች ለህሊናቸው ምለው ለተቀበሉት ሞያ ለተረከቡት ችሎት ህግ ብቻ የተገዙ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ዳኝነታቸው በህዝብ እንዲታመኑ ሆነው ሊሰሩ ይገባል፡፡ ዳኝነቱን በግልጽ ችሎት ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ “የአይንህ ቀለም አላማረኝም” በማለት ዘብጥያ መወርወር ለኢትዮጵያ አይበጅም፡፡ እንደውም የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅጣጫ ከድጡ ወደ ማጡ ሊዶለው ይችላል፡፡ ለማንኛውም ቸር እንሠንብት አበቃሁ፡፡

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።
የፍኖት እትም አሥር ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ