እንረዳቸዋለን ወይስ እናርዳቸዋለን? የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቅጥፈት በየመን በግሩም ተ/ሀይማኖት
የመን መንግስት ይውረድ በሚሉ ተቃዋሚዎች ከተናወጠች ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የወያኔ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉት ቅጥፈታቸውን ለማስተጋባት ነው። አንዳንዴ በመጠኑ መዋሸትም ጥሩ ነው። ባለፈው ረቡዕ ዕለት በዶቺቬሌ ቃላቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቃል አቀባይ አቶ አምደሚካኤል አሳፈሩኝ። ኣሳፈሩን። <<ኢትዮጵያዊያኑን እንረዳቸዋለን..ከአይ ኦ ኤም ጋር በመተባበር ወደ ሀገር መመለስ የሚፈልጉትን እንመልሳለን>> ብለዋል።
የመን ያለን ኢትዮጵያዊያንን በአባባላቸው ግራመጋባት ብቻ ሳይሆን የተለያየ መላምት እንድንሰጥ አድርጎናል። አንዳንዶች <<አዎ ይረዳሉ ግን ኤምባሲ ውስጥ ላሉ ሰራተኞች ነው። ነገር ግን ከውጭ ላሉ አጨብጫቢዎቻቸው እና ወሬ አቀባዮቻቸው እንኳን ሲረዱ አናውቅም>> ሲሉ ተደምጠዋል። ሌሎች ደግሞ <<..እንረዳለን ማለት ፈልገው ሳይሆን እናርዳቸዋለን ማለታቸው ነው። ሲያርዱ እንጂ ሲረዱ መቼ ታይተው ነው?>> ሲሉ
ተደምጠዋል። በባህር ሲመጡ ተይዘው በየመን መንግስት፣ በሳኡዲአረቢያ እና በአይ ኦ ኤም ትብብር እና ወጪ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረጉትን ነው እንረዳለን ያሉት? ለዛውም ፎቶግራፍ አንስተው ወረቀት ላዘጋጁበት ክፍያ መጠየቃቸውን ትብብር ያደረጉት ሀገሮችም ሆነ ድርጅት እያወቁ ይህን ማለታቸው ያሳፈራል። በቴሌቪዥንም ሆነ ሬድዮ ከየመን በጦርነቱ ምክንያት በፍቃደኝነት የተመለሱ ሲሉ የውሸት ዜናቸውን ማቅረባቸው የመን ያለ ስደተኛን አንገት አስደፍቷል።
በኮንትራት የመጣችን ኢትዮጵያዊ የቤት ሰራተኛ <<…አሰሪዎቼ በዱላ ደበደቡኝ በሰውነቴም ላይ ጉዳት ደረሰ…>> ብላ አምልጣ ወደ ኤምባሲ መጣች። አሰሪዋ የመናዊት ሴት ኤምባሲ ስትመጣ አሳልፈው ሰጡዋት። ተበደልኩ ያለችን፣ እግርዋ ላይ አደጋ ደርሶባት ኤምባሲ አለኝ ብላ የሸሸችን ዜጋ አሳልፎ ለአረብ መስጠት እና ስትጠፈጥፍ ማየትን የመሰለ ምን እርዳታ አለ? ይህች ጉዳት የደረሰባትን ልጅ ከኤምባሲ ጊቢ ሰብለወርቅ ታደሰ የምትባል ሴት ይዛት ሾልካ ዩኒዶም ሚባል ለአፍሪካ ስደተኞች መብት እና የሴቶችን ጥቃት የሚከላከል አንድ ድርጅት ጋር አገናኘቻት። ይህ ድርጅት ኩሩቤል በሚባል ስደተኛ የተቋቋመ ነበር። በዚሁ ድርጅት ተመዝግቦ ያለ ታሪክ ነው። አሰሪዋ የፈላ ውሀ ደፍታባት ወደ ኤምባሲ ያመለጠችን ሴት <<..እኛ ለገረድ አልመጣንም >> ብለው አሰናብተዋት ወደ ኩሩቤል ጋር ዩኒዶም ሄዳ እርዳታ ማግኘቱዋን የማያውቅ ሀበሻ ይኖር ይሆን? ይሄ መርዳት ነው ማረድ? ብራቮ!!!! ኢትዮጵያ ኤምባሲ ትክክለኛ የወያኔን ምግባር እያሳያችሁን ነው።
መርዳት ማለት እንዴት ነው? ሀገር ውሰጥ ያለው ብለሹ የፖለቲካ ስርዓት ለስደት የዳረጋቸውን ምስኪኖች ገንዘብ መብላት ይሆን? የኢኮኖሚ ስደተኛ ናቸው እያላችሁ ታብጠለጥላላችሁ። የኢኮኖሚ ድቀት፣ ድሽቀት ሆነ የኢኮኖሚ ስደት የሚመጣው ከብልሹ የፖለቲካ ስርዓት መሆኑን ዘንግታችሁት ይሆን? ሽቶ የተባለች ልጅ በኮንትራት መጥታ ሁለት አመት አሰርተዋት የሁለት አመቱን መኖሪያ ፍቃድ ሳያሰሩላት፤ ሁለት ዓመት የሰራችበትን ሳይሰጡዋት፣ ፓሰፖርቷ ላይ ቀይ አሰመትተው አባረዋት ለስሞታ ኤምባሲ መጣች። << ይሄ..ይሄ በደል ደረሰብኝ ሁለት ዓመት ሰርቼ ገንዘቤን ከለከሉኝ፣ፓስፖርቴ ላይ ቀይ አስመትተው ወደ ሀገሬም አላሳፈሩኝ፣ ለእለት የማርፍበትም ሆነ የምበላው የለኝም>> ስትል የተሰጣት መልስ <<የኮሚኒቲ አባል ነሽ?መጀመሪያ ተመዝገቢና ሁለት ሺህ ከፍለሽ መታወቂያ ውሰጂ>> የሚል ነበር። ይሄ ነው መርዳት? ጣር ላይ ሲሆኑ አንቆ መግደል?
በተናጠል ያለውን ልተውና ሌላውን እንይ…
እንደ አለመታደል ሆኖ የመን ካለን ስደተኞች ስደት የወለደው ስደት ላይ ያለን በዝተናል። በስደት የመን ውስጥ ከምንኖርበት አካባቢ በጦርነት እየተፈናቀልን ነው። የምንሰራበትም ሆነ መኖርያ ቤታችንን ትተን ከተሰደድን አስራአምስት ቀናቶች ተቆጥረዋል። ቤታችንን ጥለን ከተሰደድነው ውስጥ በርካታዎቹ በፓስፖርት ያሉ ናቸው። ስራም ሆነ መጠለያ ያጣነው ሰዎች ቁጥር ትንሽ አይደለንም። ኤምባሲው ግን ያደረገላቸው እርዳታ የለም። UNHCR ቢሆን በስሩ ላለነው ከፌዝ የዘለለ አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጠን አልወደደም። ባለፈው እሁድ በ25/9/2011 አንድ ትውልደ ሀበሻ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ 8 ኢትዮጵያዊያን መሞታቸው ተነገረ አለኝ። ሬሳውን ግን ሊወስዱ አልፈቀዱም አለኝ። እውነታውን ለማጣራት ስሞክር በትክክል መሞታቸውን እና ሬሳቸውም ጀማዕተል ኢማን የሚባል /የእስልምና ሀይማኖት ቁርዓን የሚማሩበት ቦታ/ እንዳለ ሰማሁ። ለመሄድም ሞከርኩ። የኤምባሲ ወረቀት ካላሳየህ መሄድ አትችልም። ብትሄድ እና አደጋ ቢደርስብህ አይመለከተንም ተባልኩ። ጦርነቱ የሚጋሽርበት ሮኬቱ፣ መድፉ፣ መትረየሱ..የሚንዷዷበት መንግስት የተቃዋሚዎች ማዕከል ብሎ ዶጋ አመድ ያደረገው ቦታ በመሆኑ ፈራሁ። ቢሆንም ግን 8 ኢትዮጵያዊያን 3 ሶማሊያዊያን ሬሳ መኖሩ እውነት ነው።
በማግስቱ ሰኞ እለት ኪንታኪ የሚባለው ቦታ ቤት ተከራይተው በችግሩ ሰዓት ሸሽተው ቆይተው ቤታቸው መዘረፉን ሰምተው ሊያዩ ሄዱ። ዮናስ እና መኪ ይባላሉ። በመንግስት ወታደሮች ተያዙ። ቤታችን እዚህ ነው፣ መዘረፉን ሰምተን ነው አሁን ቦታው በመንግስት ይዞታ ስለሆነ ልናይ ነው ቢሉ ማን ሊሰማ? ማን እሺ ሊል? ታሰሩ። መንግስት ለደህንነት ጥበቃ ሲል ከኤምባሲ ወረቀት አምጡ ተባለ። ለዜጋው ፈጥኖ ደራሽ የሆነው ኢትዮጵያ ኤምባሲ ንብረታቸውን ተዘርፈው በእስር ላይ የሆኑትን ልጆች ለማስፈታት የሚሯሯጡትን ቅዳሜ ተመለሱ ሲል በቀጠሮ አሰናበተ። ዜጎችን መርዳት አትሉም ይሄ ነው አይደል። በነገራችን ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች 8 ኢትዮጵያዊያን ታሰረዋል። መሀመድ ኑር፣አሊ..፣አማና ቱፋ፣ቃሲም..የሚባሉት ይገኙበታል።
ቀይ መስቀል ማህበር ቤት ለቤት ባደረገው ፍተሻ ማክሰኞ እለት ብቻ 60 ሬሳ አባብጦ፣ ሸቶ እና ተበላሽቶ እንዳገኘ መግለጫ አወጣ። በየቦታው ተሸርቁጦ፣ በየህንጻ ውስጥ የተለቀመ ነው እንጂ በሆስፒታል እና የዛኑ ሰሞን የተቆጠረውን ያልጨመረ ነው ይህ አሀዝ። ከዚህ ውስጥ አንድ ሰው ቤት ሰራተኛ የነበረች ኢትዮጵያዊ ሞታ ሬሳዋ ሸቶ ተገኝታለች። ሬሳዋን ግን የሚረከብ አልተገኘም። ጦርነቱን ፍራቻ መውጣት ያልቻለ ሁሉ በየቤቱ ከቶ በርሀብ ተጠብሷል። ይህን ረሀብ መቋቋም ያቃታቸው ሁለት ልጆች ኩበዝ/ቂጣ/ ሊገዙ ወጥተው ደብዛቸው ጠፈቷል። ሁለት አፋሮችም እስካሁን የገቡበት አልታወቀም። ፋልማታ በሚል ቅጽል ስም የሚታወቅ መሀመድ እንድሪስ የተባለ ልጅ በህክምና ቢረዳም ሊድን አልቻለም።
ሞተ።
ይህ እንግዲህ በሞት ያለፉትን እና የጠፉትን ነው የሚያመላክተው። የቆሰሉትን ሁለት አውቃለሁ። መሀመድ አልዬ እና ከዲጃ አማን ..ኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን ማንኛቸውንም ሲረዳቸው አላየሁም። ሌላው ቀርቶ በኤች አይ ቪ ሰበብ ሞታ ሬሳዋን አውጥቶ ለመቅበርም ሆነ ለቤተሰብ ለመላክ ኤምባሲው ምንም ነገር ሊተባበር ባለመቻሉ ከ3 ወር በላይ ሬሳዋ ጁሜሪ የተባለ ሆስፒታል ፍሪጅ ውስጥ የቀረች ልጅ አለች።
ለሚረዱት ዜጋቸው የሚደርጉትን ትብብር መሰል ብር ተኮር እንቅስቃሴ እና ኢትዮጵያዊያኑ ያሉበትን የመኖሪያ ፍቃድ ማጣት፣ ሀገር መመለሻ ማጣት..መሰል የስቃይ ህይወት እንይ፦…..
የመን ያለ ኢትዮጵያዊ በሙሉ አገባቡ ህጋዊ አይደለም። በአየርም ሆነ በባህር የሚገባው አገባብ ህጋዊ እንዳል ሆነ ኤምባሲው ጠንቅቆ ያውቃል። በተለይ በአየር የሚያሰገቡ ህገ ወጦቹን ደላሎች ኮሚኒቲ እና ኮሜቴ እያለ ሲያሽሞነሙን ነው የሚታወቀው። ፓስፖርት ስለተያዘ ህጋዊ የተሆነ የሚመስላቸው ሴት እህቶቻችን ለደላላ ከፍለው ወደ የመን የሚገቡት በአንድ ወር የጉብኝት ቪዛ ነው። ደሞዝ ሲከለከሉ በደል ሲደርስባቸው መጠየቅ አይችሉም። እስርቤት ገቢ ናቸው። በጉብኝት ገብተው መስራት አይቻልም እና ተጎጂ ናቸው። ይህን ኤምባሲው ያውቃል። ወ/ሮ እጅጋየሁ የተባለች ሴት ሳሪስ አካባቢ ያለች የመን ካለ ወኪሏ ጋር ሁና ሴት እህቶቻቀችንን ከሚደርስባቸው በደል በተጨማሪ ለወንዶች እየሸጡ መጫወቻ ሲያደርጉዋቸው ኤምባሲው ምን እርምጃ ወሰደ? ሴትዮዋ ዘዴዋን እየቀያየረች አሁንም ስራዋን ቀጥላለች። አሽጣል የሚባለውን ኤምባሲው ከሰስኩ ቢልም አንድ ግለሰብ ሊያገኝ የሚችለውን ያህል ፍትህ ሊያገኝ ያልቻለ ሽባ እንቅስቃሴ አድርጎ ሰውየው ነጻ ሆነ።አንድ ትውልደ ሀበሻ የሚባል በኮንትራት የወሰዳት እና ሊያስቀጥራት የነበረችን ልጅ ደብድቦ፣ደፈሮ ሚስጢር እንዳታወጣ ገሎ ማን ይጠይቀው በነጻ ወጣ። ለዜጎቼ ቆሜያለሁ ያለው ኤምባሲ አልሰማም አይባል ጉዳዩን ጀምሮ ጉርሻ ይሁን ልምሻ ያሽመደምደዋል።
ለሀገሩ ዜጎች ኤምባሲው ባያስብም ኢትዮጵያዊያኑ ህጋዊ ሆነው መኖር ያለባቸው መሆኑን የየመን መንግስት አምኖበት በጣም በዝቅተኛ ሳንቲም መኖሪያ ፍቃድ እንዲያሰሩ ፈቀደ። ኤምባሲው ግን በኮሚኒቲ በኩል ተባለና እየአንዳንዱ 25.000ሪያል እንዲከፍል ተደረገ። የየመን መንግስት ስጦታውን ሰረዘ። በነጻ የተፈቀደውን ዜጋው ላይ ንግድ በማሰቡ እድሉ ታጣ። ህይም ለዜጋ ማሰብ ነው? አንድ በሉ።
የመን ያለ ኢትዮጵያዊ የመኖሪያ ፍቃዱን ለማሰራት ችግር ውስጥ በመሆኑ ለበላተኛ ተጋለጠ። ጀበሀ የተባለ የኤርትራ ተቃዋሚ የየመን መንግስትን አስፈቅዶ የኢትዮጵያዊያንን የመኖሪያ ፍቃድ ያሰራ ጀመር። በ18.000 የየመን ሪያል ለሚሰራ መኖሪያ ፍቃድ 52.000 ሲያስከፍሉ ኤምባሲው ዜጎቼ ሰው ቤት ፤ለፍተው ያገኙትን ለበላተኛ ተዳረጉ ብሎ ያደረገው እንቅስቃሴ የለም። እንዲያውም በሰበባ አስባቡ ተጨማሪ ገንዘባቸውን የሚያቆረቁዝበት መንገድ ያመቻቻል። እውነት ለሀገር ተቆርቋሪ ቢሆኑ የዜጎች ውጪ የሚቀንስበትን መንገድ ቢያመቻቹ የተረፋቸውን ወደ ሀገር ስለሚልኩ ምንዛሪም ተገኘ ማለት ነበር። ለዜጋችን እያገለገልን ነው የሚል መግለጫ ሲያወጡ አለማፈረቸው ያሳፍራል።
ይህም ሆኖ ገንዘቡም ተከፍሎ መኖሪያ ፍቃዱ ቢሰራ ጥሩ ወደ 5.000 በላይ ፓስፖርት እና ቅድመ ክፍያ እየአንዳንዱ 200 ዶላር ሰጥተው ሁለት እና ሶሰት አመት ጠብቀው ብራቸው ተበልቶ የመኖሪያ ፍቃዱም እዳ ጨምሮ ሁሉ ሰው እዳ ውስጥ ሲዘፈቅ ለዜጋቸው ያረጉት ምንድን ነው? አሁን ለአንድ ወር የሚቆይ የእዳ ቅነሳ ከየመን መንግስት ጋር ተነጋገረናል ተባለ እና ዙሪያ ጥምዝ ሀበሻውን ለእንግልት የሚዳርግ ስራ ሰሩ። ከ30 ያልበለጠ ሰው አሰራ። በ42.000 የየመን ሪያል ያልቃል ብለው አስጀምረው በ 105 ሺህ የየመን ሪያል የጨረሰ አንድ ሰው ነው። እስክ 120 ዘእና 130 ሺህ ጨርሰዋል። ሌላው ችግር እየአንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀላፊ የሚሆን የየመን ዜጋ ያቅርብ ተባለ ኤምባሲው ለዜጎቹ ሀላፊነት መውሰድ አቅቶት ማለት ነው። አንድ በሉ። መቶ ዶላር ድረስ እየከፈሉ የመኒ ፈልገው ያስፈረሙ ምን ይገጥማቸዋል? ትንሽ ቀን ቆይቶ ወይ ብር ወይ ሴትነትሽን ያለበለዚያ የመኖሪያ ፍቃድሽን አሰርዘዋለሁ ይባላል። ሌላ እዳ…ምኑ ነው ለኢትዮጵያዊያን የሰሩት?
ቢያአስረዱን ቢዝርዘሩት ጥሩ ነበር።
ቅጥፈት መሰረቱን፣ ማገሩን…ሰው ውንጀላ ማሰር መግደል ስራው ከሆን መንግስት ኤምባሲ ከዚህ የበለጠ አውሬነት ቢታይ ምን ሊደንቅ? ግን በቃ!!!! ቅጥፈቱ ይቁም ህዝቡ እንዲሁ የቆሰለው መቼ አነሰው?