የሽብርተኝነት ትርጓሜዎች ሲዛቡ
በዛሬይቱ ኢትዮጵያ “ሽብርተኛ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ተዛብቷል። በአገራችን ሰዎች “ሽብርተኝነትን” ቢያንስ በሚከተሉት ሶስት መንገዶች ይረዱታል።
- የመለስ ዜናዊ አገዛዝ “በአሸባሪነት” “ጠርጥሮ” ያሰራቸውን ዜጎችን ስብዕና ያስተዋሉ፤ “ሽብርተኛ” የጨዋነት፣ የመልካም ሥነ-ምግባርና የመልካም ዜግነት መጠሪያ አድርገው ወስደውታል። እናቶች ልጆቻቸው ሲያድጉ እንደ አቶ አንዱዓለምና አራጌ፣ እንደ አቶ እስክንድር ነጋ ወይም እንደ ወ/ት ርዕዮት ዓለሙ ስም አስጠሪ እንዲሆኑላቸው ይመኛሉ። ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ መታገል፤ ሃሳብን በነፃ መግለጽ፤ ነፃነትንና ፍትህን መስበክ …. ሽብርተኛ የሚያስብሉ ከሆነ “እኔም አሸባሪ ነኝ!” የሚሉ ድምፆች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው፤ በጽሁፍም እየቀረቡ ነው።
- “የፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል” እየተባለ የሚንቆለጳጰሰው አካል የሚያወጣቸው መግለጫዎችና የሚያሰራቸው “ዶክመንተሪ” ፊልሞችን የተከታተሉ ሰዎች “ሽብርተኛ” ማለት የቀልድ ልብ-ወለድ ገፀ-ባህሪ አድርገው ወስደውታል። በዚህም ምክንያት ደራሲዎቻቸው የማይታወቁ በርካታ “ሽብርተኛ” ቀልዶች ሰውን ያዝናናሉ።
- በሌሎች አገራት “ሽብርተኛ” የሚባሉ ሰዎችን ባህርያትንና ተግባራትን የተከታተሉ ደግሞ የአገራችን ቀንደኛ ሽብረተኞች መለስ ዜናዊ እና ጥቂት ባልደረቦቹ መሆናቸው ይረዳሉ። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ሽብርተኝነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የመለስን አገዛዝ ማስወገድ ግዴታ እንደሆነ የተገነዘቡ ናቸው።
የሽብርተኝነት ትርጉም እንዲህ ቢምታታም በመለስ ዜናዊ “ሽብርተኛ” መባልና በኢትዮጵያ ህዝብ “ሽብርተኛ” መባል ለየቅል መሆናቸውን ማስረገጥ ተገቢ ነው።
በኢትዮጵያዊያን ዓይን ሲታይ መለስ ዜናዊ እና ቡድኑ በሽብር ተጸንሰው፤ በሽብር ያደጉ እኩይ ኃይሎች ናቸው። መለስ ዜናዊ እና ቡድኑ በኢትዮጵያዊያን ደም ተረማምደው፤ ብዙ ድልድዮችን አፍርሰው እና በርካታ ባንኮችን ዘርፈው ምኒሊክ ቤተመንግሥት መድረሳቸውን እነሱም አይክዱትም። በረሃ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ የተለየ አስተያየት የያዙ፣ አሊያም ወደፊት ይቃወሙን ይሆናል ብሎ የጠረጠሯቸውን ወዳጆቻቸውን ሳይቀር ገድለዋል፤ አሰቃይተዋል። ቅልብ ገዳዮችን በማሰማራት በበደኖ፣ በአዋሳ፣ በሻሸመኔ፣ በአሰበ ተፈሪ፣ በሆሮ ጉዱሩ፣ በሀረር፣ በጋምቤላ፣ በጎንደር፣ በኦጋዴን፣ በአዲስ አበባ እና በሶማሊያ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል።
ቦንቦችን እያፈነዱ ዜጎችን ከገደሉ በኋላ በኦነግና በኦብነግ ሲያላክኩ ኖረዋል። ከአሜሪካ ኤምባሲዎች ሾልከው የወጡ የዊኪሊክስ መረጃዎች እንዳረጋገጡት መለስና ቡድኑ በድብዳባ የሞተን ሰው እንደና በፈንጂ እንዲሞት አድርገው “የሽብርተኛ” ድራማ የሰሩ አጋንንት ናቸው። እነሱ የፈፀሙት የሽብር ሥራ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም።
በመለስ ዜናዊና ተከታዮቹ ውሸቶች ሌላው ቀርቶ “የፀረ-ሽብር ግብረ-ኃይል” ተብየው ቡድን አባላትን እንኳን ሳይቀር ተንገሽግሸዋል። “ግብረ-ኃይል” ተብዬው የመለስ ዜናዊና በረከት ስምኦን ቀኝ እጅ በሆነ አንድ ዘረኛ ግለሰብ የሚዘወር መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ቀሪዎቹ አባላት በቡድኑ ስም የሚፈጸመው ሰቆቃ፤ የሚነዛው ፕሮፖጋንዳና ጉራ መልሶ እነሱኑ የሚያጠፋቸው እንደሆነ እየተረዱት ነው።
መለስና ልቦናቸው የታወሩ ወዳጆቹ የማያውቋቸው አሊያም ሊያውቋቸው የማይፈልጓቸው ሃቆች አሉ።
- ህዝብ የሚሰሩትን ያውቃል፤ በቀልድም በአሽሙርም በዜናቸው ላይ ያፌዛል፤
- የኢትዮጵያ ህዝብ መለስንና ቡድኑን ለመቅጣት አድብቷል፤
- የኃያላን መንግሥታት ተወካዮችም የተታለሉ ቢመስልም ውስጥ ውስጡን ግን እየሳቁባቸው ነው። ይህንን ማወቅ የሚፈልግ የዊኪሊክስ መረጃዎች ያንብብ።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በሽብርተኝነት ስም እየነዛ ያለውን ሽብር አጥብቆ ያወድዛል። መለስ ዜናዊ እና ቀንደኛ ተባባሪዎቹ አሸባሪዎች በመሆናቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ ይታገላል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!