በትግራይ ህዝብና በህወሃት ሥም በህዝባችን ላይ ወንጀል እየፈጸመ ያለው የመለስ ዜናዊ ቡድን በትግራይ ህዝብ በአደባበይ ተወገዘ

ባለፈው ሳምንት በመኪና አደጋ ህይወታቸውን ያጡትና በከባድ ሁኔታ የቆሰሉት የነባር ህወሀት ታጋይ አርቲስቶች ጉዳይ፤ የትግራይን ህዝብ ክፉኛ እንዳስቆጣ የቀድሞ የህወሃት አመራር አባል የነበሩ አቶ አስገደ ገብረሥላሴ መግለጻቸውን ኢሳት ዘገበ።

ታጋይ አርቲስቶቹ በሱዳን ዝግጅታቸውን ለማቅረብ  በመስቀል ዋዜማ በአሮጌ አውቶቡስ ከመቀሌ ተነስተው ጉዞ ቢጀምሩም፤በስተደቡብ 200 ያህል ኪሎ ሜትር ከተጓዙ በሁዋላ ቆቦ አካባቢ ሲደርሱ አውቶቡሱ ተገልብጡ 10 ታጋዮች ወዲያው መሞታቸውና 17ት ታጋዮች ደግሞ በከባድ ሁኔታ መቁሰላቸው ይታወቃል።

“ለዘግናኙ የመኪና አደጋ እልቂት ተጠያቂው ማነው?”በሚል ርዕስ አቶ አስገደ ባቀረቡት ዕሁፍ እንደጠቆሙት፤ የአርቲስቶቹ አደጋና ከተሰማ ጀምሮ  የመቀሌ ነዋሪ፦”ሌቦች! ስስታሞች !የሄሊኮፕተር ላለመክፈል ብለው  አስጨረሷቸው! ሌላው ቢቀር ለ 26 ሰው እኮ ሶስት ኮብራ መኪና ይበቃ ነበር። ለራሳቸውማ ቢሆን ኖሮ ለአንድ ሰው- አንድ አውሮፕላን ሲያንቀሳቅሱ እናውቃቸዋለን” በማለት ቁጣውን በስርዓቱ ሹመኞች ላይ እያሰማ ይገኛል።እንደ አቶ አስገደ ገለፃ፤ ይህ ቁጣ እየተንፀባረቀ ያለው፤ በነዋሪ፣ በነጋዴው፣ በመንግስት ሠራተኛውና በህወሀት አባላት ጭምር ነበር።

የሟቾቹ አስከሬን ምሽት ላይ ሚላኖ ሆቴል እንደደረሰ የህወሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከሆኑት አንዱ አቶ ቴወድሮስ ሀጎስ ማልቀሳቸውን የጠቀሱት አቶ አስገደ፤ አጠገባቸው የነበሩ ወጣቶችና ሴቶች ግን፦ ”አስመሳዮች! እናንተን ማን ያምናችሁዋል? ማታ ማታ ለአንድ ጠርሙስ ብሉ ሌብል ውስኪ ከ 6 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር እያፈሰሳችሁ ወንድሞቻችንን በ አሮጌ መኪና ልካችሁ አስጨረሳችሁዋቸው! አሁን የምታለቅሱት ማን ያምነናል ብላችሁ ነው?”  ሲሉ እንደነበር ጠቁመዋል።

“ከዚህም ባሻገር ወጣቶቹ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሢሳደቡ ይደመጡ ነበር” ያሉት አቶ አስገደ፤ “ወጣቶቹ ያመረሩበት ነገር ቢኖር ነው እንጂ፤እንደዚህ እየጮኹ በህወሀት ባለስልጣኖች ፊት ተሳድበው አያውቁም ነበር”ብለዋል።

እንዲሁም አስከሬኑ ከሚላኖ ሆቴል ተነስቶ አይደር ሆስፒታል ሲደርስም በስፍራው የተሰበሰበው በርካታ ህዝብ ቁጭት በተሞላበት ሀዘን ቁጣውንን ስድቡን በህወሀት ሹመኞች ላይ ሲያወርደው መሰማቱን አቶ አስገደ በፅሁፋቸው ገልጸዋል።

በተለይ የአስከሬኑ ሽኝት እንደተጠናቀቀ በወያኔ ተሹሞት የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጳጳስ አቡነ ጳውሎስ ከተናገሩ በሁዋላ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  አባይ ወልዱና የመለስ ዜናዊ የደህንነት አማካሪ ፀጋይ በርሄ ንግግር ማድረግ ሲጀምሩ  አብዛኛው ህዝብ በቁጣ ስነ ስርዓቱን አቋርጦ መመለሱንና በስፍራው የነበሩ የህወሀት አመራሮች አስኪደነግጡ ድረስ ከፍ ያለ ተቃውሞ መሰማቱን አቶ አስገደ አመልክተዋል።

ልክ ሹመኞቹ መናገር ሲጀምሩ አንዳንድ ሰዎች ጮኽ ብለው፦ ”አታጭበርብሩን! ራሳችሁ ከገዳላችሁዋቸው በሁዋላ ቀብራቸውን ወደ ፖለቲካ ማራመጃነት በመቀየር አታጭበርብሩን!” ማለታቸውን የጠቀሱት አቶ አስገደ፤ይሄ ተቃውሞ ኪዚያም፤ከዚህም ሢስተጋባ የሰሙ የህወሀት አመራሮች በሙሉ በድንጋጤ አንገታቸውን መድፋታቸውን ገልፀዋል።

እስከዛሬ ድረስ በመቀሌ ኤፍ .ኤም ራዲዮ ስርጭት፤ ተመሣሳይ የህዝብ ቁጣ እየተስተጋባ መሆኑንም አቶ አስገደ ሳይጠቁሙ አላለፉም። ታጋይ አርቲስት ኢያሱ በርሄ በተንኮል እንደተገደለ የሚያረጋግጡ መረጃዎች አፈትልከው እንደወጡ መዘገቡ ይታወሳል።

ህወሃት የትግራይን ህዝብ እያስገደለና ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ እያጋጨ የትግራይን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርገው ጥረግ ከጊዘ ወደጊዜ ከፍተኛ አጣብቅኝ ውስጥ እየገባ እንደመጣ በርካታ የትግራይ ተወላጆች ይናገራሉ።