የአሜሪካውያን በጎ አድራጎት ድርጅት ታገደ

(በብርቱካን ፈንታ፣ ሪፖርተር)

ሳመሪታን ፐርስ የተባለ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሕገወጥ መንገድ 14 አሜሪካውያን ሲሠሩበት ቆይተዋል በሚልና በሌሎች ተጨማሪ ወንጀሎች ምክንያት፣ ከመስከረም 14 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ መታገዱን የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሰፋ ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ድርጅቱ እንዲታገድ የተደረገው በዋነኛነት በሦስት ምክንያቶች ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሥራውን በጀመረበት ወቅት ማሟላት የነበረበትን መስፈርት ሳያሟላ በማጭበርበር ተመዝግቧል፡፡ በዳግም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ምዝገባ ወቅትም የውጭ ድርጅት በመሆን በድጋሚ በማጭበርበር ተመዝግቧል፡፡

ኤጀንሲው በተከታታይ ባደረገው ማጣራት 14 አሜሪካውያን በንግድና በቱሪስት ቪዛ በመግባት ለዓመታት በድርጅቱ ውስጥ ሲሠሩ መቆየታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢምግሬሽን ሕግ መሠረት በንግድ ወይም በቱሪስት ቪዛ የገባ የውጭ ዜጋ አገር ውስጥ መቆየት የሚችለው 90 ቀናት ብቻ እንደሆነ የሚገልጹት ኃላፊው፤ በድርጅቱ ላይ በተደረገው ማጣራት ግን ግለሰቦቹ ከተፈቀደው ጊዜ በላይ በመቆየት በሥራ ላይ ተሠማርተው ተገኝተዋል፡፡

ሌላው ከሦስት ዓመት በላይ ለአገር ውስጥ ገቢ በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር ግብር ድርጅቱ ሳይከፍል መቆየቱ ሦስተኛው ወንጀል መሆኑን አቶ አሰፋ አብራርተው፤ በተዘረዘሩት ወንጀሎች ምክንያት ለድርጅቱ የእገዳ ደብዳቤ የደረሰው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በአሜሪካውያኑ ሠራተኞችና በድርጅቱ ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ እንደሚወሰድ የተወሰነ ነገር አለመኖሩን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ሳመሪታን ፐርስ የተባለው ይኼው አሜሪካ በቀል ድርጅት ከ40 ዓመታት በላይ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አገሮች የሚኖሩ ችግረኞችን በትምህርት፣ በምግብና በጤና አቅርቦት ሲያግዝ የቆየ ሲሆን፣ ከ10 ዓመት በፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ በተለይ በትምህርትና በሕጻናት ላይ ሲሠራ የቆየ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የድርጅቱን ኃላፊዎችና ሠራተኞች አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ ድርጅቱ በኤጀንሲው በመታሸጉ ምክንያት ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡