ከሦስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የሐረር ውኃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት አቆመ
(በኃይሌ ሙሉ፣ ሪፖርተር)
የሐረርና አጎራባች ከተሞችን ለሚቀጥሉት ሰላሳ ዓመታት የንፁህ መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከሦስት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተጠናቀቀው የሐረር ውኃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከሃያ ቀናት በኋላ ተቋረጠ፡፡
የሐረር ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ምንጮቻችን እንደገለጹት ከአምስት ዓመታት በላይ የወሰደው የሐረር ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም ከሃያ ቀናት በኋላ ማለትም ነሐሴ 15 ቀን 2002 አገልግሎቱ ሊቋረጥ ችሏል፡፡
ከምንጮቻችን ለመረዳት እንደቻልነው የሐረር ውኃ ፕሮጀክት ሲቪል ኮንስትራክሽን ሥራ በትክክል ቢጠናቀቅም በሕንዱ ኩባንያ የተከናወነው የፓምፕ ተከላ ላይ ችግር በመፈጠሩ፣ ለሰላሳ ዓመታት የታቀደው የከተማዋ የውኃ አቅርቦት በሃያ ቀናት ጊዜ ውስጥ ተቋርጧል፡፡ የሐረር ከተማ ሕዝብም ከነሐሴ 15 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ቀድሞው የውኃ ፈረቃ በመግባት በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ውኃ ማግኘት ጀምሯል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት የሐረር ውኃ ፕሮጀክት አገልግሎት መቋረጡን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አንድ የፕሮጀክቱ ኃላፊ፣ የፓምፕ ተከላውን ያካሄደው የሕንዱ ኩባንያ የአቅም ማነስ ያለበት መሆኑንና ለፕሮጀክቱ የዋሉት ዕቃዎች የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑ ለውኃ ሥርጭቱ መቋረጥ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የሐረር የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ኃላፊ አቶ አሪፍ መሐመድ፣ የሐረር ውኃ ፕሮጀክት አዲስ ቴክኖሎጂ እንደመሆኑ መጠን በሒደት አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ነሐሴ 15 ቀን 2002 ዓ.ም. ከመብረቅ አደጋ ጋር በተያያዘ በፓምፕ ተከላ ሲስተሙ ላይ ችግር የተከሰተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የአዲሱ የውኃ ስርጭትን መቋረጥ ተከትሎ በኮንትራክተሩና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አሪፍ፣ በውኃ ሀብት ሚኒስቴር መድረክ አመቻችነት ትናንት በተካሔደው ስብሰባ ሁለቱ አካላት የፈጠሩትን አለመግባባት ለመፍታት መቻላቸውን፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም በአዲሱ የውኃ ሲስተም አማካኝነት የሐረር ከተማ ሕዝብ የውኃ አቅርቦት የሚያገኝበትን መፍትሔ እንዲያመጡ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
ከአቶ አሪፍ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ የፓምፕ ተከላውን ሥራ ያከናወነው የሕንዱ ኩባንያ ለችግሩ መከሰት መብራት ኃይልን ተጠያቂ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ መብራት ኃይል በበኩሉ ችግሩ በኮንትራክተሩ የሥራ ድክመት አማካኝነት የተከሰተ ነው በማለት እርስ በርሳቸው ሲካሰሱ ነበር፡፡
‹‹የሕንዱ ኩባንያ ያቀረበው ማቴሪያል ጥራቱን የጠበቀ አይደለም፤›› በሚል ከአንዳንድ ባለሙያዎች የተሰጠውን አስተያየት በተመለከተ ማብራሪያ የጠየቅናቸው አቶ አሪፍ እንደገለጹት፣ በጥራት ደረጃ ችግር መኖሩንና አለመኖሩን ለማጣራት አማካሪ መሐንዲሱ እያንዳንዱን ሥራ እየፈተሸ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የሐረር ከተማ የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት የዕቅድና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቡሽራ መሐመድ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ በቴክኒክ ኮሚቴ በመታየት ላይ ስለሆነ ምንም ዓይነት አስተያየት ለመስጠት እንደማይፈልጉ ገልጸውልናል፡፡