ከዋቤ ወንዝ ማዶ -ፖለቲካ
ከሳምንታት በፊት በተከበረው የመስቀል በዓል ላይ ለመታደም በአንዲት አነስተኛ የጉራጌ ቀበሌ ተገኝታ የነበረችው ማኅሌት አበጋዝ በጉራጌዎቹ ክትፎ እና ቆጮ መሀል ደጋግሞ ስሙ የሚነሳ የፖለቲካ ሰው እንዳለ እና ስሙም “ሰውየው“ እንደሚባል ትተርካለች፡፡
ጉራጌዎች ገራገር ቢጤ ሳይኾኑ አይቀሩም። ጸሐፊ ተውኔቶችም በየፈጠራ ሥራዎቻቸው የጉራጌን ገፀ-ባሕርይ መሳል የሚቀናቸው ለዚያ ይመስለኛል። የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በድራማዎች መረጋገጥ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንኳ ባየኋቸው የተውኔት፣ የድራማ እና የቀልድ ሥራዎች ቢያንስ አንድ የጉራጌ ገፀ-ባሕርይ አጥቼ አላውቅም። በሁሉም ገፀ-ባሕርይ ጉራጌ የሚወከለው ሊስትሮ ወይም የኪዮስክ ባለቤት እየኾነ እንጂ በሌላ ጽንፍ አይደለም። በተለይ ጉራጌ እና ፖለቲካ የተዛመዱበት ሥራ አጋጥሞኝ ማየቴ ትዝ አይለኝም። በአንድ የተጨቆነ ቀልድ ላይ ያየኹትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው።
አማራ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ እና ሌሎች ብሔሮች መንግሥትን ተቀየሙት እና የትጥቅ ትግል መጀመር አሰቡ አሉ። ሁሉም በየተራ እየተነሱ ስለ ትጥቅ ትግል አስፈላጊነት ሲያስረዱ ጉራጌውም ተራ ደርሶት እንዲህ አለ አሉ፤
“ወንድሞቼ ለምን እንፈራለን ወንድ ከኾናቹ ለምን ጫካ አንገባም ወሬ ብቻ ምን ያደርጋል?”
ለካንስ በስብሰባቸው መካከል አንድ የመንግሥት ደኅንነት ሰርጎ ገብቶ ኖሮ፤ “አንተ ምን አልክ! ጫካ እንግባ ነው ያልከው?” ቢለው፤ ጉራጌውም “አሃ ጋሼ እንጨት መልቀም አይቻልም እንዴ?” አለ፤ አሉ።
ፖለቲካን ለተወሰነ ብሔር ለይቶ ማስቀመጥ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ባይኾንም የጉራጌ ክህሎት (እስፔሻላዜሽን) ግን በንግድ መስክ ላይ ብቻ የሚያተኩር ይመስለኝ ነበር። ይህን መላምቴን ማስቀየር የሚችል ምልከታን ለማግኘት የቻልኩት ለመስቀል በዐል የዋቤን ወንዝ በተሻገርጉበት ወቅት ነበር።
ፖለቲካ ያወደው በዓል
ጸሐፊ እንዳለጌታ ከበደ “ኬር ሻዶ” በሚለው መጽሐፉ “ሰባት ቤቶች” ስምንት ቤት ኾነው ሳለ ነው “ሰባት ቤት” የተባሉት ይለናል። ዒዣ፣ እኖር፣ ቸሃ፣ ሞህር፣ መቆርቆር፣ አክሊል፣ ጎማረ እና ጌታ ተብለው ይታወቃሉ፤ ስምንቶቹ ቤቶች። ብዙ ቅሬታን ያስከተለው የ2000 ዓ.ም የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ውጤት ጉራጌዎችን ከ1.8 ሚሊዮን አትልቁም ይላቸዋል። 2.5 በመቶ የሚኾነው ኢትዮጵያዊ ጉራጌ ነው ማለት ነው። ብዙ ጉራጌዎቸ ውለው የሚያድሩትም ኾነ ጥረው የሚኖሩት በከተሞች አካባቢ ነው። ጉራጌዎች ለአቅመ ከተማ ሲደርሱ የዋቤን ወንዝ ለማቋረጥ ታንኳ አያስፈልጋቸውም። ሲፈልጉ በሎንቺን ሳይኾን በእግር ጭምር ሸገር ከተፍ ይላሉ። ለእነርሱ ከተማ ለመሰደድ አንድ የሊስትሮ ሳጥን ማሠራት የሚችል ብር መቋጠር መቻል ብቻውን በቂ ነው። እስከዛሬም “ሸዋ” እያሉ የሚጠሯት አዲስ አበባ በሥራ ሱሰኝነታቸው( workaholic culture) ለሚታወቁት ለጉራጌዎቹ ቅርብም ምቹም ናት። ለእነርሱ እንኳን “ሸዋ” ቻይናም ሩቅ አይደለችም። የትኛውም ጉራጌ “ሸዋ” ሄደው ብር ማብዛት የቻሉ የቅርብ እና የሩቅ ዘመዶች ስላሉት አትሰደድ ቢባል ምቀኝነት ይመስለዋል። አዲስ አበባን ያልረገጡ ለአቅመ ሊስትሮ ያልደረሱ ሕፃናት ሳይቀሩ ስለ “ሸዋ” እና “ሞጃ” ስለኾኑ ዘመዶቻቸው በቂ መረጃ አላቸው። በጉራጌ አገር ያገኘሁት አንድ ልጅ እግር “ሸዋ” ስለሚገኙ ሕንፃዎች እና የማን እንደኾኑ ጭምር በመዘርዘር አስደንቆኛል። አበሩስ ሕንፃ፣ ደንበል ሕንፃ፣ ይርጋ ኀይሌ ሕንፃ፣ ጌቱ ሕንፃ፣ ዲኤች ገዳ ሕንጻ…እያለ በቃሉ ይወጣቸዋል። ስንቶቹን ልክ ይኹን ማወቅ ባልችልም የልጁ ሀብት የማፍራት ፍላጎት እና ጉጉት በስም እንጂ በአካል የማያውቃቸውን ሕንፃዎች ያህል ግዙፍ እንደኾነ ለመረዳት አስችሎኛል።
ጉራጌዎች ብር መሥራት ያውቁበታል፤ ብር መቆጠብንም እንዲሁ። ገንዘብን ቆንጠጥ የሚያደርግን ሰው በዚሁ ብሄር ስም የምንጠራውም ለዚሁ ነው። የስኬታቸው ምስጢርም ይኸው ሊኾን ይችላል። አንድ ጉራጌ ፀጉር ቤት ገብቶ አገልግሎት ካገኘ በኋላ ሂሳብ ሊከፍል እጁን ወደ ኪሱ ከተተ። ዋጋ ጠየቀ። ፀጉር 15 ብር፣ ፂም 10 ብር በአጠቃላይ 25 ብር ተጠየቀ። ይህን ጊዜ ብር ሊያወጣ ወደ ኪሱ ገብቶ የነበረውን እጁን ወደ ጭንቅላቱ በመስደድ መላጣውን ዳበሰ። “ከፈለግክ ፀጉሬን ትከለው እንጂ ይህን ሁሉ አልከፍልም” አለ። የሚሰማው አጣ። 25 ብሩን ለማዳን የመጨረሻ ሙከራ ማድረግ ነበረበት። “እዮ እዮ ዘረፉኝ…ሌባ ሌባ…” የሚል ጩኸት አሰማ። የፌደራል ፖሊስ አባሎች ደረሱ። ምን ኾነህ ነው? አለው አንደኛው። “ጋሽ ፎሊስ…ፀጉርህ በዛ ብለው 25 ብር ዘረፉኝ አለ የጉራጊኛ ቅላፄ በተጫነው አማርኛ። ይህን ጊዜ የፌደራል ፖሊስ ልብ ተነካ። ወደ ፀጉር አስተካካዩም ዞረ። ፊቱንም በጥፊ አጣመመ። እንዲህም አለው፤ “ቧ! ስግብግብ ነጋዴ ሁላ! ለምንስ ነው ለዚህ ለሚስኪን ምታስለቅስ ያለህ?”
ከእነዚህ መሰሎቹ የጉራጌ የማኅበራዊ ግንኙነት ትርክቶች ባሻገር የጉራጌዎች ሳንቲምን የመቋጠር ጥበብ ብዙ ዐይነት መልክ አለው፤ ነገር ገን የተቋጠረው ሁሉ መስቀል በዐል ላይ ይሸረሸራል። አንድ ሊስትሮ ዓመቱን ሙሉ ጫማ በማሳመር የቋጠራትን ሳንቲም በመስቀል በዓል ደስ እያለው አውድሞት ሊመለስ ይችላል። በአነስተኛ ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከመስቀል ሲመለሱ ኪሳቸው ስለሚራገፍ ትካዜ የሚጀምሩት አውቶብስ ውስጥ ነው። ከበዐል በሚመለሱ አውቶብሶች ውስጥ ዝምታ ይነግሳል። በቀጣዩ ዓመት የተሻለ ብር ለመቋጠር ዕቅድ ይነደፋል። በየሰፈሩ የሚገኙ ኪዮስኮችን ከመስቀል መልስ ዱቤ መጠየቅ ብዙም አይመከርም የሚባለውም ለዚሁ ነው።
የመስቀል በዓል በወርኀ መስከረም መከበሩ ጉራጌዎች የአገራቸውን ፍፁም ልምላሜ “እንዲያጣጥሙ” ያስችላቸዋል። የአየሩን ንፁህነት ለመግለጽ በቂ ቃላት አይገኝም። የየመስኩን ማራኪነት፣ የመሬት ገጽታውን መሳጭነት፣ ማየት እንጂ መጻፍ ያስቸግራል። ይህን ድንቅ አየር እና ልምላሜ የትም ቢሄዱ እንደማያገኙት የተረዱ የጉራጌ ባለጸጐች የጡረታ ዘመናቸውን ከዚያው ለማሳለፍ ሲታትሩ አስተውያለኹ። በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ዕድሜያቸውን የፈጁ ዕድሜ ጠገቦችም ክብ ባርኔጣቸውን እንዳጠለቁ ፈረሶቻቸው ላይ ኾነው በየመስኩ ጎምለል እያሉ እርሻዎቻቸውን ይቃኛሉ። በኮባ ተክሎቻቸው ይሽሎኮሎካሉ። በነጋዴ ልጆቻቸው ይጦራሉ።
መስቀል ከወፍራም ቻይና ተመላላሽ ነጋዴዎች እስከ ጥቃቅኖቹ ድረስ ያሉ የጉራጌ ልጆች ቤተሰባቸው ዘንድ ሄደው የሚያከብሩት በዐል ነው። አውቶብስ ተራም እንደመስቀል በዓል ወቅት ትንፋሽ የምታጣበት ጊዜ የለም። ብዙ መቶ ቅጥቅጥ አይሱዙዎች፣ ብዙ መቶ ሚኒባሶች፣ ብዙ መቶ ሎንችኖች ሕዝበ-ጉራጌን አገሩ ይዞ ለመሄድ ይሰለፋሉ። አሁን አሁን ደግሞ የሥራ ውጤትን የሚያንጸባርቁ ብዙ መቶ የግል አውቶሞብሎች ወደ ጉራጌ አገር ይነዳሉ።
ለመስቀል ክብረ በዐል የሚተመው ሕዝበ ጉራጌ አያሌ መኾኑን ከሚያሳብቁ ነገሮች አንዱ የመርካቶ ጭርታ ነው። በመስቀል ሰሞን መርካቶ ከየትኛውም በዐል በተለየ መልኩ የወትሮ ወከባዋ ጋብ ይላል። አንዳንድ የመርካቶ ሰፈሮች የሥራ ማቆም አድማ የተመታባቸው ይመስል ወናነታው ያስፈራል። የጎዳና ንግድ የሚከላከሉት ደንብ አስከባሪዎች እንኳ ዘወትር የሚያሳድዷቸውን የጉራጌ ልጆች ይናፍቃሉ። በነገራችን ላይ የጉራጌ ልጆች እነዚህን ደንብ አስከባሪዎች የተለያየ ስም እንዳወጡላቸው ነግረውኛል። “ጨለሌ፣ ሦስት አለቃ፣ ጋሽ ፎሊሱ …”
ሰውየው አለ ወይ?
ጉራጌዎች መስቀልን የሚያከብሩት በመስከረም 17 ሳይኾን መስከረም 15 ላይ ነው። ለዐይን ማራኪ በኾነ የሥነ ሕንፃ ጥበብ የተሠሩ የሚመስሉ ጎጆ ቤቶች ሁሉ ለበዐሉ የሚሰው ከብቶችን በውስጣቸው ይሸሽጋሉ። በርጩማ ወንበሮች በክብ ቅርጽ ተደርድረው ሲያበቁ ቤተሰብ ይሰበሰባል። ለእርድ የሚሰዋው ከብትም መሀል ላይ ይቆማል። በዕድሜ ጠና ያሉ የቤተሰቡ አባላት ለእርድ የተዘጋጀውን ከብት ጀርባ እየዳበሱ ረዣዥም ምርቃቶችን ያዥጎደጉዳሉ፤ አገሩ ሰላም እንዲኾን፣ ሳር ቅጠሉ ፍሬ እንዲያፈራ፣ ልጆቻቸው በአውሮፕላን የሚመላለሱ አስመጪ እና ላኪ እንዲኾኑ አጥብቀው ይማጸናሉ። “ማርያም አጊ ትበል፤ ገብሬል አጊ ይበል፣ ጎርጊስ አጊ ይበል…” እያሉ። ክብ ቅርጽ ሠርቶ የተሰበሰበው ቤተሰብ የሽማግሌዎቹ ፀሎት መሬት ጠብ እንዳይል እጁን ዘርግቶ “አሜን!” እያለ ይቀበላል። በተሳተፍኩባቸው የምርቃት እና የእርድ ሥነ-ሥርዐቶች ሁሉ ግን ቀልቤን የሳበኝ በየምርቃቱ ሾልከው የሚገቡ ፖለቲካዊ የሚመስል ይዘት ያላቸው ፀሎቶች ናቸው። ለምሳሌ በብዙዎቹ የእርድ ሥነ ሥርዐቶች “ኤርችትኡት የገነታ ያብቋን” የምትል ዐረፍተ ነገር ሰምቻለሁ። “ሰውየውን ለእናት አገሩ ያብቃው” እንደማለት ነው። ማን ነው ሰውየው?
የሰውየው የትውልድ ቀዬ ደብረዘይት እንጂ አሁን እኔ የተጓዝኩባት የጉራጌ ቀበሌ አይደለችም። የ”ሰውየው” ወላጆች ግን ለዚህች ቀበሌ ቅርብ ናቸው። ለመስቀል በዐል የታደምኩበት ቀበሌ ከሰውየው ቤተሰቦች የትውልድ ስፍራ በ25 ኪሎ ሜትሮች ላይ ርቃ የምትገኝ ቀበሌ ናት። የሰውየው ቤተሰቦች ትውልድ ከሸራር ጎሳ ሲኾን የትውልድ ቀያቸውም አገና እዣ የሚባል ቦታ እንደኾነ ተነግሮኛል። የሸራር ጎሳ በሰባት ቤት ጉራጌ ላቅ ያለ ክብር ከሚሰጣቸው ጎሳዎች መካከል የሚደመር ነው። በተለይም ምርጫ 97 ላይ ድንገት የተከሰተው የነጋ ቦንገር ልጅ ለዚህ ጎሳ ሌላ ግርማን አላብሶት ነበር። ፖለቲካ ያወጋኋቸው የጀምቦሮ አዋቂዎች እንደነገሩኝ ከኾነ ሰውየው ያኔ የምርጫው ሰሞን ከአንድ ሌላ ዶክተር ጋር ለጉራጌዎች ዝነኛ ወደኾነው “ቦሌ ገበያ” ከተፍ አለ አሉ። “ቦሌ” ጉራጌ አገር የሚገኝ ታዋቂ ቅዳሜ ገበያ ሲኾን የአገሬው ሰዎች ተገናኝተው ወሳኝ የመረጃ ልውውጥ የሚያካሄዱበት ስፍራም ነው። ያኔ ታድያ ሰውየው በ “ቦሌ ገበያ” ተገኘ እና ልብ የሚያጠፋ ንግግር አደረገ አሉ። “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰውየው መቼ መጥቶ ሕይወታችንን እንደሚለውጠው እንናፍቃለን” ይላሉ የአገሬው ሰዎች። ቦሌ ገበያ ከፈረስ እስከ መርፌ የሚሸጥበት ሜዳ ነው። በዚያ ገበያ “ሰውየው” ባቀረበው ዲስኩር “እንኳን ገበያተኞቹ ይቅርና በስፍራው የነበሩ ፈረሶችም ተመስጠውበት ነበር” አሉ፡፡ ሕፃናት አሁንም ስለ ሰውየው ትንንሽ መረጃ አላቸው። ግማሾቹ ኢትዮጵያን የሚመራው እርሱ እንደኾነ ነው የሚያውቁት። የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ማን ነው ስትሏቸው የሰውየውን ስም ይጠሩላችኋል። የሚገርመው አንዳንድ እናቶች “ሰውየው” እሰከአሁንም እስር ቤት እንዳለ ነው የሚያውቁት። ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ደግሞ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የተወለዱ ብዙ ልጆች በ“ሰውየው” ስም ነው የሚጠሩት።
መስቀል የጉራጌ ምርጡ ክብረ በዐል ነው፤ ክትፎ ምርጡ ምግባቸው ነው። “የቦንገር ልጅ ደግሞ ምርጡ ልጃችን ነው” ይላሉ፣ በሹሹክታ። ያኔ ከአምስት ዓመት በፊት ሰውየው አገሩን እንደ ክትፎ ፖለቲካ ሲያጠጣው የጉራጌ ልጆች ለፖለቲካ እምብዛም ነበሩ። ሰውየው ድንገተኛ መሲህ የኾነባቸውም ለዚሁ ነበር። የአዲ’ሳባ ቱባዎቹ ነጋዴዎች እንኳ ይህን “የጉራጌ ነፍጠኛ” ከማወቃቸው በፊት የሚያውቁት የአባቱን እቁብ ነበር። እርሳቸው ጋራ የሚሰበሰብ ባለ ብዙ ሺሕ ብር እቁብ በጉራጌ ሀብታሞች ዘንድ እውቅ ነበር አሉ። በእርግጥ ከተሜ ጉራጌዎች ከምርጫው በፊትም ሰውየው በኢኮኖሚክስ ባለሞያዎች እና በዩኒቨርስቲ የነበረውን እንቅስቃሴ ያውቁለታል። ብዙኀኑ የጉራጌ ልጅ እርሱን በስስት ዐይን ማየት የጀመሩት ግን ያኔ ለምርጫው ክርክር በቴሌቪዥን እየወጣ ቱባ ቱባ ባለሥልጣናትን በዝረራ ጭምር እየረታ ጉድ ያሰኘ ጊዜ ነው። በተለይም የኾነ ቀን ለኾነ ባለሥልጣን “የጉራጌ ነፍጠኛ መጥቶሎታል” ሲል የቀለደ ለታ የነጋ ቦንገር ልጅ በጉራጌዎች ልብ ታተመ አሉ።
የሰውየው የአሁኑ የስደት ሕይወት በጉራጌ ልጆች የተዘበራረቀ ስሜትን ፈጥሯል። በብዙዎቹ አስተሳሰብ ሰውየው በቅርቡ መጥቶ የኢትዮጵያን ልጆች በፍቅር ሊያስተሳስር በትረ ሥልጣኑን ይረከባል። ያኔ ኢትዮጵያ የጥጋብ አገር ትኾናለች። የማር እና የወተት።
ስለ ነጋ ቦንገር ልጅ ጉዳይ ካወራኋቸው ከተማ ቀመስ የጉራጌ ልጆች አንዳንዶቹ ሰውየው አሜሪካን ኾኖ ኦባማን በቅርብ እያማከረ እንደኾነ የምር በኾነ ስሜት ነግረውኛል። ኦባማ ከምርጫ ዘመቻው ጀምሮ ያደርጓቸው የነበሩ ዓለምን ያነኾለሉ ንግግሮች የተከተቡትም በነጋ ቦንገር ልጅ ነው ብለው በጽኑ ያምናሉ። ኦባማ አሁን በአገሩ ጉዳይ ፋታ በማጣቱ እንጂ ልጃችንን ይዞት ይመጣል የሚል በጥርጣሬ ያልታጀበ ተስፋ አላቸው።
የቦንገር ልጅ በጉራጊኛ ቅኔ
የነጋ ቦንገር ልጅ በጉራጌዎች ልብ ከፉኛ ጠልቆ እንደገባ ለማወቅ ብዙ ድካም አይጠይቅም። የመስቀል በዐል ዋዜማ ምሽት በሚያበሩት የችቦ ሥነ-ሥርዐት ደማቅ የጉራጊኛ ጭፈራዎች ይካሄዳሉ። ችቦው የሚበራው ደግሞ “ጀፎሮ” ተብሎ በሚጠራው በጎጆ ቤቶች ደጃፍ በሚገኝ ለጥ ያለ መንገድ ላይ ነው። የየአባወራው “ጀፎሮ” በእሳት የጋየ በሚመስልበት የምሽት የችቦ ማብራት ሥነ ሥርዐት ልብ የሚያጠፉ የጉራጊኛ ዜማዎች በወጣት ሴቶች እና ወንዶች በቅብብሎሽ መልክ ይዜማሉ። እንዲህ የሚል ግጥም ግን ሊኖር እንደሚችል የሚጠረጥር የለም፡-
የቦንገሬ ኤገዋለ፣
ወሰደኖም ፎካከረ።
(ሲተረጎም)
የማይበገረው የቦንገር ልጅ፣
አንበርክኮ ነዳቸው (ከደጅ)፤
ኢሕአዴግ ከጉራጌዎች ለመታረቅ ሊቀመንበሩን ወልቂጤ ድረስ ልኳል። ለዩኒቨርስቲ ግንባታ “ግዙፍ” የመሠረት ድንጋይ አኑሯል። የጉራጌ ልጆች ልብ ግን “ሰውየው” ጋራ አልፕስ ተራራ ላይ ያለ ነው የሚመስለው። በመንግሥት ለረዥም ጊዜ እንደተረሱ ያምናሉ። ውኃ እና መብራት ናፍቋቸው ትተውታል። “ዕድሜ ከዓመት ዓመት ለማትጎድለው ምንጭ እና ወንዛችን” ይላሉ። መንገድ ከ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለሚገኙ ከተሞች እንኳ ሲታሰብ እኛ አዲሳባ አፍንጫ ሥር ኾነን ከኮረኮንች አልወጣንም ባይ ናቸው። መንግሥት የጉራጌ ሽማግሌዎችን ሰብስቦ ጥፋቱንም አምኖ እንታረቅ ቢላቸውም አሁንም ጠና ባሉ ሰዎች ሸንጎ፣ በገበሬዎች የማሳ ቅኝት ወቅት፣ በክትፎ ገበታ፣ በእርድ ሥነ ሥርዐት፣ በችቦ ማብራት ሥነ ሥርዐት ወዘተ የ“ሰውየው” ስም ይነሳል፣ ይወሳል፣ ይሞካሻል፤ በሹክሹክታ። አምላክ በሰላም ለእናት አገሩ እንዲያበቃው ይፀለያል። “የጉራጌ ንጉሠንዳ ጎይታ የቀየንዳ” እየተባለ። ይህን የጉራጌ “ስደተኛ መሲህ” መንግሥት “አሸባሪ” እንደሚለው ለጉራጌ ልጆች ብትነግሯቸው “ነቢይ በአገሩ መቼ ይከበር እና” የሚል ትርጉም ያለው የጉራጌ ተረት ይተርቱላችኋል። “ሰብ በገነታ ኤያሀቡጂ!!!” እያሉ፤ በከፍተኛ ሹክሹክታ።