ለዘግናኙ የመኪና ኣደጋው እልቂት ተጠያቂው ማን ነው?

ሰሙኑን የመስቀል ዋዜማ ህዝብ በኣሉን ለማክበር ሽርጉድ እያለ ነበር። በዕለተ ሰኞ ከሰባት ሰኣት በኋላ ኣስደንጋጭ የወሬ ንፋስ መንፈስ ጀመረ። ወሬውም የህወሓት የባህል ቡድን በኣንድ ኣሮጌ ኣውቶብስ ተሳፍረው ወደ ሱዳን ሲጓዙ ሩቅ ሳይሄዱ ከመቀሌ በስተደቡብ 200ኪሎሜትር ርቀት ላይ በቆቦ ኣከባቢ ተገልብጠው ብዙ ኣርቲስቶች እንደሞቱና ብዙዎቹም እንደቆሰሉ ይወራል።

የወሬው ፍንጭ መቀሌ እንደደረሰ ሰዎች ካለወትሮው በየመንገዱ፣ በየንግድ ቤቱና በየሻሂ ቤቱ ሦስትና ከዚያ በላይ እየሆኑ ቁጭት የሚነበብበት ዝምታ እንዲሁም በመንሸኳሸክ ሲነጋገሩ ይታይ ነበር። ቆይቶ ከ10 ሰዓት በኋላ ግን በግልጽ መሰማት ተጀመረ፤ በህወሓትና በመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ህዝቡ ከሰማ በኋላ ይሰራጭ ጀመር። ኣደጋ የደረሰባቸው ቁስለኞች በሄሊኮፕተር ወደ ኣሉላ ኣባ ነጋ ኣውሮፕላን ማረፍያ ማመላለስ ጀመሩ። ቁስሎኞቹ ወደ ዓይደር ሆስፒታል ሲገቡ በኣደጋው የሞቱት ደግሞ እየመጡ ናቸው ተብሎ ተወራ፤ የት እንደሚያርፉ ግን ኣልታወቀም። ህዝቡ ግን ከየኣቅጣጫው እየተመመ ወደ ህወሓት ባህል ቡድን ጽፈት ቤትና ወደ የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮምሽን ጽፈት ቤት ተጓዘ። ወደየጽፈት ቤቱ የሚጓዘው ህዝብ ፊት የሚነበበው ሃዘንና ቁጭት ካልሆነ በማሃከላቸው ንግግር የሚባል የለም ነበር።

ግን ደግሞ ለማን መሆኑ የማይታወቅ በየግሉ “ስስታሞች! ሌቦች! ለኣውሮፕላን ክራይ እንዳይከፍሉ ብርቅዬ ወገኖቻችን ኣስጨረሱዋቸው። 26ን ሰዎች እኮ 3 ኮብራዎች ይበቁዋቸው ነበር! ለራሳቸውማ ቢሆን ለኣንድ ሰው ኣንድ ኣውሮፕላን እያንቀሳቀሱ ኣይደለም እንዴ ይላሉ። ይህንን ኣባባል ህዝቡ፣ ነጋዴው፣ መንግስት ሰራተኞችና የህወሓት ኣባል ኣንድ ያደረገ ንግግር ነበር። በኣደጋው የሞቱት የህዝብ ወገኖች በቦታው ሳይደርሱ መሸ ። ህዝቡ ግን እነሱ እስኪገቡ ድረስ እያለቀሰ በፖሊስ ኦርኬስትራ ጽ/ቤትና በፖሊስ ኮሚሽን ጽ/ቤት ኣከባቢ ወደ ሚላኖ ሆቴል ኣከባቢ ሞልቶታል ። በማሃል የክለሉ ባለስልጣናት እነ ኣባይ ወልዱና ቴድሮስ ሓጎስ መጡና ሬሳውም ደረሰ ። በግዜው ኣቶ ቴድሮስ ሓጎስ ማልቀስ ጀመሩ። እዛ ኣጠገባቸው የነበሩ ሴትና ወንደ ወጣቶች ግን ለቀሰውን ትተው ኣስመሳዮች ማን ያምናቸዋል ማታ ማታ ለኣንድ ጠርሙስ ብሉ ለበል ዊስኪ (blue level whiskey) ከ6 እስከ 10 ሺ ብር ኣፍስሳችሁ ስትጠጡ ሳታፍሩ ይባስ ብሎ መጠጣቹ እንዳይጎድልባቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻቹ በኣሮጌ መኪና ልካቹ ኣስገልብጣቹ ስታበቁ ኣሁን ማልቀሳቹ ለማስመሰል ነው እንጂ ማን ያምናቸዋል ይላሉ። ግዜው ጨልሞ ስለነበር የኣምቡላንስ መብራት ካልሆነ ምንም ኣይታይም ። የወጣቶቹ ንግግርም በድምጽ እንደሆነ እንጂ ፊታቸው ኣይታይም ነበር በዚህ ምክንያትም በተለይ ከወጣቶች መጥፎ መጥፎ ስድቦች ይደመጥ ነበር ። ኣዎ ወጣቶቹ ኣንድ ያመረሩት ነገር ኣለ እንጂ እንዲህ የህወሓት ባለስልጣናት ፊት ለፊት ተሰድበው ኣያቁም ነበር ምክንያቱ የሰደባቸው ካለ ኣይቀጡ ቅጣት ይጠብቀዋልና ነው።
ኣስከሬኖቹ ወደ ዓይደር ሆስፒታል ተወሰዱ። እዛም ብዙ ህዝብ ነበር የጠበቃቸው:: በክልሉ መሪዎችና በፖሊስ ሓላፊዎችም ላይ በግልጽ የስድብ መዓት ይወርድ ነበር። በወቅቱ በሁሉም ቦታዎች ነበርን። ከኔ ጋር ኣብረውኝ የነበሩ ሁለት ነባር ታጋዮች ለሞቱት የኪነት ቡድን ኣባላት ለኣንኣንደቹ ጎረቤትና በጣም ኣድናቂዎቻቸው ናቸው።
እኔም ለነባር የኪነት ቡድኑ ኣባላት በመመልመል እስከማሰልጠን ልዩ እንክብካቤ ኣድርጌ ስለኣሳደኩዋቸው እንደ ልጆቼ እማያቸው ስለሆንኩ ሁኔታው ስስማ ማመን አቅቶኝ ህልም ወይም ቅዠት ሁነብኛል። የኪነት ቡድን አባላት ለመኪና አደጋ ተጋልጠዋል፤ ከተገለበጡትም ወድያውኑ የሞቱት ብርሃነ ጋኖ፣ ለተመስቀልና ሃንደበት እንደ ሞቱ ሰማሁ። እንደሰማሁ ወድያውኑ መንገድ ይዤ ወደ ማሃል ከተማው ተጓዝኩ። ታክሲዎች ነበሩ ገንዘብም ቢሆን ነበረኝ ግን በእግሬ እጓዛሎህ ኣልናገርም ጸሓይ ነው 3 ኪሎሜትር እንደ ተጓዝኩ ኣሁንም ታክሲዎች ይተላለፋሉ እኔም ብሆን እጓዛሎህ ሳይታወቀኝ የኪነት ብዱኑ ጽፈት ቤት ጋር ደረስኩ። በቦታውም የሟች ቤተሰቦች በሌሉበት በብዙ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ተሰብስቦ ሁሉም ያለቅሳል። እኔም ተቀላቀልኩ። ህዝብም በሁሉም ኣቅጣጫ ይመጣል።ከላይ እንደገለጽኩት ሁሉም ንዴትና ሓዘን በፊቱ ይነበባል። እኔም ከኣምስት ሰዎች ጋር ሁኜ ወደ ሚላኖ ሆቴል ደረስኩ ምክንያቱ የኣስከሬን ማረፍያ እዛው ነው ስላሉኝ። በሚላኖ ሆቴልና በትግራይ ክልል ፖሊስ ኮምሽን በኪነት ቡድኑ ጽፈት ቤት ላይ የነበረው ሁኔታ እዛውም ተመሳሳይ መንፈስ ኣለ። ዓይደር ሆስፒታልም ሄድን። በሺ የሚቆጠረውን ህዝብ ስሜቱ ተመሳሳይ ነው። ከዓይደር በጨለማ ተነስቼ ወደ ቤቴ ለመሄድ ታክሲ ላገኝ ኣልቻልኩም። ለዚህም በእግሬ ወደ ከተማ ተጓዝኩ። ኣብረውኝ ወደ ከተማ የሚጓዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ሁላችንም ኣንነጋገርም። ለየብቻችን ግን ንዴት የወለደው ብቻችን እንነጋገር ነበር። በንደዚህ ሁኔታ ሁነን መሃል ከተማ ገባን። በከተማውም መቀሌ እንደ ሁሉ ግዜዋ ኣይደለችም። ምክንያቱም ሁሉም ህዝብ አዝኗል። በየመጠጥና ሻሂ ቤት እንዲሁም ንግድ ቤቶች የሃዘን ሙዚቃ ይሰማል። ጸጥ ረጭ ብሎም ያደምጣል። ይህ መንፈስ ባለፉት ኣመታት ብዙ ታዋቂ ነባር ታጋዮችና ባለስልጣኖች፣ ታዋቂ ነዋሪ ግለሰቦች ሞተዋል። እንደዚህ ኣይነት ኣስደንጋጭ ሁኔታ ግን ኣልታየም። እንደ ገለጽኩት ታዋቂ ሰዎችንና ባለስልጣኖች ሲሞቱ በቀበሌና በየመስራቤቱ ተነግሮዋቸው የማይመጣ ብዙ ሰው ነው። በነዚህ ብርቅየ ኣርቲስቶች ኣደጋ ግን ከህጻን እስከ ሽማግሌ ራሱ ተነሳስቶ ኣስገራሚ የሆነ ትእይንት ኣሳየ። ግዜው መሸና ቤቴ ገብቸ ተኛሁ፤ ይሁን እንጂ እንቅልፍ ባኣይኔ ሊዞር ኣልቻለም። በዚህ ግዜ እኔም ማሰብ ጀመርኩ። የሮብን የቀብር በስነስርኣቱ ትእይንት ሳላይ ለኣደጋ ሰለባ የሆኑ የነበረው ኣቀባበል ኣሳሰበኝ። ለምን የመቀሌ ህዝብ በተለየ ለነዚህ ሚስኪን የህዝብ ልጆች ደነገጠና ተቆረቆረ የሚል ጥያቄ ኣነሳሁ። ብዙ የህወሓት ታጋይና ባለስልጣንም እነሱም በመቀሌ 20 ዓመት ተቀምጠዋል። ለምን እነሱ በተለየ ተወዳጅ ሆኑ የሚል ጥያቄ ደግሜ ኣነሳሁ። የያንዳንዱን ኣርቲስት የ20 ዓመት ጉዞም ገመገምኩ።ምክንያቱም እኔም ስለምወዳቸው ሁሉ ግዜ በሚሰሩበት ጽፈት ቤታቸው ሳልፍ ሰላምታ እንለዋወጥ ነበርን። ሻሂም ይጋብዙኝና ኣብረንም እንጫወት ነበርን። የምንጫወተውም ስላለፈው የትግል ግዜ፣ ስለ ጎስቋላ ኑሮዋቸው፣ መኖርያ ቤት የሌላቸው መሆኑን፣ ንሮኣቸው የተጎሳቆለ መሆኑንና በረሃ ከነበረ ሂወታቸው የተሻለ ኑሮ እንደ ሌላቸው እኔም ኣውቃለሁ እነሱም ያጫውቱኛል። እኔ የዓረና ኣባል በመሆኔ የሚደብቁኝ ነገር ኣልነበረም። እንዳውም እንደ ኣባት ቆጥረው ሁሉም ነገር ሳይሸማቀቁ ያጫውቱኝ ነበር። እንግዲህ እነሱ ይህን የሚያደርጉት ከዓረና ኣባል ኣብረህ ነበርክ ኣብረህም ትጫወታለህ በሚል ህዝብ ተሸማቅቆ እንዲርቅ በሚደረግበት ሁኔታ ነው እነዲህ እየቀረቡ የሚያጫውቱኝ።

እነዚህ ሰዎች 20 ዓመት በመቀሌ ተቀምጠው ምንም እንኳ በማህበር (በእጣ) ቤት ደርሶዋቸው መስራት የጀመሩ ቢኖሩም ኣብዛኛዎቹ ግን በቤት ኪራይ የሚኖሩ ናቸው። የነበረቻቸው የወር ደሞዝ ይቅርና ቤት ሊሰሩባት፣ ቤተሰብ ሊያግዙባት ለራሳቸውም ኣትበቃቀም ነበር። ለዚህ ኣብነት የብርሃነ ጋኖና የለተመስቀል እናቶች ፊት ያየ ሰው ራሱ ምስክር ነው። ሌላ ግን ከመቀሌ ህዝብ በኣጠቃላይም በትግራይ ህዝብ ፍቅር እንደ ነበራቸውና ራሳቸው ዝቅ ኣድርገው ሰው ኣክባሪ እንደነበሩ በህሊናዬ ማሰላሰል ጀመርኩ።

በሌላ በኩል በትግሉ ወቅት የነበራቸው የስራ ድርሻ ህወሓት የደርግ ስርዓት ደምስሶ ወደ ስልጣን እንዲወጣ የነዚህ ብርቅየ ኣርቲስቶች ቡድን የነበራቸው ወሳኝ ሚና ፈጽሞ ተወዳዳሪ የሌለው በስራቸው ውጤት ሲገመት በሻለቆች፣ ብርጌዶችና፣ ክፍለጦሮችና ኮሮች የማይገመት ትልቅ ስራ ሰርተዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሓት ካድሬዎች ብዙ ዓመታት ፖለቲካዊ ስራ ሰርተው ህዝብን ኣንቅተው ኣደራጅተው ወደ ትጥቅ ትግል ማስዘመት ያቃታቸው እነኚህ የህወሓት ኣርቲስቶች ግን ለኣንድ ወይም ሁለት ወር ወደ ህዝብ ገብተው የህዝብን ውስጣዊ ሁኔታና ስሜት በማወቅ በመዝሙር፣ ዘፈን፣ በድራማና ትያትር ወዘተ ኣድርገው በመቀስቀስ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የገጠርና የከተማ ወጣቶች ወደ ወታሃደራዊ ማሰልጠኛ ገብተው ሰልጥነው በየጦር ግንባር እንዲዘምት የማድረግ ኣቅማቸው ከፍተኛ እንደነበር በቅርብ እማውቀው ስለነበረ የነዚህ ሰዎች ትዝታ ጭንቅላቴን ረብሾት ኣደረ። ለነባር ሰራዊትም ለውግያ እንዲዘጋጅ ማነሳሳት በድህረ ውግያም ለማጽናናትና ኣእምሮን ለማደስ ትልቅ መሳርያ እንደነበሩ በወታሃደራዊ ፖለቲካዊ ማሰልጠኛዎች ለሰልጣኞች ከሚሰጣቸው ትምህርት ተስማሚ የሆኑ ቅስቀሳ በማድረግ በውጭም በኣገር ውስጥም ለሚኖረው ህዝብ ወደ ትግል እንዲዘምት በማድረግ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው በህዝብ እጅጉን ተወዳጅ ያደረጋቸው ስለነበር ያ በትግል ወቅት ከህዝብ የተሰጣቸው ፍቅር ከደርግ ውድቀት በኋላም በመቀሌ ይሁን በሌሎች የክልሉ ዞኖችና በሌላ ክልሎች በነበራቸው ጭዋነት የተሞላበት ኣቀራረብ የፈጠረው ነው የሚል እምነት ያዝኩና የህዝቡ ሰልፍና የነበረው ሃዘን እነኚህ ሰዎች ባህርያቸው በህብረተሰብ ታማኝነትን ኣሰርጸው ስላለፉ ነው የሚል ስሜት ያዝኩኝ። ሰኞ መሽቶ ሲነጋ የመቀሌ ኖዋሪና የመንግስት ሰራተኞች፣ የግል ድርጅት ሰራተኞች በሁሉም የሚታይ በሃዘን ምክንያት ሲነጋገርም ስለብርቅየዎቹ ኣርቲስቶች እልቂት ነው። ሰኞ ቀንን ሙሉ በሁሉም ቦታ መቀሌ በተቃውሞ ሓሜት ተንጣ ዋለች። ከሓሜቶቹም

1. ከመቀሌ ካርቱም ከ3400 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ጉዞ ሲደረግ በኣየር ወይም በኮብራ መኪና ለምን ኣልሄዱም? ይህም በገንዘብ ሲለካ ከ100 ሺ ብር ኣይበልጥም።
2. በኣውቶብስ ከሆነስ ምን ኣይነት ኣውቶብስ? ምን ኣይነት ሹፌር? ብትበላሽ ጥገና ወይም ቅያሪ መኪና የኪነቶቹ ጤንነት የመጎሳቆል ጉዳይ ሂደው ምን ዓይነት ተጽኖ ይነሮዋል የሚል ለምን ኣልታሰበበትም
3. ኪነቶቹ የተከራዩዋት ኣውቶብስ በሰላም ባስ ኣክስዮን ማህበር ለብዙ ዓመታት ኣገልገላ ኣርጅታ ተብላ የተሸጠች ሹፌርዋም ያልታወቀ ለረካሽ ገንዘብ ብለው ለምን ተኮናተሩ? እንደዚህ ዓይነት ስራ የሰሩ ሰዎች መጠየቅ ኣለባቸው
4. ለምን የሰላም አውቶቡስ ኣልተከራዩም ? ከሰላም አውቶቡስ ጋርም ኮንትራት ጠይቀው ውድ ሆኖብናል ብለው እንደተውት ተብሎም ይወራል። በመሆኑም በነዚህ ሰዎች እልቂት ተጠያቂ ሰው መኖር ኣለበት። የሚል ማጉረምረምና ስድቦች ማክሰኞ ስታስተናግድ ዋለች።
የኔ እምነትም ህዝቡ ከላይ ካነሳቸው ጥያቄዎች ጋር ነው የምስማማው። ከመቀሌ ካርቱም ቢያንስ ደርሶ መልስ 3400 ኪሎ ሜትር ነው። ከዛ የሚቀጥሉ ከሆነም ይጨምራል። ታድያ እንዴት ቢያጠኑት ነው ጉዘው? እነኚህ ኣርቲስቶች በሺዎች የሚቆጠር ኪሎሜትር ርቀት በመኪና ተጉዘው ደክመውና በሙቀት ተቃጥለው ምን ሊሰሩ ነው የሚል ጥያቄ በትክክል በመሪዎች መነሳት ነበረበት። ሌላም እነዚህ ሰዎች የትግራይ ህዝብ ሃብትና የብዙ ኣሴት ማህደር ናቸው። ከሁሉም ኣደጋ ሊጠነቀቁላቸውና ሊንከበከብዋቸው ይገባ ነበር። ለባጀት ቁጠባ ከተባለ በዚህ ክልል ያለው የገንዘብ ኣጠቃቀም ኣባካኝ መሆኑና ለብዙ ግብዣና ቅንጦት እንደሚውል ህዝብም የህወሓት ኣባላቶቹም ራሳቸው መሪዎቹም ያውቁታል። ለምን ለዚህች ትንሽ የ26 ሰዎች 100.000 የማይፈጅ በጀት ወደ ሱዳን ደርሶ መልስ ስንት ነው ለኣንድ ሰው 10 ሺ ቢሆንም በጠቅላላ ቢያወጡ 260.000 ብር ነው። ይህ ገንዘብ ለነዚህ ብርቅየ ወንድሞቻችን ቢከፈል ምን ጉዳት ይነሮዋል? ባለ ስልጣኖች በመቀሌ ከተማ ብሉ ለበል ዊስኪ ለኣንድ ማታ ከ6ሺ እስከ 8ሺ ገዝተው የሚጠጡ የማያሰቡ ባለ ስልጣናትም ኣሉ።

እነ ጋኖና እነ ሃንደበት እኮ ከነ ሱራፊኤል፣ መሰረት ስቡሕ (ጠርጣራው)፣ ተወልደ ጅቡቲ፣ ገብረጻድቅ፣ ሙሉጌታ ኣብረሃ (ወዲ ሰርጀንቲ)፣ ሙላው፣ እያሱ በርሄ፣ ወዲ ሰቦቃ፣ ምሕረት፣ ቀለም ማንጁስ፣ ነጻነት (እጅጋዮህ ዮውሃንስ)፣ ብርሃነ ጎበዛይና ብዙ ኣየነ ወዘተ ከላይ እንደጠቀሰኩት እንደ ሺዎች ካድሬዎች፣ ኮሮችና ክፍለጦሮች እንደሚሰሩት ሁሉ የማይተናነስ ሰራ ሰርተው ደርግን በመደምሰስ የነበራቸው ሚና እጀጉን ከፍተኛና የተከበሩ ነበሩ። ስለዚህ የነዚህ ሰዎች ሞት አግዚኣብሄር የፈቀደው እደሜያቸው ስለደረሰ ነው ተብሎ መታለፍ የለበትም። በነዚህ የታየው የጥንቃቄ ጉድለት ብዙ ህጻን ሽማግሌ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ገድለዋል ወይም ወደ ኣደጋ ጥለዋል። ብዙ ሞያዎችና ልምድ ለትውልድ ሳያሳልፉ በእንዳ ገብሪኤል ተቀብረዋል። በ21ኛው ክፍለዘመን ሰውና ሙያው በጣም ውድ ነው።
ሌላም እነኚህ የኪነት ኣባላት ወደ ሱዳን ሊጓዙ ሲታቀድ ኣሁን እንደተረዳሁት በፌደራል፣ በክልልና በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ታውቀው ኣገር ከኣገር ተስማምተው ኣገር ወክለው የሚሄዱ ናቸው። ለምን ፕሮተኮላቸው ጠብቀው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዝግጅት ተደርጎላቸው ኣልተጓዙም? ጥያቄው ለትግራይ ክልል ባለስልጣኖች ብቻ የሚተው ኣይደለም። ይህ ጉዳይ ለትግራይ ህዝብ ያበሳጨውና እንዲቃወም ያደረገው ይህም ጭምር ነው። በኔ እምነት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ተዛማጅ ድርጅቶችና ሚኒስቴሮችም ተጠያቂ መሆን ኣለባቸው የሚል እምነት ኣለኝ።
ሌላ ለነዚህ ኣገር ወክለው እየሄዱ ያሉ የኣርቲስት ቡድን የጉዞ ዋስትና፣ ፓስፖርቱ፣ እዚያው ሂደው የሚያርፉበት እየኣንድ ኣንዱን በጀት፣ ለጤንነታቸው፣ ሓኪም የኣገሩ ኣየር ጠባይ ወዘተ ተጠንቶ መፈጸም ነበረበት። ግን እሚያሳዝነው እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ነገሮች ማሟላትስ ይቅር ስለ ኣንድ ኣሮጌ ኣውቶብስም ሊያጠኑ ኣልቻሉም። ከላይ እንደገለጽኩት ሦስት የተመቹ ኮብራዎችም ይበቁዋቸው ነበር ግን ኣልተደረገም። የሚገርመው በኣሁኑ ግዜ ኮብራ ቅመምና በርበሬ ልትገዛ በመርካቶና በክልል ከተሞች ነው ስትሽለኮለክ የምትታየው። ግለ ሰቦችኮ ከሁለት ሦስት ኮብራዎች በላይ ያሰማራሉ። ችግሩ ግን የህወሓት/ኢህኣዴግ ባለስልጣኖች ህዝብ መስታዎት ነውና ህዝብ ይታዘበናል የሚል ኣሰተሳሰብ ከጭንቀላታቸው ከፋቁት ብዙ ኣመታትን ኣስቆጥረዋል።

የቀብሩ ዋዜማ በመቀሌ ከተማ ህዝብ የነበረው ተመልክተናል። ሮብ (የመስቀል) ቀንስ ከጥዋት እስከ ማታ አንዴት ኣለፈች? ትእይንቱ ምን ነበር?
ዕለተ ሮብ ከጥዋት እሰከ ማታ የነበረው ትእይንት
ማክሰኞ መሽቶ ሲነጋ ሮብ 17 መስከረም የተፈጥሮ ዑደት ነውና ተረከበቻት። ይህቺ ቀን ድሮ የመቀሌ ነዋሪ ህዝብ የመስቀል በዓል ለማክበር ጥዋት ተነስቶ ወደ ሰውሒ ንጉስ የመስቀልና ጥምቀት የሚከበርበት ሜዳ ዳሜራ ለመሳተፍ ያለችው ልብስ ለብሶ ሲጓዝ ይታይባት ነበር። የዘንድሮ መስቀል ግን ወደ መስቀል ዳሜራ እንደ መሄድ ፈንታ ጉዞው በሰውሒ ንጉስ ኣጠገብ ወደ ሚገኘው የህወሓት ባህል (ፖሊስ ኦርኬስትራ) ጽ/ቤት እንደ ገመድ ተሳስሮ እያለቀሰ እንደጎርፍ ተመመ። የነዛ ጀግኖች ኣርቲስቶቻችን ኣስከሬንም እዛው መጥቶ ሙሉ ስርዓተ ፍትሓት ሲደረግላቸው ኣረፈደ።
የተከበራቹ ኣንባብያን! ባለፉት 20 ዓመታት ታዋቂ ግለሰቦች ሲሞቱ ወይም የፖለቲካ ባዓሎች ሲከበሩና ስብሰባ ሲደረግ በየቀበሌውና በየወረዳው ትእዛዝ እየተሰጠ ተሰለፉ! ቅበሩ! ተሰብሰቡ! እየተባለ ሰው በግድ ነበር የሚወጣው። በየመስሪያ ቤቱም በትእዛዝ ነው የሚወጣው። የሚወጣው ህዝብም በጣም ኣነስተኛ ነው። እስካሁን ያየናቸው ሰልፎችና ቀብሮች ህወሓት/ኢህኣዴግ እንዲሁ ሳይሰለች በ1984ዓ.ም የየካቲት የህወሓት የምስረታ በዓል ቀበሌ፣ ሲከበር፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዋዜማና ከድል በኋላ የተደረጉ ሰልፎች ብዙ ይባሉ ነበር ያም በግድ በቀበሌና በወረዳ ተጎትጉቶ። የነዚህ ብርቅየ ጀግኖች ኣርቲስቶቻችን ቀብር ግን የመቀሌ ከተማ የቀጠና፣ ወረዳ መሪዎችና ካድሬዎች ስራ ያስፈታቸው ክስተት ሁኖ ታየ። የመቀሌ ህዝብ ግን ራሱ ኣምኖበት ብቻ ሳይሆን ያ ጉዳይ ዘግናኝና ኣሰደንጋጭ፣ ያለ ጥናት የተሰራ፣ እነዛ ኪነቶች በህዝብ ኣይንና ልብ ገብተው ተወዳጅ በመኖራቸውና በስርኣቱም ተሰሩት ስራ ግምት ሳይሰጠው በዝቅተኛ ኑሮና ድህነት ውስጥ የነበሩ በመሆናቸው ቆጭቶት ማንም ሰው ና ውጣ ሳይለው ከመቀሌና ኣከባቢዋ፣ ከዞኖችና ወረዳዎች ቁርስ ሳይበላ በየኣከባቢው የመስቀል ዳሜራ ሳያከብር ሰውሒ ንጉስና የመቀሌ ጎደናዎች በሙሉ በህዝብ ተጥለቀለቁ። ኣስከሬኑ ገና ሳይነሳ ህዝቡ ተሰልፎ ስርዓተ ፍትሓቱ እየተገባደደ ነው። ሰው ሁሉ በለቅሶ እያረረ እምባውም እየፈሰሰ ኣሳዛኝ ገጽታ ይታይ ነበር።

ሰኣቱ ከተባለለት 3 ሰዓት እያለፈ ነው። ምክንያቱም የህወሓት ባለስልጣኖችና ሌሎች ቀባሪዎች ከኣዲስ ኣበባ እየመጡ ነው ተባለና ቆይተው በቦይንግ ተጭነው ብዙ ሰዎች መጡ። ብዛት ያላቸው የህወሓት ባለስልጣኖችም በተሰለፈው የህዝብ ማሃል ሰንጥቀው ገቡ። ግራና ቀኝ የነበረው የህዝብ ሰልፍ ሓሜትና ጥላቻ እንዲሁም ስድብ ከህዝቡ ፊት ያነቡ ስለነበረ ኣንገታቸው ደፍተው ኣንጠርምመው ኣስከሬኑ ወደ ኣለበት ገቡ። ቆየት ብለው ከህዝቡ ጋር ተፋፍነው ለመጓዝ ጠልተው ነው መሰል ወይም ሌላ ምክንያት ይኖራቸዋል ኣይታወቅም ተመልሰው ኣሁንም ወጡ። ሲመለሱ ሓሜት ቀርቶ ስድብም ነበር። ግን እነሱ ሰምተው እንዳልሰሙ ሄዱ። የኣገር መከላከያ ሰራዊት እጅጉን በብዛት ነበረ። መከላከያው ሰራዊቱ ሓዘን እንደተሰማው ከፊቱ ይታያል።

ሌላ የሟች ቤተሰቦች ከተምቤን፣ ከቆቦ፣ አላማጣ (ራያ) ከኣክሱም፣ ከሸራሮ በብዙ ኣውቶብሶች ሞልተው መጡ። ብዙ ሳይቆዩም ኣስከሬኑ ጉዞ ቀጠለ። መንገዶቹ ጠበቡ፣ ሰው ተጨናነቀ። የከተማው መንገዶች ሁሉ በተጓዥ ሞሉ። ወደየሰማእታት ሓወልት በሁሉም ጎደናዎች ተከፋፍሎ ተጓዘ። የሰማእታቱ ግቢ ከመጣው ህዝብ 1 ከመቶም መያዝ ኣልቻለምና ህዝቡ ወደ እንዳገብሪኤል ጫካ ኣልፎ ለመቆየት ተጓዘ። ያም ቦታ ህዝቡ ሊይዘው ኣልቻለም። በሁሉም ጎዳናዎች በጠራራ ጸሓይ ቆመ። በሓወልት የነበረ የኣስከሬን ሽኝት ስነ ስርዓት ረዘመ። ህዝብም በጸሓይ ደከመ። የአቡነ ጳውለስ ንግግር ኣዳመጥንና ቀጥሎም የክልል መሪያችን ኣቶ ኣባይ ወልዱና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድህንነት ኣማካሪው ኣቶ ጸጋይ በርሄ መግለጫ ሲሰጡ ብዙ ህዝብ ተበሳጭቶ ከነበረበት እየፈረሰ ወጥቶ ወደ እንዳ ገብሪኤል ሄደ። ኣንድ ኣንድ ሰዎችም ጮክ ብለው በመናገር ኣስመሳዮች ኣታጭበርብሩን ራሳችሁ ገድላችሁ ስታበቁ ቀብሩን ወደ ፖለቲካ ማራመጃነት ቀይራችሁ ኣታጭበርብሩን ሲሉ በኣከባቢው የነበሩ የህወሓት መሪዎች ደንግጠ0ው ሁሉም ኣንገታቸው ደፉ። በግዜው ከኣጠገባቸው ብዙ ካድሬዎች ነበሩ። ለነዛ ሲሳደቡ ለነበሩ እውነታቸው ነው የሚሉ ነበሩ። ሲቪል ለባሽ ደህንነትም ነበሩ። ህዝቡ ግን ፍርሓት ኣልነበረውም ድህንነትም ሰምተው እንዳልሰሙ ክትትላቸውን እየቀጠሉ ከህዝብ ኣብረው ማማት ጀመሩ። በሌላ ስራም ይህን ባህል ቢያዳብሩት ኣይከፋም።

ሌላ የነበረው ስድብ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው የመጣችሁ እንጂ ኣዝናቹ ልትቀብሩ ኣልመጣቹሁም። ሓቀኞች ብትሆኑ ለገንዘብ ሳትሳሱ ወጪ ብታወጡና በኣውሮፕላን ቢሄዱ ልጆቻችን ኣይጠፉም ነበር ስስታሞች ናችሁ። ለቦይንግ ኣውሮፕላንና ለሄልኮፕተርና ለኣበላቱ ለሆቴል በኣጠቃላይ ለቀብር ማስፈጸምያ ስንት ሚልዮን ብር ጠፋ የሚል ንግግር ሁሉም ቀባሪ ህዝብ ነው የሚናገረው ህጻናትም ጭምር። ሌላ ቀርቶ በኤፍ ኤም መቀሌና ኤፍ ኤም ፋና ህዝቡ በስልክ እየደወለ ወንድሞቻችን በኣሮጌ መኪና ደፋቹሃቸው፤ መንግስት ካለ እነሱን በዚይ መንገድ ያሰማሩ ሰዎች ይጠይቁልን። ለኣንድ ሰው ኣውሮፕላንና ሄልኮፕተር እያንቀሳቀሳችሁ ለነዚህ ኣንድ ኣውሮፕላን ወይም ሄሊኮፕተር ለምን ኣልመደባችሁም። ለዘር ማንዘራችሁ በሚልዮኖች እየከፈላቹህ እያሳከማቹሁና እያስተማራችሁ ለነዚህ ብርቅየ ልጆች ከትግራይ ካርቱም ድረስ ያውም ለመንግስት ተልእከሎ ሊፈጽሙ የኣውሮፕላን መጓጓዣ መመደብ ለምን ተሳናችሁ? የሚሉ ኣስተያየቶች ይሰነዘሩ ነበር። በቀብሩ ስነስርዓት የ10 ዓመት ዕድሜ ህጻናት ሳይቀሩ ነበሩ። ሌላ ቀርቶ ወጣት ሴት ልጆች ወደ ቀብር መሄድ የቅርብ ዘመድ ካልሆኑ በስተቀር ወደ ቀብር ወጥተው ኣያውቁም ነበር። በኣርቲስቶቹ ቀብር ግን የሚበዛው ወጣት ሴቶችና ወንዶች ነበሩ።

የኣርቲስቶቹ ቀብር ኣንድ ኣንድ ሰዎች ተቃውሞ ሰልፍ ነው ወይስ ተራ ቀብር እያሉ ጥያቄ የሚያነሱ ብዝዎች ናቸው። በኔ በኩልም ይህ ጉዳይ ቀብርም ተቃውሞ ሰልፍም ነው የሚል እምነት ኣለኝ። ምክናያቱም
1. ህዝብ በምሬት ኣዝነዋል። ለምን? የሚወዳቸው ልጆቹ በመቀሌ ከተማ እየተቀበሩ ነውና በተጨማሪም እነዚህ ኣርቲስቶች በህብረተሰቡ ውስጥ በሁሉም ኢኮኖምያዊ÷ ማህበራዊና ባህላዊ ችግሮችና ሁኔታዎች እንዲሁም በሃዘንም በደስታም ተሳታፊ ስለነበሩ ነው።
2. ተቃውሞም ነው። ምክንያቱም ለምን በኣውሮፕላን ኣልሄዱም? ለምን እንክብካቤ ኣልተደረገላቸውም? ድሆች ከሆንም ለመሪዎችና የት ነበሩ ለማይባሉ ካድሬዎች እንክብካቤ ይደረጋል። በኣጠቃላይም ህወሓት ለፍተውና ተዋግተው ኣካላቸው ጎድለው ወደ ስልጣን ያመጡዋቸው ታጋዮች እንክብካቤ ኣያደርግም። ኣሁን መጥተው ያሉ መሪዎችም በህዝብ ተቃውሞ ስላለ ለፖለቲካ ፍጆታ ነው የመጡ የሚል ተቃውሞ ነው። በሌላ በኩል በዚህ ከተማ ከባድ የኑሮ ውድነት፤ ስራ ኣጥነት፤ የውሃ ችግር፣ የሙስናና ብልሹ ኣስተዳደር ስላለ ተጨማሪ ስሜትም ስላለው ነው። እዚህ ላይ በቀብሩ ስነ ስርዓት ለነበሩ መሪዎች ትልቅ ቅጣት ነው ያጋጠማቸው። ህወሓቶች ግን ሁሌ ከጥፋታቸው ኣይማሩምና ለዚህ የህዝብ ጥያቄና ቁጭት ለማለሳለስ በቀብሩ ስነስርዓት ማግስት በየቀበሌው ካድሬዎችን በመሰብሰብ ሁሌ እንደተለመደው ባህሪያቸው ችግሮቻቸውን በሌላ ኣካል መለጠፍ ይህም ለዓረና ትግራይ እነዚህ ነፍጠኞችና የነፍጠኛ ኣሽከሮች ኣርቲስቶቹ ለምን በኣውሮፕላን ኣልተላኩም እያሉ በሚያናፍሱት ወሬ ህዝብ እያደናገሩ ነው ስለዚህ በትግራይ ህዝብ ንፋስ አንዳይገባ ተጠንቀቁ እያሉ ያስፈራራሉ።

ኣስከሬኑ ወደ መቃብሩ ደረሰ
ሁሉም ቀባሪ ወደ ኣስከሬን ማረፍያ ጉድጓድ ተጠግቶ ከበበው። ሴቶቹም ወደ መቃብር ኣከባቢ መጡ በህጉ ሴት መጠጋት የተከለከለ ነው። ኣሁን ግን እጅግ ብዙ ወጣት ሴቶች ከወንዱ ተደባልቀው ወደ መቃብሩ መጡ። ሴቶች ልቀቁ ሲባሉ ኣንለቅም ኣሉ። ከፊታቸውም ከባድ ቁጣ ይነበብ ነበር።

የህወሓት መሪዎች ወደ መቃብሩ ኣበባ ሊያስቀምጡ ሲመጡ ከወጣቶች ይወርድ የነበረ ስድብ ከተራራ እንደሚወርድ የድንጋይ ናዳ ይመስል ነበረ። ይህ ምን ያሳያል? ለህወሓት መሪዎች የማስጠንቀቅያ ቢጫ ካርድ ነው ከልብ ካዳመጡት።
የቀብር ስነ ስረኣቱ ህዘቡ ከ12 ሰዓት ጥዋት እስከ 7ሰዓት ከ30 ጸሓይ መታኝ ውሃ ጠማኝ ራበኝ ደከመኝ ብሎ ሳይሰለቸው በህዝብ ሓዘንና ንዴት ተፈጸመ። እዚህ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ያለ ምንም ኣስገዳጅ ይህን ያህል ቁጥር ያውም ካሁን በፊት ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ መንገድ ተገባደደ።

የቀብሩ ስነ ስርዓት ከተገባደደ በኋላ ምክንያቱ ባልታወቀ ጥዋት ያልነበሩ ብዙ ፌደራል ፖሊሶች ወደ መቃብሩ ባለስልጣኖች ወደ ኣሉበት መጡ። ህዝቡ ምንም ደንታ ሳይሰጣቸው መንገዶች ጠበውት ለማለፍ ተቸግሮ በየኣቅጣጫው በየቤቱ ሄደ። ባለ ስልጣኖቹም በብዙ ወታሃደሮች ታጅበው ተጓዙ። ወደ ማሃል ከተማ ስንመለስ ሁሉም ሴቶች የኩታቸውን ጥለት ወደ ላይ ኣድርገው ለብሰው በተለያየ ስራቸውን ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ እነኚህ ኣርቲስቶች ራሳቸው በበጎ ተግባራቸው በህብረተሰቡ ተወዳጅነት ስለፈጠሩ ነው።

ከቀብር በኋላ ህዝቡ ምን ይላል?
ሁሉም ሰው ከወጣት እስከ ሽማግሌ የነዚህ ሰዎች መጥፋት ተጠያቂዎች መኖር ኣለባቸው የሚል ጥያቄ ኣለ። እነዚህ ኣርቲስቶች ለጉዞ ተነሱ ሲባሉ እንደነ ሃንደበት ያሉ ለምን በኣውሮፕላን ኣንሄድም? ወደ ሱዳን በመኪና ጉዞ ለጤናችንም ጥሩ ኣይደለም፣ ለኣደጋም ተጋላጭነት ኣለው፣ ምክንያቱም ከኣሁን በፊት ወደ ሱዳን ተጉዘን ብዙ ችግር ኣጋጥሞናል የሚል ሓሳብ ቢሰጡም መሪዎቹ ግን ለኣውሮፕላን የሚሆን በጀት የለንም እንዳሉዋቸው ህዝቡ ይናገራል።
ገብሩ ፋኖ የሚባል ኣርቲስት ግን ፍጹም ጠንክሮ በመቃወም ያ የመኪና ለትራንስፖርት የተመደበ በጀት ስጡኝና የራሴን ጨምሬ በኣውሮፕላን ልሂድ ካልበለዚያ በመኪና ኣልሄድም ብሎ እንደቀረ ህዝብ ኣውቀዋል። ይህም በህዝቡ መጥፎ ስሜት ፈጥረዋል።

በሌላ በኩል እነኚህ ኣርቲስቶች ለሰላም ባስ ኣክስዮን ማህበር ኣውቶብስ ኩንትራት ጠይቀው እንደ ነበሩና ዋጋው ውድ በመሆኑ ባጀት የለንም ብለው መልስ የሰጡዋቸው ህዝብ ስላወቀው ሓዘኑንና ንዴቱ ኣባባሰው። ግን እነዚህ ባለ ስልጣኖች ለምን እስከዚህ ድረስ ሳሱ? በትግራይ ክልል በብዙ ሚልዮን ብር በሙስና ይመዘበራል። ሌላ በማስፈጸም ኣቅም ማነስና በላሸቀ ኣስተዳደራቸው ምክንያት ከ2003 ዓ/ም የክልሉ 3.1 ቢልዮን በጀት የ በጀቱ 30% የሚይዝ (930 ሚልዮን) ብር ወደ ማእከላዊ መንግስት ፈሰስ ሁኖ የለም እንዴ? ሌሎች የህወሓት ድርጅቶች በቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ኣለ ኣይደለ? እነዚህ ሰዎች ለምን ከሕይወት ይልቅ ገንዘብ ለማካበት ይሳሳሉ? ለገንዘብ እኮ ሰው ነው የሚያመጣው። ኣሁን ሊሄዱበት ታስቦ በነበረው የሱዳኑ ፌስቲቫል ቢያንስ ለጉዞዋቸው ሊሸፍን የሚችል ሽልማት አያጡም ነበር። ግን የሆነውን ሆነዋልና የሚጠየቁ ይጠየቁ። ኣሁን ቤተሰቦቻቸውና ልጆቻቸው የወደፊት እጣ ፈንታቸው ምን ይሁን?

በኔ እምነት የህዝብም ስሜትና ፍላጎት ሊሆን የሚችል እነዚህ ኣርቲስቶች ከበረሃ እንደገቡ የራሳቸው የልጆቻቸውና ቤተ ሰቦቻቸውም በኣኗኗራቸው ምንም ለውጥ የላቸውም። ኣብዛኛዎቹ እስከ ኣሁን የራሳቸው መጠለያ የላቸውም። ጥቂቶቹ ቦታ ኣግኝተው ሊሰሩት ያልቻሉ ናቸው። በነበረች የወታደር ደሞዝም ይቅርና መጠለያ ለመስራት ንሮዋቸው ለመግፋትም ኣታስችልም። የነዚህ የሙታን ልጆች ልትሰጣቸው የምትችል የጥሮታ ኣበል ናት እሷም ትርጉም ያላት ኣይደለችም።
የኔ ኣስተያየት የህወሓት/ኢህኣዴግ መሪዎች በትክክል ኣዝነው ከሆነ ጃኬት ሻርፕና ኮፍያ ለብሰው በኣውሮፕላን ተጉዘው በሓዘን መገኘቱ ጥሩ ነገር ነው። ግን ይህንን በቂ ኣይደለም። ያለፈው ወንጀል እንዳለ ሁኖ መታሰብና መተግበር ያለበት የነዚህ ጀግና ኣርቲስት ልጆችና ቤተሰቦች መጠለያ፣ ምግብ፣ ውኃ፣ ህክምናና ትምህርት የሚያገኙበትን ዕድል ቢያፈላልጉላቸው ሁሉም ዜጋም ለነዚህ ሰዎች እጁ ከመዘርጋት እንደማይቆጠብ ተስፋ ኣለኝ። የህወሓት መሪዎችም የሚሰበሰብ ገንዘብ እንዳይባክን በህዝብና በሟች ቤተሰቦች እንዲሁም በሌሎች ድርጅቶች ኣንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ገንዘብ ተሰብስቦ ለዘለቄታ ህጻናት ልጆቻቸውም ለመጻኢ ዕድላቸው ቢታሰብላቸውና ቢሰራላቸው ለህወሓት/ኢህኣዴግ ለህዝብም ለመንግስትም መልካም ነገር ይፈጥራል። የሚሰበሰበው ገንዘብ ግን ጥብቅ ቁጥጥርና ግልጽነት እንዲሁም ተጠያቂነት ባለበት ማንም ድርጅትና ግለ ሰብ እጁ በማያስገባበት መፈጸም ኣለበት። ከኣሁን በፊት የነ ሓየሎምና ሌሎች የተሰዉ ታጋዮች ከሰራዊትም ከህዝብም ብዙ ሚልዮን ብር ተሰብስቦላቸው ነበር። ብዙ ሓሜት ኣለ። የነዚህም እንደዛ እንዳይሆን ከሓሜት የጸዳ መሆን ኣለበት። በነዚህ ሰዎች ስምሪት ተሳታፊ የነበሩ ባለ ስልጣኖችም ኣስፈላጊውን እርምት ቢሰጣቸው የህዝብን ቁጣ ሊያበርድ ይችላል።

ክብርና ሞጎስ ምንም ሳያልፍላቸው ለተሰዉ የህዝብ ልጆችና ኣርቲስቶች!
ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ ብርታትና መፅናናትን እመኛለሁ!

አቶ አስገደ ገ/ስላሴ

ኢትዮሚድያ – Ethiomedia.com
October 3, 3022