[አንድ ለቅዳሜ!] መለስ ኮሎምቢያ ፖፕ ቤኔዲክት እንግሊዝ

በነገራችን ላይየሰሞኑ የኢሕአዴግ ጉባኤ ምን ማለቱ ነው? እኛ እኮ ቻይና ሞዴላችን ናት ሲባል በኢኮኖሚ ብቻ መስሎን ነበር። ውይ በፓርቲ ልብስም ጭምር ሆነ እንዴ? ኮፍያው አልቀረ፤ ምንጣፉ አልቀረ። አይ እንዲህ ከሆነ አንድ ፊቱን አጠራርም ይቀየርልና። ሊቀ መንበር መሌ ይባልልን፤ ልክ ሊቀ መንበር ማኦ ወይም ሊቀ መንበር መንጌ እንዲል። ጉባኤው በኢቲቪ የተዘገበበት መንገድ ደግሞ በልጅነታችንን ያየነውን የኢሰፓ ጉባኤ የሚያስታውስ ነው። “አውራ ፓርቲ” በደንብ እየገባችን ነው።ግን ግን ይሄ “አውራ ፓርቲ” የሚለው ስያሜ በድርጅቱ ሊቀ መንበር ታምኖበት የጸደቀ ነው? ትርጉሙ እኮ ያምታታል። ለምሳሌ “አውራ” የሚለው ዋና፣ ታላቅ፣ መሪ፣ የጫጩቶቹ ፓርቲዎች ሁሉ አባት የሚል በጎ ትርጉም ይሰጣል። እናቲቱን ዶሮ መፈለግ የሕዝብ ጉዳይ ነው። ጸረ ልማትና ጸረ ሕዝብ ኀይሎች ግን “አውራ” የሚለውን “እንደልማድህ ለፍልፍ፣ ተናገር፣ ወሬ እንደሆን አያልቅብህም፣ አንተን ከማዳመጥ ሌላ ምን ምርጫ አለን አውራብን፣ ደሞ ጀመረህ በል አውራብን ልባችንንም አውልቀው” እያሉ የተሳሳተ ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ። እስቲ አሁን አንዱ ተንኮለኛ “አውራ ፓርቲያችን” ሲል ምን ማለቱ ነው? ደግሞስ ይህ ስያሜ አጋር የምንላቸውን ፓርቲዎች ጸረ ሕዝቦች “ጫጩት ፓርቲዎች” እንዲሏቸው በር አይከፍትም ወይ? በሒደት “አውራ ፓርቲ” ምስጋና መሆኑ ቀርቶ ስላቅ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ወይ ይህንን ቃል አለአግባባ አጥብቆ ወይም አላልቶ ማንበብን፤ እንዲሁም ለራስም ሆነ ለሌላ ሰው ከተፈቀደው ውጭ የሆነ ትርጉም ሊሰጥ በሚችል ወይም ሊሰጥ ይችላል ተብሎ በሚያስጠረጥር ቃናና ድምጽ መናገርን የሚከለክል ሕግ ማውጣት የአዲሱ ፓርላማ የመጀመሪያ ስራ ይሁን አለዚያም ሳይለመድ ይቀየር። አማራጭ መጠሪያዎችን እንቀበላለን። ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ