የ“መድረክ” ውሎ
(ሙሉ ገ.)
ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው የመብራት ሃይል አዳራሽ በበቢንጎ ጨዋታ አፍቃሪዎች ዘንድ ተወዳጅ ነው።በተለይ በእረፍት ቀናት ። አንዳንድ ሰንበቶች ግን የተለመዱት “ቢንጎ” የሚሉ ተደጋጋሚ ጩኽቶች “ዲሞክራሲ፤ ፍትህ፤ ነጻነት” በሚሉ ቃላት ተተክተው በአዳራሹ ያስተጋባሉ። ያኔ አንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ አዳራሹን ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ እንደተከራየው ግልጽ ይሆናል። ባለፈው ቅዳሜ መስከረም ስምንት የሆነውም ይሄው ነው።
የኢትዮጵያ ፌዲራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሰኘው የፓርቲዎች ጥምረት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር ለመምከር ከሰባት ሰዓት ጀምሮ የአዳራሹን በር ክፍት አድርጎ መጠበቅ ይዟል። ሁሉም የመድረክ የበላይ አመራሮች በቦታው ተገኝተዋል። ከወቅቱ የጥምረቱ ሊቀመንበር ኢንጀነር ግዛቸው ሽፈራው አንስቶ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር እና የ“አንድነቱ” አቶ ስዬ አብርሃ፣ የ“ኦህኮው” መረራ ጉዲና፣ የ“ህብረቱ” በየነ ጴጥሮስ፣ የ“አረናው” ገብሩ አስራት ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። አሁን በእስር ላይ የሚገኙት እና ከሁለት አመት በፊት በዚሁ መድረክ ላይ ስለ ፓርቲያቸው የወደፊት ራዕይ ለህዝብ አብራርተው የነበሩት የአንድነት ሊቀመንበር ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአመራሮቹ ጋር መገኘት ባይችሉም በስብሰባው ታውሰዋል።
በአካባቢው በርከት ብለው ጥብቅ ክትትል ያደርጉ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት ቢኖሩም በስብሰባው ለመሳተፍ ወደ አዳራሹ የተመሙት አብዛኞቹ የመድረክ አባላትና ደጋፊዎች የወይዘሪት ብርቱካን ምስል ያለበትን ቲሸርት አድርገው ነበር። የሊቀመንበሯን ጉዳይ “ለምን ችላ ተባለ?” ሲሉም ጠይቀዋል። ለጥያቄው ከአንድነት ፓርቲ አመራሮች ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ፓርቲው የሊቀመንበሯን እስር አስመልክቶ ያደረጋቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለተሳታፊው ተብራርቷል። “ኢህአዴግ ለሴቶች የመሪነት ድርሻ ሠፊ ድጋፍ እሰጣለሁ እያለ በመገናኛ ብዙሃን ቢናገርም፣ በተግባር ግን የሴቶችን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማኮላሸት ወጣቷንና ጠንካራዋን የጽናታችን ተምሳሌትና የአንድነት- መድረክ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በማሰር ሴቶችን በፍርሃት ድባብ ውስጥ በመክተት ወደ ፖለቲካው መድረክ እንዳይመጡ ገድቦታል” ሲሉ የመድረክ የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ተጠሪ የሆኑት ወ/ሮ ላቀች ደገፉ ተናግረዋል።
ስምንት ሰዓት ተኩል የተጀመረው ስብሰባ ቀጥሏል። የስብሳበው ተሳታፊዎችም ጥያቄዎችን ማዝነብ አላቋረጡም። ድንገት ከተሳታፊዎቹ መሀል ቀልብ ሳቢ ጥያቄ ተሰነዘረ። “ለመሆኑ መቼ ነው ቀደም ሲል ለሰሩት ስህተት ይቅርታ የሚጠይቁት?”። ጥያቄው ለአቶ ስዬ አብርሃ የቀረበ ነበር። ይቅርታ ለመጠየቅ ወደ ወደኋላእንደማይሉ የተናገሩት አቶ ስዬ ከይቅርታ በፊት ግን መቅደም ያለበት ነገር እንዳለ 2500 ለሚጠጋው ተሰብሳቢ አስረድተዋል። “መጀመሪያ አብረን ታግለን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እናድርገው፤ ከዚያ በኋላ በሀገሬ ላይ ያጠፋሁት ጥፋት ካለ የኢትዮጵያን ሕዝብ እግር ሥር ወድቄ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ያሉት አቶ ስዬ “የሕግ የበላይነት እስኪሰፍን ድረስ እኔ መቼም ቢሆን ከሠላማዊ ትግሉ አልወጣም፤ እናንተም በፍርሃት ተሸብባችሁ ከሠላማዊ ትግሉ አትውጡ፤ በቃኝ ደከመኝ ሳንል አብረን ታግለን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እናድርገው፡፡ ከዚያ በኋላ ያጠፋሁት ካለ ይቅርታ ለመጠየቅ ወደኋላ አልልም” ሲሉ ለጥያቄው ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ወቅት የአቶ ስዬ የትግል አጋር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራትም ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቀዋል። “መድረክን ከሠላማዊ ትግል ወጥቶ ወደ ትጥቅ ትግል እንዲገባ መምከር ተገቢ አይደለም” ሲሉ የስብሰባውን ታዳሚ የሳሰቡት አቶ ገብሩ “አረና ለዴሞክራሲና ለነፃነት ፓርቲ በሚንቀሳቀስበት ቦታዎችም ወጣቶች እንዲህ አይነት ዝንባሌ እያሳዩ ነው፣ ነገር ግን በጭራሽ ተስፋ መቁረጥ የለብንም” ብለዋል፡፡ “እኔ እና የትግል ጓደኛዬ አቶ ስዬ አብርሃ በዚህ አይነቱ የትጥቅ ትግል ብዙ ዓመታትን አሳልፈናል፤ ይሄንን አይነቱን ትግል ብናምን ኖሮ እንገባበት ነበር” ያሉት አቶ ገብሩ አስራት ነገር ግን “እንደ ሠላማዊ ትግል ሁሉን አቀፍ ፋይዳ ያለው ትግል የለም” በማለት የዚምባቡዌን የነፃነት ታጋይ ፓርቲን ተመክሮን ዋቢ አድርገው አንስተዋል፡፡ አቶ ስዬም ሆነ ሌሎች የመድረክ አመራሮች ስለ ሰለማዊ ትግል ፋይዳ ለስብሰባው ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ ቢያስረዱም ተሰብሳቢዎቹ በጥያቄ ከመሞገት አልቦዘኑም።
አንድ ተሳታፊ “ላለፉት ሃያ ዓመታት በሠላማዊ ትግል ታገላችሁ፣ ግን ምን ለውጥ አመጣችሁ?” ሲል ከመድረክ አመራር ውስጥ ለረጅም ጊዜ በተቃዋሚነት የቆዩትን ጠይቋል። “ላለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሂደት ተጠናክረን በመስራታቸው በ1997 ዓ.ም ምርጫ የሕዝቡን ድምጽ ሙሉ በሙሉ አግኝተናል፤ በ2002 ምርጫም ኢህአዴግ አሸንፌያለሁ ቢልም በእውነት ማን እንዳሸነፈ መራጩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ ያውቀዋል” ሲሉ ዶክተር መረራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አቶ ገብሩ አስራትም “ሕዝቡ የሰጠንን ድምጽ ኢህአዴግ ነጥቆን አሸንፌያለሁ ቢልም፤ በእውነት በፖለቲካና በሞራል የበላይነት አሸንፈነዋል” ሲሉ የዶክተር መረራን ሀሳብ ተጋርተዋል። “ሠላማዊ ትግል ብዙ ደረጃዎች አሉት ያሉት ዶክተር መረራ ጉዲና ይህንን ሰፊ እና ጥልቅ የትግል መስመር አሟጠን እየተጠቀምንበት ግን አይደለም” ሲሉ አምነዋል፡፡ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጹን ለተቃዋሚዎች ከመስጠት ባሻገር የሰጠውን ድምጽም ከነጣቂና ከዘራፊ ለመጠበቅ ገዢው ፓርቲን በያዝከው መሣሪያ ድምፃችንን መስረቅና መንጠቅ የለብህም፤ ያወጣኸውን ሕገ-መንግሥት አክብር ማለት አለበት” ሲሉም አሁን መደረግ አለበት ያሉትን ጠቁመዋል።
“በ2002 የምርጫ ውጤት ተስፋ አልቆረጣችሁም ወይ ተብለው?” በሚል የተጠየቁት ዶክተር መረራ በቀልድ መልክ ፈገግ ብለው “እኛ ተስፋ ብንቆርጥም ኢህአዴግ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሥራ አይሰራም፡፡ ህብረተሰቡን በሙሉ ቀን ከለሊት በኢፍትሃዊነትና በግፍ እያጨናነቀ እየጨቆነ ተስፋ እንዳንቆርጥ እያነቃቃን እንገኛለን” ብለዋል፡፡ “በተቃዋሚዎች ዘንድም ኢህአዴግ እኛን የሚያዳክሙለት የሚቀልባቸው ታማኝ ተቃዋሚዎች አሉት፤ ቀን ቀን ከእኛ ጋር ይውላሉ፣ ማታ ማታ ደግሞ ኢህአዴግ ኪስ ውስጥ ያድራሉ ብለዋል” ዶክተር መረራ፡ አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው መድረክ ወደ ምርጫ ሲገባ የተወሰኑ ስትራቴጂዎችን መሥራቱን አስታውሰው ወደ ምርጫው ከመገባቱ በፊት መንግሥትን ቅድመ ሁኔታ ጠይቆ ነበር፤ ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ባለመቀበሉ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ “ይህ ባይሳካና ሁኔታው እጅግ ፈታኝ ቢሆንም እንኳ ከምርጫ መውጣት አልነበረብንም” ያሉት አቶ ገብሩ፤ ምክንያቱን ሲያብራሩም “ከፖለቲካው ጨዋታ መውጣት ትግሉን ወደ መቃብር ማውረድ ይሆናል” ብለዋል።
መድረክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ መገምገም ያለበት ባለው ጊዜ፤ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ የፖለቲካና ማህበራዊ ሁኔታ አንፃር እና ከገዢው ፓርቲ ባህሪ አንፃር እንደሆነ አቶ ገብሩ አስረድተዋል፡፡ “መድረክ ኢህአዴግን ያስደነገጠና ያደናበረ ፓርቲ ነው፤ ለዚህም ነው ኢህአዴግ መድረክ ላይ ጦርነት በጠዋቱ ያወጀውና አባላቱን ከገጠር እስከ ከተማ በደህንነትና በፀጥታ ኃይሎች እያዋከበ፣ እያሰረና እየገደለ የነበረው”ያሉት አቶ ገብሩ “መድረክ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ሕይወት ገብሯል፡፡
በአንዳንድ የምርጫ ክልሎች ቦንብ የተወረወረባቸው አካባቢዎችም አሉ” ሲሉ መድረክ እየሰራበት ነው ያሉትን ምህዳር ገልጸዋል፡፡ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው “ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ማግስት ጀምሮ ኢህአዴግ በህዝባችን ላይ ከፍተኛ ደባ በመፈጸም ላይ ይገኛል፤ በመሆኑም ለነፃነት የሚደረግ ትግል ማቆሚያ ስለሌለው የተሻለ ለመሥራት በመጣር ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡ “መድረክ ተስፋ የሚቆርጥ ፓርቲ አይደለም” ሲሉም ጥምረቱ ወደፊትም ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። መድረክ በአዲስ አበባ ያካሄደውን ተመሳሳይ ውይይት በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በባህር ዳር እና በመቀሌ ለማካሄድ እቅድ አለው፡፡