በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የወያኔ አገዛዝ በወገኖቻችን ላይ እየፈጸመ የሚገኘውን ሽብር በመቃወም በየሃገሩ ሰላማዊ ሰልፍ እያዘጋጁ መሆኑ ታወቀ

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በወገኖቻችን ላይ የጀመረውን የእሥር ዘመቻ ለማስቆምና ሽብርተኝነትን በመከላከል ሥም በአገዛዙ እየተካሄደ ያለውን መንግሥታዊ ሽብር ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማሳወቅ ኢትዮጵያዊያኑ በየሚኖሩበት የምዕራብ አገሮች ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እያካሄዱ መሆኑን ወደ ዝግጅት ክፍላችን እየደረሱ ያሉ መረጃዎች አመለከቱ።

ባለፈው ሰኞ በአሜሪካን አገር ስቴት ዲፓርትመንት ፊት ለፊት የተጀመረው የኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ፤ በነገው ዕለት መስከረም 19 ወይም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ስብተምበር 30 በስዊድን ስቶክሆልም እንዲሁም ከወያኔ አገዛዝ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላት የእንግሊዝ ዋና ከተማ ሎንዶን የፊታችን እሁድ መስከረም 21 ወይም ኦክቶበር 2 እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሎአል።

ከዚህ በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ፤ በአውስትራሊያና በአውሮጳ የተለያዩ ከተሞች ተመሳሳይ የሆነ የተቃውሞ ሰልፍ እየተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ የየአገሮቹ መንግሥታት ወያኔ በጸረ ሽብርተኝነት ዘመቻ ሥም ህዝባዊ ተቃውሞን ለመደፍጠጥ በወገኖቻችን ላይ እየፈጸም ያለውን እስር፤ ግርፋትና ግዲያ እንዲገነዘቡ ለማስቻል ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በተጓዳኝ እየተካሄደ መሆኑ ታውቆአል።

ይህ በዚህ እንዳለ ባለፈው ሰኞ ከአሜሪካን አገር ስቴት ዲፓርትመንት ፊት ለፊት በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት የዲሞክራሲ አክቲቪስት ታማኝ በየነ፤ የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ኤፍረም ማሉቦና ወጣቶችን በመወከል ንግግር ያደረገች አንዲት ሴት ታጋይ የወያኔ የመከራና የግፍ አገዛዝ እንዲያበቃ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ላሉ ኢትዮጵያዊያን ጥሪ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሎአል። አርቲስት ታማኝ በየነ ባደረገው ንግግር አገራችንን ለመበታተን ታላቅ አደጋ የጋረጠውን የወያኔ አገዛዝ ከሥልጣን ለማውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ህዝባችንን ቀስፎ የያዘው የፍርሃት መንፈስ ይገረሰስ ዘንድ ሁሉም በራሱ ላይ ዘመቻ መክፈት እንዳለበት አስታውቆአል። አገር ውስጥ ያሉ የዲሞክራሲ ታጋዮች በወያኔ እስር ቤት የሚፈጸምባቸውን ሰቆቃ ከመጠፍ ሳይቆጥሩ እየተጋፈጡ ባሉበት ፤ እነ እስክንድር ነጋና አንዱአለም አራጌን የመሳሰሉ እምነታቸውን በአደባባይ እየተናገሩ ባለበት በአሁኑ ሰዓት በተለይ በውጪ የምንገኘው ኢትዮጵያዊያን ለወያኔ ማስፈራሪያና ዛቻ ቦታ መስጠት እንደማይኖርበን ተናግሮአል።

የግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በበኩላቸው ህጻን ከሽማግሌ ሳይለይ በህዝባችን ላይ ሰቆቃ እየፈጸመ ያለው ይህ ዘረኛ አገዛዝ በአስቸኳይ ካልተወገደ በቀር መዘዙ የከፋ መሆኑን ለማስረዳት፤ ድህረ ምርጫ 97 ወላጆቹ በተፈጸመባቸው እስር ምክንያት እስር ቤት የተወለደው የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ሰርካለም ፋሲካ የ5 አመት ህጻን ልጅ፤ የአባቱ አሳሪዎች የብረት ካቴና እጁ ላይ ሲያስገቡ ምርር ብሎ ሲያለቅስ ርህራሄ የሌላቸው የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ ፖሊሶችና ፊልም ቀራጮች እንደመዝናኛ ፊልም ተረጋግተው የቀረጻ ተግባራቸውንና የጭካኔ ድርጊታቸውን ሲፈጽሙ መታየታቸው ሊኖረው የሚችለውን መልዕክት ምን እንደሆነ ሁሉም ልብ ሊለው እንደሚገባ ካስገነዘቡ ቦኋላ ከወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት የምንችለው እያንዳንዳችን እስከ ህይወት የሚደርስ መስዋ ዕትነት ለመክፈል ስንችል ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል።