አሸባሪው፣ ዘረኛና አምባገነን የወያኔ አገዛዝ በሽብርተኝነት ስም እየፈጸመ ያለው የጅምላ እስራት ስርአቱ የራሱን መቀበሪያ ጉድጉአድ እየቆፈረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ተባለ
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ንጹሃን ዜጎችን ሽብርተኞች ናችሁ በማለት የጀመረው የጅምላ እስራት፣ የአምባገነኑ ስርአት ማብቂያ ዋዜማ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን አገዛዙ እየፈጸመ ያለው ድርጊት ደግሞ የራሱን መቀበሪያ ጉድጉአድ እየቆፈረ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው በማለት በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለዘጋቢያችን ገለጹ::
እንደዘጋቢያችን ሪፖርትና በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች በመዘዋወርም ያነጋገራቸው በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት የወያኔ ኢህአዴግ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚፈልገውን ግፍ ሁሉ ፈጸመ፣ ኢትዮጵያዊያንን በርሃብ አለንጋ ቀጣ፣ ለሞትና ለስደት ዳረገ:: ይህ ሁሉ አላረካው ሲል ደግሞ ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ያሉ ንጹህና ውድ ኢትዮጵያዊያንን ተራ በተራ ወደ ቃሊቲና ሌሎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የሚገኙ እስር ቤቶች ሽብርተኞች ናችሁ እያለ አጎረ:: ይህን ሁሉ እየፈጸመ ያለው ቀደም ብሎ በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈለገውን በደል ሲፈጽምና የፈለገውን እንዳሻው ሲያደርግ ኢትዮጵያዊያኑ ቁጣቸው ባለመቀስቀሱ የት ትደርሳላችሁ በሚል ንቀት እንደሆነ ገልጸው አሁን የጀመረው ዘመቻ ግን እጅግ በርካቶችን ያበሳጨ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንም በያዝነው አመት ወያኔን ፍጹም በሆነ ወኔ እንዲፋለሙ ያዘጋጀ ነው:: እናም እየፈጸመ ያለው ድርጊት ደግሞ የራሱን መቀበሪያ ጉድጉአድ እየቆፈረ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::
የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱአለም አራጌ፣ የኦፌዴን ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦህኮ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንንና አቶ አሳምነው ብርሀኑ፣ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፣ ጋዜጠኛ ርዮት ዓለሙ፣ ጋዜጠኛ ስለሽ ሐጎስ እንዲሁም አርቲስት ደበበ እሸቱ የአምባገነናዊው ዘረኛ ሥርዓት ጅምላ እስራት ሰለባ ከሆኑት ጥቂቶቹ መሆናቸው በተለያዩ የዜና አውታሮች ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል::
ይህ በንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ባለፈው ቅዳሜ በቅርቡ በ”ሽብርተኝነት” ስም እየታሰሩ ያሉትንና በሠላማዊ ትግልና በጋዜጠኝነት እየሠሩ ያሉትን ግለሰቦች አስመልክቶ ”በሽብርተኝነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!” በሚል ርዕስ መግለጫ አውጥቷል። መድረክ በመግለጫው ታሳሪዎቹ በሀገሪቱ በሚደረገው ፈታኝ ሠላማዊ ትግል ውስጥ በሕገ-መንግሥቱ ጥላ ስር ግንባር ቀደም ተዋናይ የሆኑ ፖለቲከኞችና ሞያዊ ግዴታቸውን አክብረው ለህዝብ ትክክለኛና ያልተዛባ መረጃ ለማድረስ የሚተጉ ጋዜጠኞች መሆናቸውን መድረክ አጥብቆ እንደሚያምን ገልጿል። በማያያዝም ወያኔ ኢህአዴግ በሽብርተኝነት ወንጀል ስለመታሰራቸው በመገናኛ ብዙኀን ፕሮፖጋንዳ ሲያሰራጭ እንጂ ስለፈፀሙት የሽብር ተግባር ተጨባጭ ማስረጃ ሲያቀርብ አለመታየቱን መድረክ ገልጿል።
መድረክ በመግለጫው ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤ የሁሉም የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች ሰብዓዊ-መብት መከበሩ በአስቸዃይ እንዲረጋገጥ፤ በፀረ-ሽብርተኝነት ሕግ ስም የሚደረገው የህዝብ መብት ረገጣና እስራት በአስቸዃይ እንዲቆም፤ ህዝብን አፍኖ ለመግዛት ታስቦ የተዘጋጀው “የፀረ-ሽብርተኝነት” አዋጅ ከበርካታ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሻር፤ እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ በወንጀል ተጠርጥሮ እስካልተፈረደበት ድረስ እንደወንጀለኛ ያለመታየት ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው ይታወቃል። በመሆኑም የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ፍርድ ባልተሰጠባቸው ዜጎች ላይ እንደተፈረደባቸው ወንጀለኞች በመቁጠር የሚያሰራጩትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አሳስቧል። በመጨረሻም ”በሽብርተኝነት ስም የህዝብ መብቶችን ማፈን ይቁም!” ሲል መድረኩ ያለውን አቋም ገልጿል።