አሜሪካ ለመለስ ዜናዊ ሽብርተኛ አገዛዝ የምትሰጠውን ድጋፍ እንድታቆም በዋሽንግተን ዲሢና አካባቢዋ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በሠላማዊ ሠልፍ ጠየቁ

በምዕራባዊያን የገንዘብና የፖለቲካ ድጋፍ ህዝባችንን አፍኖና ረግጦ እየገዛ ያለው የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዜጎቻችን ላይ አጠናክሮ የቀጠለውን እስር በማውገዝ ቁጥራቸው በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በትናንትናው ዕለት በአሜሪካን ስቴት ዲፓርትሜንት ፊት ለፊት ተገኝተው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ሪፖርተራችን ከሥፍራው በላከልን ዜና ገለጸ።

ሞት ለወያኔ-፤ ሞት ለጎጠኞች ፤ ሞት ለሽብርተኛው መለስ ዜናዊ፤ መለስ ዜናዊ ለፍርድ ይቅረብ፤ አሜሪካ ለፋሽስቱ መለስ ዜናዊ የምታደርጊውን እርዳታ እንቃወማለን፤ የቱኒዚያን፤ የግብጽና የሊቢያን ህዝብ ነጻ ያወጣው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ ይደገማል፤ ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን በከፈተኛ ቁጭትና እልህ ሲስተጋቡ እንደነበረ የገለጸው ዘጋቢያችን በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ለወያኔ ያላቸው ትዕግሥት የተሟጠጠ እንደነበር ያስተጋቡ ከነበረው መፈክር መረዳት ይቻላል ብሎአል።

ሰላማዊ ሰልፉን ያስተባበረው በሰሜን አሜሪካ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ድርጅት በአጭር ጊዜ በተዘጋጀው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እጅግ እንዳስደሰተው በመግለጽ ወያኔ በህዝባችን ላይ የሚፈጽመው ሽብር እስኪገታ ድረስ ተመሳሳይ ተቃውሞ ሰልፎችንና ህዝባዊ ስብሰባዎችን በማካሄድ በአገራችን የሚካሄደውን ፋሽስታዊ እርምጃ ማጋለጡን እንቀጥላለን ብሎአል።

ይህ በዚህ እንዳለ በአውስትራሊያ አገር በሜልቦርን ከተማ የሚገኝ “ዲሞክራሲ ለኢትዮጵያ የድጋፍ ኮሚቴ የተባለ ድርጅት “መለስ ዜናዊ አገዛዝ በንጽሗን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን የእስርና የአፈና እንግልት ለመቃወም ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን በሜልቦርን ከተማ የጠራው ህዝባዊ ስብሰባ በጋለ ስሜት መካሄዱን የደረሰን ዜና አመለከተ።

የስብሰባው ተሳታፊዎች ዘረኛው የመለስ አገዛዝ በህዝባችን ላይ እያደረሰ ስላለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በሰፊው ከተወያዩ በሗላ ህወሀት/ ኢህአዴግ በቅርቡ በግፍ ያሰራቸውን እነ አቶ እስክንድር ነጋ፤አንዱኣለም አራጌ፤ ዘመኑ ሞላ፤አሳምነው ብርሃኑ፤ ናትናኤል መኮንን፤ በቀለ ገርባ ፤ ኦልባና ሌሌሳ፤ ደበበ እሸቱ፤ እንዲሁም ሌሎች ጋዜጠኞች፤ ታዋቂ ሰዎች እና የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ የአለማቀፍ መንግስታትን ጠይቀዋል።

በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ በእስር ላይ ለሚገኙት ዜጎች ቤተሰቦች የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ህብረትሰቡን በማስተባበር ለማሰባሰብ በሙሉ ድምጽ ሲወስኑ ይህንንም የሚያከናውኑ ልዩልዩ ንኡሳን ኮሚቴዎችን ማዋቀራቸውን የደረሰን ዜና አክሎ አመልክቷል።