የህዝባችንን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየር ሲል የአባይን ወንዝ እገድባለሁ ብሎ የተነሳው ወያኔ ለግድብ ማሰሪያው የህዝብ መዋጮ አነስተኛ በመሆኑ የግል ባለሀብቶች እንዲሳተፉበት ጥሪ እንዳቀረበ ተዘገበ

የአባይ ግድብ የህዝብ አደራጅ ኮሚቴ ተብሎ የተቋቋመው ድርጅት ሀላፊ የሆነው በረከት ስምኦን ለብሉምበርግ እንደተናገረው ፣ የመንግስት ሰራተኛው ከደሞዙ እየቀነሰ የአባይን ግድብ ቦንድ እንዲገዛ መታዘዙ የሚያዛልቅ አልሆነም በማለት ቀደም ሲል ከፍተኛ የህዝብ መነቃቃት ታይቶበታል ተብሎ በወያኔና ተባባሪዎቹ ሚዲያ ሲራገብ የነበረውን ባዶ ፕሮፖጋንዳ አጋለጠ።

ላለፉት በርካታ ወራት ጠዋትና ማታ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ለግድቡ ማሰሪያ ገንዘብ እያዋጣ ነው እንዳልተባለ እስከዛሬ የተዋጣው 7 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነና ቀሪውን 80 ቢሊዮን ብር ለማግኘት የግሉ ክፍል እንዲሳተፍ ጥሪ መቅረቡን የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ ተቀጽላ የሆነው በረከት ተናግሮአል። በስልጣን ላይ ያላቸውን ቆይታ ለአንድ ቀን እስከአራዘመ ድረስ ህዝብ ፊት ወጥተው የሚናገሩት ውሸት ከማያሸማቅቃቸው አንዱ የሆነው በረከት ስም ዖን እንደተናገረው የግሉ ባለሃብቶች ካልተሳተፉ በቀር የግድቡን ወጪ ለመሸፈን አዳጋች እንደሆነ አልደበቀም።

አስተያየት ሰጪዎች ግን ይህን ግዙፍ ግድብ አለ ውጭ እርዳታ መስራት እንደማይቻል ገልጸው፣ ምናልባትም መስራት የሚችል የአገር ውስጥ የግድል ድርጅት ካለ የህወሀት ንብረት የሆነው ኢፈርትና አለሙዲ ናቸው ይላሉ።

ኢፈርትና የአላሙዲ ድርጀቶች በጋራ ግድቡን ሊያስጨርሱ እንደሚችሉ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፣ ይህም ቢሆን አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ሙሉ በሙሉ በሁለቱ ድርጅቶች እንዲገባና የአባይ ባለቤትነት የኢፈርትና የአላሙዲ እንደሚሆን እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
ከኢፈርት ና ከአላሙዲ ድርጅቶች ውጭ ያሉ የግል ድርጅቶች በሀይል ቦንድ እንዲገዙ የሚገደዱ ከሆነ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚገድለው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ይፋ የሆነው የአረቡን አለም አብዮት ጅማሮ ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል። የአባይ ግንባታ ፕሮጀክት የተጠበቀውን ያክል የህዝቡን ትኩረት ሊስብ አለመቻሉና የህዝቡን ምሬት መጨመሩ አገዛዙን ክፉኛ ያስደነገጠ መሆኑን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወቃል።