ሂውማን ራይትስ ወች የእንግሊዙን የልማት ሚኒስትር ወቀሰ
የአለማችን ጠንካራው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች የሆነው ሂውማን ራይተስ ወች ለእንግሊዙ የውጭ የልማት ትብብር ሚኒስትር አንዲሪው ሚቼል በጻፈው ደብዳቤ፣ ባለስልጣኑ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የውጭ እርዳታ ኢትዮጵያውያንን ለመጨቆኛነት መዋሉን ማረጋገጥ አልቻልም በማለት ለቢቢሲ የሰጡት ቃል ተአማኒነት የሌለውና ህዝብን ሆን ብሎ ለማደናገር የቀረበ ነው በማለት ወቅሷል።
ሂውማን ራይትስ ወች ለኢትዮጵያ የሚሰጠው እርዳታ ለተገቢው ህዝብ ከሚደርስ ይልቅ የመለስ መንግስት የፖለቲካ ደጋፍ መግዢያ ማዋሉን ለሚኒስትሩና በኢትዮጵያ ለእንግሊዝ አምባሳደር በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም፣ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ መቆየቱን አስታውሷል።
ሂውማን ራይትስ ወች፣ አንድሪው ሚቼል የእንግሊዝ መንግስት እርዳታ ለኢትዮጵያ መንግስት በቀጥታ አይደርስም ብለው የተናገሩት ፍጹም ተአማኒነት የሌለው ነው ካለ በሁዋላ፣ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው እርዳታ በቀጥታ የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚጠቀምበት የእንግሊዝ አምባሳደርም ሆነ የአሜሪካ መንግስት የሚያቁት ጉዳይ ነው ብሎአል።
እርዳታው ለክልል መንግስታት ቢሰጥም የክልል መንግስታትን በቀጥታ የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ነው የሚለው ሂውማን ራይተስ ወች፣ ገለልተኛ የመንግስት አካል እርዳታውን እንደሚቆጣጠረው ተደርጎ በአንድሪው ሚቸል የቀረበው አስተያየት ተገቢ ያልሆነና ፍጹም አሳሳች ነው።
ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው እርዳታ ውስጥ እጅግ በጣም ትንሹ ለምግብ እርዳታ ተብሎ የሚሰጠው መሆኑንና ይህም እርዳታ ችግር እንዳለበት አንድሪው ሚቸል መናገራቸው ተገቢ አለመሆኑን የገለጠው ሂውማን ራይተስ ወች፣ ከ7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሴፍቲ ኔት ወይም በመጠባበቂያ ምግብ እርዳታ፣ ከ7-10 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ ደግሞ በአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚኖር በመሆኑ እርዳታውን አሳንሶ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም ብሎአል። እንደ ሂውማን ራይተስ ገለጻ 20 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ በአንድም ይሁን በሌላ በውጭ እርዳታ የሚኖር ነው።
ሂውማን ራይተስ ወች የኢትዮጵያ መንግስት በአገሩ ምንም አይነት ምርመራ እንዲካሄድ እንደማይፈልግ የታወቀ ቢሆንም፣ እንግሊዝም ሆኑ ሌሎች መንግስታት ከግብር ከፋዩ ህዝባቸው የሚሰበስቡትን ገንዘብ እንዴት ሊቆጣጠሩት እንደሚገባ ከኢትዮጵያ መንግስት መመሪያ ሊቀበሉ አይገባም ብሎአል።
እንግሊዝን ጨምሮ ሁሉም አገሮች ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡት እርዳታ ህዝቡን ለመጨቆኛ እየዋለ አለመሆኑን ማረገጋጥ ይጠበቅባቸዋል ሲል አክሎአል።
ሂውማን ራይተስ ወች በመጨረሻም የእንግሊዝ መንግስት ወደ ገጠር ወርዶ በሂዋማን ራይተስ ወችና በቢቢሲ የቀረበውን ዘገባ ማጣራት ይጠበቅበታል ብሎአል።