በስዊድን የሚገኙ አትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ
ነዋሪነታቸው በስዊድን የሆኑ ኢትዮጵያውያን ትናንት መስከረም 19 ቀን 2004 ዓም በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም ከአገሪቱ ፓርላማ ፊት ለፊት ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ ወያኔ የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ሲል ያለአግባብ በእስር ቤት ያጎራቸው የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ሰልፈኞቹ በያዙዋቸው መፈክሮች መለስ ዜናዊ በዘጎች ላይ ለፈጸመው ፍጅት ለፍርድ ይቅርብ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ይሁን፣ መጻፍና መናገር ሽብርተኝነት አይደለም፣ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ይቁም፣ ህዝብ ለነጻነት የሚያደርገው አመጽ በመለስ አይታፈንም፣ አሸባሪው ርእዮት ሳትሆን መለስ ና አገዛዙ ናቸው ፣ አሸባሪው አንዱአለም ሳይሆን መለስ ነው ፣ አሸባሪው እስክንድ ነጋ ሳይሆን መለስ ነው ፣ ኢትዮጵያ የመለስ ዜናዊ እስር ቤት አትሆንም፣ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ትሆናለች የሚሉት ይገኙበታል።
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የአገሪቱ ጋዜጠኞች በብዛት መገኘታቸውን፣ የስዊድን የተለያዩ ፓርቲዎች አባላትና መሪዎችም መገኘታቸውን ዘጋቢያችን ከላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎአል።
በስዊድን የኢትዮጵያ ማህበር ተወካይ የሆኑት አቶ ግሩምጌታ ዘላለም እንዲህ አይነቱን የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የተፈለገው የታሰሩ ፖለቲከኖችና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ለመጠየቅ ነው በማለት በአገራችን ፍትህ እስኪከበር ና ዜጎች የአገራቸው ባለቤት መሆን እስኪችሉ ድረስ ኢትዮጵያዊያኑ ጸንተው መታገል እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰላምዊ ሰልፉ ላይ በስዊድን የአንድንት ፓርቲ የድጋፍ ኮሚቴ ስብሰቢ ንግግር እንዳደረጉና ግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ የላከው የጽሁፍ መልዕክት በንባብ መሰማቱ ተያይዞ በደረሰን ዜና ተመልክቶአል።
በመጨረሻም ሰልፈኞቹ ለሲዊድን ፓርላማና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የጻፉት ማመልከቻ በሰልፉ ተወካዮች አማካይነት ለማለስልጣናቱ መሰጠቱ ታውቆአል።