ለመስከረም 21 ሰላማዊ ሠልፍ በመጥራታቸው ከታሰሩት አንዱ የሆኑት አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ ከወያኔ አቃቤ ህግ ጋር ፍርድ ቤት ተብየው መድረክ ላይ መወዛገባቸው ተሰማ

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ አለኝ በማለት በሚኩራራው ህገ መንግሥት በመተማመን ለነገ መስከረም 21 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ወስጥ የሚካሄድ ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት ሲንቀሳቀሱ በወያኔ ደህንነትና ፖሊስ ተይዘው እስር ቤት ከተወረወሩት የሰላም ታጋዮች መካከል አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ፣ ወጣት ተስፋሁን አናጌ፣ ወጣት ታምራት ሻማና ሌሎች ከእነሱ ጋር የታሰሩ 3 ግለሰቦች በትናንትናው እለት ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበር የግንቦት 7 ዘጋቢ ከአዲስ አበባ በላከልን ዜና ገለጸ።

ታሳሪዎቹ ወያኔ የፖለቲካ ባላንጣዎቹን ሞራል ለመስበርና ለመቅጣት በሚገለገልበት ፍርድ ቤት ተብዬው ሲቀርቡ ለሆዳቸ ያደሩና የባንዳነት ተግባር በማከናውን የ ዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑ አቃቤ ህጎች ፤ ግለሰቦቹ የተያዙት በውጭ አገር ከሚገኙ አሸባሪ ድርጅቶች ጋር በመሆን መስከረም 21 ቀን 2004 ዓም ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ወረቀት ለመበተን ሲዘጋጁ እጅግ ከፍንጅ ተይዘዋል የሚል ክስ እንደመሰረቱባቸው ሲገልጽ ችሎት ተብዬው ቦታ ላይ የተሰየመቺው ሴት ዳኛ በአቃቢ ህጉ የቀረበውን ክስ አምናችሁ ትቀበላላችሁ ወይስ ትቃወማላችሁ በማለት ጥያቄ አቅርባ እንደነበር የደረሰን ዜና አመልክቶአል።

ከዚያ ቦኋላ አቶ ክንፈሚካኤል ብድግ ብለው፣ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እርሳቸውና አብረዋቸው የታሰሩት በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ መደብደባቸውን፣ እግራቸው ወደ ላይ እራሳቸው ወደ መሬት ተዘቅዝቆ በግንድ ላይ ታስረው መገረፋቸውንና ዘርን የሚያንቋሽሽ ስድብ መሰደባቸውን በመግለጽ፣ አብረዋቸው የታሰሩት በሙሉ ንጹሀን ሰዎች በመሆናቸው ሀላፊነቱን እርሳቸው እንደሚወስዱ በድፍረት በመናገር የዳኛዋንና አቃቤ ህግ ተብዬዎችን ቅስም መስበር መቻላቸውን ሂዴቱን የተከታተሉ ምንጮች ለዘጋቢያችን አስረድተዋል።

ዳኛዋ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ሳታገኙ ለምን ወረቀት ማባዛት ውስጥ ገባችሁ በማለት ላቀረበቺው ጥያቄ ፣ አቶ ክንፈ ሚካኤል በድፍረት በህገ መንግስቱ መሰረት አንድ ሰለማዊ ሰልፍ በ48 ሰአታት ውስጥ ፈቃድ ካልተሰጠው እንደተፈቀደ ይቆጠራል፣ እኛም በተደጋጋሚ ወደ ከንቲባው ኩማ ደመቅሳ ብንሄድም መልስ ሊሰጠን አልቻለም፣ ስለዚህ ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረናል በማለት መመለሳቸው ታውቆአል።

አቃቢ ህግ ከውጭ አገር ገንዘብ ተቀብለዋል ለሚለው ክስ አቶ ክንፈ ሚካኤል ሲመልሱ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም ፓርቲ በራሱ ገንዘብ አይንቀሳቀስም፣ ፓርቲዎቹ ደሀ ናቸው ስለዚህ ከኢትዮጵያውያኑ ገንዘብ መቀበል የተለመደ ነው፣ እንኳንስ እኛ ኢህአዴግም ገንዘብ ይቀበላል በማለት አገዛዙን አንገት የሚያስደፋ ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ክንፈ ሚካኤል፣ ሌሎች እስረኞች በማያዉቁት ጉዳይ መታሰራቸውን ገልጸው፣ እነርሱ እንዲፈቱና እርሳቸው ሀላፊነቱን እንዲወስዱ ፍርድ ቤት ተብዬውን ጠይቀዋል። ከዚያ ቦሃላ እንደተለመደው እስረኞቹን ለማሰቃየት ሌላ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶ የ ዕለቱ የፍርድ ቤት ድራማ ተተናቆአል።

በወያኔ የሰሞኑ ዘመቻ በሽብር ተጠርጥረው የተያዙት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በመላ አሰቃቂ የሆነ ድብደባ ሳይፈጸምባቸው እንዳልቀረ የደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።