ረሃብ ጊዜ አይሰጥም!! ወገኖቻችንን ለመታደግ፣ ወያኔን ለማስወገድ እንጣደፍ

የግንቦት7 ርዕሰ አንቀጽ ቁጥር 75 ላይ ወጥቶ የነበረ

“ለስድስት ተከታታይ ዓመታት ከአስር በመቶ በላይ የኢኮኖሚ እድገት አሳይተናል” የሚለው ዓይን ያወጣ ውሸት፤ “ድህነትን ተረት እናደርጋለን” የሚለው ጉረኛ መፈክር፤ የወያኔዎችና ጀሌዎቻቸው በፎቅና ቪላዎች መንበሽበሽ፤ ለም መሬቶች በአበባ እርሻዎች መተካታቸው እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ራድዮ ”የህዳሴ ብስራቶች” ለሕዝባችን ምሳና እራት አልሆኑም።

የረሃቡ ስጋት እየገፋ ሲመጣ መለስ ከአፄ ኃይለሥላሴም ሆነ ከኮሎኔል መንግሥቱ በባሰ ተፈጥሮ ላይ ማላከኩን ተያይዞታል። ለመሆኑ ተፈጥሮ ብቻውን እየተደጋገመ ለሚመጣ ችጋርና ቸነፈር በቂ ምክንያት ሆኖ ያውቃልን? ለምንድነው ፍትህና ነፃነት በሰፈነባቸው አገሮች ውስጥ ዝናብ ጠፍቶ የእርሻ ምርት ቢቀንስ እንኳን ሰው በረሃብ የማይሞተው? አስከፊ የረሃብ ዜናዎች የሚሰማባቸው አገሮች በሙሉ ነፃነት የታፈነባቸው አገሮች መሆናቸውስ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው? የዝናብ እጥረት ለኢትዮጵያዊ ገበሬ አዲስ ነገር አይደለም። ለምንድነው አንድ ዓይነት ችግር እየተደጋገመብን መላ መፈለግ ያቃተን? “ችግር የመሳካት እናት ናት” የሚለው ብሄል ምነው እኛ ዘንድ አልሰራ አለ? የመጨረሻው ጥያቄ መልስ አጭርና ቀጥተኛ ነው። ችግር የመሳካት እናት የምትሆነው በነፃነት ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ሲኖር ነው።

በባርነት ጨለማ ውስጥ ያለ ጭንቅላት ለችግሮች መፍትሄ የማፍለቅ አቅም የለውም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ድኩም ጭንቅላት ችግሮችን ማሸነፍ ሳይሆን ተሸናፊነትን ተቀብሎ ከችግሮች ጋር ተስማምቶና ተወዳጅቶ መኖርንይመርጣል። ለዚህም ነው የአስተዳደር በደልና ረሃብ ምክንያትና ውጤት ብቻ ሳይሆን እጅና ጓንትም ጭምር የሆኑት። ነፃነት ያለው ሕዝብ ረሃብን እንደሚያሸነፍ ተደጋግሞ የታየ ጉዳይ ነው _ ህንድ የቅርብ ጊዜ ምሳሌያችን ነች። ለዚህም ነው ረሃብን የተፈጥሮ ሚዛን መዛባት ውጤት ብቻ አድርጎ ማቅረብ እውነትን መሸፈጥ የሚሆነው። ረሃብ የብልሹ አስተዳደር ውጤት ነው።

በአገራችን ውስጥ የተንሰራፋው ስር የሰደደ ድህነትና ረሃብም የዘመናት የብልሹ አስተዳደር ውጤቶች ናቸው። ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የነበረው ብልሹ የምጣኔ ሃብት አስተዳደር አገዛዝ በተቀየረ ቁጥር እየባሰበት መጥቷል። በረሃብ የሚጠቃው ሕዝብ ብዛትም እንደዚያው እየጨመረ መጥቶ ዛሬ 14 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ ፈላጊ ሆኗል። ችጋር አድማሱን አስፍቶ ቀድሞ በለምለምነታቸው ብቻ ይታወቁ ወደ ነበሩት የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ መንደሮችም ዘልቋል። አገራችንን የረሃብ ቀጠና ካደረጉ የ19 ዓመታት የወያኔ “የዘርፈህ ብላ” የኢኮኖሚ ፓሊሲ ውጤቶች መካከል አንዳንዱን ለአብነት ያህል መዘርዘር ይቻላል።

  1. የወያኔ ቁንጮዎች ራሳቸውን ባለሚሊዮኖች አድርገዋል። እነዚህ በአንድ ጀምበር የበቀሉ ቱዳሮች ከገንዘብ በተጨማሪም የጄኔራልነት፣ የሚኒስቴርነት፣ የክልል ገዢነት፣ እጅግ ቢያንስ የቢሮ ኃላፊነት ሥልጣንን ኪሳቸው ውሰጥ ከተዋል። የመንግሥት ሥልጣንና ሃብት ይኸን ያህል የተቆራኙበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። የጥቂቶች ያለአገባብና ያለቅጥ መክበር በአንፃሩ ደግሞ የብሃኑን ሕዝብ መደህየት ድህነትን ቀጣይ ያደርጋል።
  2. በአቋራጭና በፍጥነት ለመክበር አስተማማኙ መንገድ የገዛ ራስ ጥረትና ታታሪነት ሳይሆን ቅጥፈት፣ አጭበርባሪነትና ሎሌነት ማደር መሆኑን በተግባር ወያኔ እያሳየ ጥሮ ማደርን “ኋላ−ቀር አሠራር” አድርጎታል። በዚህም ምክንያት አድርባይነት፣ ስንፍናና እና ልመና ችግርን የመጋፈጥ አቅማችንን ሰልበውታል።
  3. ደኖቻችን ተጨፍጭፈው፣ ለም መሬታችን ተሸርሽሮ በማለቁ የግብርናችን ምርታማነት በእጅጉ ቀነሷል። በዘመነ ወያኔ የደን ጭፍጨፋና የመሬት መሸርሸር በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል። አገሪቷ በፍጥነት ወደ ምድረበዳነት እየተቀየረች ነው።
  4. ገበሬና መሬት ተለያይተዋል፤ አዳዲሶቹ ባላሃብቶች ለፈጣን ኪስ መሙላት እንጂ ለዘለቄታ የአፈር ልማት ፍላጎቱም እውቀቱም የላቸውም። ለም መሬቶች በኢንቨስትመንት ስም በዘመኑ የወያኔ ጉልተኞች በመያዛቸውና እነሱ ደግሞ በተራቸው ለባዕዳን እየሸጡ በመሆኑ ባለሃገሩ ጭሰኝነት እንኳን አጥቶ ለቀን ሠራተኝነትና ልመና ተዳርጓል። በዚህም ምክንያት ገበሬው እንኳንስ ትልቁን የአየር መዛባት ትንሿንም የዋጋ ነውጥ መቋቋም እስከማይችልበት ደረጃ ተዳክሟል።
  5. በዘር በተመሰረተ ክልላዊ ድንበር ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች በአገራቸው ውስጥ ተዘዋውረው መሥራት አልቻሉም። ከሰሜን ወደ ደቡብ ከተሰደደ የአገራችን አርሶ አደር ይልቅ ለቻይና ገበሬ መሬት ማግኘት ይቀለዋል። እንዲያውም ኢትዮጵያዊው ገበሬ በዱላ ሲባረር፤ የቻይናው ገበሬ ብድርና ማበረታቻዎች ይሰጠዋል።
  6. ኢትዮጵያዊያን ገበሬዎች ድርቅን መቋቋም ስለሚችሉ ሰብሎች ወይም የአስተራረስ ዘዴዎች ማሰብ፣ መመራመርና መፈተሽ አይችሉም። አዲስ ነገር መሞከር የግብርና ፓሊሲን በመቃወም ወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ነው። ፈጠራ በእንዲሀ ዓይነት ሥርዓት ውስጥ አያድግም።
  7. ፋይዳ ያለው የስነ ሕዝብ ፖሊሲ ባለመኖሩ የሕዝብ ብዛት አሻቅቧል። እንደ ኢኮኖሚው ሁሉ ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት ሊቆጣጠር የሚሞክረው ቢሮ ውስጥ ቁጭ ተብሎ በሚደረግ የቁጥር ምርጫ ነው። የስታተስቲክሱ ባለሥልጣን ቁጥራችንን በትክክል ሊነግረን ባይፈልግም እንኳን ረሃብ መብዛታችንን እየነገረን ነው።

እነዚህና የመሳሰሉት ጭብጦችን በማንሳት የረሃቡ መሠረታዊ ምክንያት ወያኔ እንጂ ተፈጥሮ አለመሆኑን አስረግጠን እንናገራለን። ሕዝባችን በነፃነት ማሰብ፣ መመራመር፣ መፈተሽ ቢችል ኖሮ ረሃብን ማጥፊያ ብልሃት ማግኘት ባላቃተውም ነበር። ወደፊትም ቢሆን ተፈጥሮ እኛ እንደፈለግናት አትሆንም፤ መተማመኛችን የሰው ልጅ ወሰን የለሽ የፈጠራ ችሎታና ችግሮችን የመፍታት አቅም ነው። ለዚህ ችግሮችን በልጦ መገኘት ያስፈልጋል። ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሌ ከችግሮች በታች ሆኖ የእሱን ፈቃድ እንዲያሟላ ይፈልጋል፤ ለዚህም ነው ባርነትን ያወጀብን። እኛ ደግሞ የችግሮቻችን ቁንጮ ራሱ ወያኔ ነው የምንለው ለዚህ ነው። ወያኔን ሳናስወግድ ድህነትንና ረሃብ እናስወግዳለን ማለት ዘበት ነው::

ድህነት የወያኔ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ስለመሆኑ በዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ያነሳነው ጉዳይ ነው። ረሃብና ችጋርም እንደዚያው የወያኔ “ጪስ አልባ” እንዱስትሪዎች ናቸው። ሕዝባችን ተራበ ማለት የወያኔ ኩባንያዎች ሥራ አገኙ ማለት ነው። ወያኔ የራሱን “መንግሥታዊ ያልሆኑ” ድርጅቶች የማጠናከርና ገለልተኞቹን የማቀጨጭ ሥራ የጀመረው አራት ኪሎ እንደደረሰ ቢሆንም ረሃቡ በጨመረ መጠን እሱም “ገበያውን” ብቻውን ለመቆጣጠር የሚያደረገው ልብ ይሏል።

ረሃብ ያለፉት ሶስት ተከታታይ አገዛዞች የባህሪይ ተመሳሳይነትንም አጉልቶ አሳይቶናል። የሶስቱም አገዛዞች ቁንጮዎች ሰለረሃብ ተጠይቀው የሰጡት ትዕቢት የተሞላበት ምላሽ በሚገርም መጠን ተመሳሳይ ቢሆኑም የመለስ ግን ከሁሉ ይብሳል። መለስ ከቀደሙት ሁለቱ በባሰ እየለመነ ይሳደባል፤ እየተሳደበ ይለምናል። ስለ ኢኮኖሚ እድገት ሰፊ ገለፃ ከሰጠ በኋላ ንግግሩን በእርዳታ ልመና ይደመድማል። በመለስ አመክኖ ተፈጥሮ፣ ለጋሽ አገራት፣ የእርዳታ ድርጅቶች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለረሃቡ ተጠያቂ ናቸው። እውነታው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። ለወገኖቻቸን መራብ ተጠያቂው ወያኔ ነው። ወያኔን ሳናስወግድ ድህነትና ረሃብን ከኢትዮጵያ ምድር መንቀል አንችልም።

በወያኔ አገዛዘ በረሃብ ለሚጠቃው ወገናችን መድረስ የምንችለው፤ የረሃቡን መሠረታዊ ምክንያት የሆነውን የወያኔን አገዛዝ አስወግደን ፍትህና ነፃነት የሰፈነባትን፤ ፈጠራ የተስፋፋባትን ኢትዮጵያን ስንገነባ ብቻ ነው። ጊዜ የለም …. ረ ሃ ብ ጊ ዜ አ ይ ሰ ጥ ም ። የወገኖቻቸንን ሕይወት ለመታደግ በአንድነት እንነሳ።

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!