የመለስ አገዛዝ ሰድቦ ለሰዳቢ ሰጠን

በአለፈው 2003 መጨረሻ አካባቢ የብርታኒያ የዜና አውታር (ቢቢሲ) የምርመራ ጋዜጠኞቹን በስውር ወደ ኢትዮጵያ ልኮ እንደነበር ይታወሳል። ጋዜጠኞቹ በኦጋዴን፣ በባሌ፣ በወላይታ፣ በደቡብና ምዕራብ ኦሮሚያ እና አዲስ አበባ በመዘዋወር ከታዘቡት ውስጥ ጥቂቱን በነሐሴ ወር ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል።

በዚያም ጊዜ ባቀረቡት ዘገባ መሠረትም

  • የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን ሳይጨምር ለልማት እየተባለ ከምዕራባዊያን በየዓመቱ የሚጎርፈው 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማለትም አምሳ አራት ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር (ብር 54, 000, 000, 000) መለስ ዜናዊና ጭፍሮቹ እንደፈለጉ እንደሚያዙበት ማረጋገጣቸው፤
  • መለስን አልደገፉም የተባሉ ነዋሪዎች መሰረታዊ የሆኑ የምግብና የውሃ አቅርቦት እርዳታ መነፈጋቸውና በዚህም ምክንያት አዋቂዎች ሳይቀር በረሃብ መሞት መጀመራቸው ቦታው ድረስ በመሄድ በዓይኖቻቸው መመልከታቸውን፤
  • መለስን ያልደገፉ ገበሬዎች ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር እንደማያገኙ ከገበሬዎቹ አንደበት መስማታቸው፤
  • ወጣት ሴቶች ብቻ ሳይሆን በእድሜ የገፉ እናቶች፣ አያቶች፣ ነፍሰጡሮች ሳይቀር በወታደሮች መደፈራቸውን ከበደሉና ግፉ ቀማሾች አንደበት መስማታቸውና የተበዳዮችን ጠባሳዎች መመልከታቸው።
  • ሰቆቃ የተፈፀመባቸው፤ ተዘቅዝቀው የተሰቀሉ፣ ብልታቸውን የተኮላሹ ወንዶችን ማናጋገራቸው፤
  • በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ግፎች የሚፈፀሙ መሆኑ

በምስል በተደገፉ ማስረጃዎች አረጋግጠዋል።

ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የቢቢሲን ዘገባ ማፍረሻ ያለውን የተለመደውን ድራማ ሰርቶ ሲያደነቁረን ከረመ። ለጋዜጠኛቹ መረጃ የሰጡትን፤ በአስተርጓሚነት የአገለገሉትን ለቃቅሞ አሰረ፤ አንገላታ።

ይሁን እንጂ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሰቆቃ (ቶርቸር) እንደሚፈጽም እና የእርዳታ እህል ለፓለቲካ ተግባር እንደሚያውል አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንደሚያውቅ ዊኪሊክስ ከቢቢሲ ዘገባ በኋላ ይፋ ያደረጋቸው ሾልከው የወጡ መረጃዎች አረጋገጡ።

ቢቢሲ እነዚህን ተጨማሪ ነገሮችን ይዞ እንደገና ቀረበ። የአገሪቱ የውጭ ትብብር ሚኒስትር የሆኑትን ሚስተር አንድሬ ሚቸልን “ለእንዲህ ዓይነቱ መንግሥት እንኳንስ በመቶዎች ሚሊዮኖች እንዴት አንድ ፓውንድ እንኳን ይሰጣል?” ሲል ሞገተ።

በዚህ አጭር ሙግት ውስጥ ኢትዮጵያዊያንን ሊያሳስቡ የሚገቡ በርካታ ነገሮች ተሰምተዋል፤ ከትንሹ ጀምረን ወደ ትልቁ እንሂድ: –

  1. ተጠሪነቱ ለሚስተር አንድሬይ ሚሸል የሆነ የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ያለውን የእርዳታ አሰጣጥ ሥርዓት መርምሮ “በተቀናጀ መንገድ የእርዳታ እህል ለሌላ ተግባር እንደማይውል አረጋግጧል” አሉ። “የድርጅትዎ መርማሪዎች ገጠር ድረስ ሂደው መርምረዋል ወይ?” ተብለው ሲጠየቁም “አዎ ተቀማጭነታቸው እዛው ነው” አሉ። ሆኖም የልማት ሠራተኞቹ ምርመራውን ያካሄደቱ አዲስ አበባ ውስጥ ቁጭ እንደሆነ ቢቢሲ ሠራተኞቹን ጠይቆ ማረጋገጡ በፕሮግራሙ መዝጊያ ላይ አሳወቀ።
  2. ሚኒስትሩ “የእንግሊዝ የእርዳታ ገንዘብ ወደ መንግሥት ካዝና አይገባም። ከ1997 ወዲህ በቀጥታ መንግሥትን መደጎም ትተናል። እርዳታችንን በቀጥታ ለክልሎች ነው የምንሰጠው” ሲሉ ተሟገቱ – ከወሬ ባለፈ ክልሎች ያሉ ይመስል። ሁሉም-ጠቅላይ በሆነ አገዛዝ ውስጥ ገንዘብ ለማዕከል ተሰጠ ለክልል አሊያም ለወረዳ እምብዛም ለውጥ የሌለው መሆኑ እርሳቸው ያጡታል ብለን አናምንም።
  3. ሚኒስትሩ “በእንግሊዝ እርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጥረትን በግማሽ (50%) ቀንሰናል” አሉ። መለስ አመጣሁ እያለ የሚመፃደቅበት እድገት የእንግሊዝ እርዳታ ውጤት መሆኑ መናገራቸው መልካም ቢሆንም የሰጡትን ቁጥር ግን እንጠራጠራለን። እውን ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጥረት በግማሽ ቀንሷል? በምንስ ጋር ነው የተነፃፀረው?
  4. ከሁሉም አስከፊው ግን ምርጫን በሚመለከት የተናገሩት ነው። መለስ ዜናዊ 99.6% አሸነፍኩ ያለበት ምርጫ “ገለልተኛ ቡድን እንደገመገመው ምርጫው ፍጹም ነው ባይባልም እንኳን በአፍሪቃ ደረጃ ጥሩ ነበር፤ ከበፊተኛው ምርጫም የተሻለ ነበር” አሉ።

ሁሉም የሚኒስትሩ ምላሾች የሚያሳዝኑና የሚያስተዛዝቡ ቢሆንም የመጨረሻው ግን የሚያበግን ነው።

ለመሆኑ የአፍሪቃ ዲሞክራሲ መመዘኛ የተለየው በምን ምክንያት ነው? እንዲህ አሳንሰው የሚያይዋት አፍሪቃ ሰሜን አፍሪቃንም ይጨምራል ወይስ የጥቁርን ዘር ብቻ ነው? እንደምን የ2002ቱ “ምርጫ” ከ1997ቱ የተሻለ ነበር ይባላል። እነማናቸው እንዲህ ያሉት “ገለልተኞቹ” ገምጋሚዎች?

እንደሚታወቀው መለስ ዜናዊ የእርዳታ ጥገኛና ሱሰኛ ነው። በረሃ እያለ በአሸዋ የተሞሉ ጆንያዎችን ስንዴ ነው እያለ ሸጦ ባጋበሰው ገንዘብ እዚህ ደርሷል። አሁንም ነብሱ ያለችው በእርዳታ ነው። ከእርዳታ የዘረፈውንም የሚያስቀምጠው በእነዚሁ በለጋሾቹ አገር ነው። ይህንን ሁሉ የሚያውቅ ለጋሽ እንደምን ያክብረን?

መልዕክቱም ግልጽ ሆኖ፤ ጠልቆ ሊሰማን ይገባል። “ራሱን ያቀለለ አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” እንዲሉ በራሳችን ባርያ ፈንጋዮች እየተገረፍን እንደምን ባዕዳን ሊያከብሩን ኖሯል። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ራሱ የሚያደርስብን በደል ሳያንስ በዓለም አደባባዮችን ምን ያህል እንደተናቅንና እንደተዋረድን በየእለቱ የምናየው ሃቅ ሆኗል። ከዚህም አልፎ እነሆ የመንግሥታት ሹማምንትም ይፋዊ መግለጫ እየሆነ ነው? ምንድነው የምጠብቀው? እስከመቼ በመለስ አገዛዝ ክብራችን እንደዋረደ እንቆያለን? መለስ ሰድቦ ለሰዳቢ፤ ገርፎ ለገራፊ እንዲያቀብለን እንፈቅዳለንን? ወይስ መለስን ራሱን ከጫንቃችን አውርደን ክብራችንን እንቀዳጃለን? ምርጫው የእያንዳንዳችን ነው።

በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ውስጥ የተሰባሰብን ኢትዮጵያዊያን “በቃን!!!!” ብለናል። እርስዎስ?

በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!