የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ለተቃዋሚዎች

መጀመሪያ ጭብጨባ

አንድነት ፓርቲ በቅርቡ ተቃዋሚዎች/የተቃዋሚ ደጋፊዎችበቂ የመረጃ ምንጭ የላቸውም በማለት በየሣምንቱ ማክሰኞ፣ በ5 ብር ገበያ ላይ የምትውል ‹‹ፍኖተ ነፃነት›› የተሰኘች ጋዜጣ ማሳተም ጀምሯል፡፡ አንዱአለም አራጌሲናገር እንደሰማሁት ‹‹በጋዜጣዋ ላይ የኢሕአዴግ ደጋፊና አባላትም ቢሆኑ መጻፍ ይፈቀድላቸዋል፤ አንድነት እንደ ኢሕአዴግየመናገር ነፃነትን የማፈን ፍላጎት የለውም፡፡››

ከዚህ በተጨማሪም ፓርቲው በየሣምንቱ እሁድ ማለዳበተጋባዥ ምሁራን ጽሁፍ አቅራቢነትና በተሳታፊዎች መካከል የሚካሔድ የውይይት ፕሮግራም ጀምሮ ነበር፡፡ (የእነ አቶ አንዱአለምበ‹‹አሸባሪነት›› ተጠርጥሮ መታሰር ይህንን ጠቃሚ ልምድ እስከወዲያኛው ያስቀረው ይሆን?)
በሌላ በኩል (የኔ favorite ባይሆንም እንኳን) ኢዴፓ የዓለም ሊበራል ፓርቲዎችን ጉባኤ በ2004ዓ.ም. በኢትዮጵያለመጀመሪያ ጊዜ ሊያካሒድ ጎንበስ ቀና እያለ መሆኑ የሚያስመሰግን ነው፡፡ እንዲህ ሰበብ እየፈለግን የምናቆለጳጵሳቸው ተቃዋሚዎችግን በደመስማሳው ስንመለከታቸው መንግስት አንድ ውሳኔ ባሳለፈ ቁጥር የፕሮፓጋንዳ መግለጫ ከመስጠት ባሻገር (ያውም ከሰጡ)ባለፈው ምርጫ ካየናቸው በኋላ የት እንደገቡ ጠፍተዋል፡፡

ተቃዋሚዎች እና “ተቃዋሚዎች”
የተቃዋሚዎችን ትክክለኛ ቁጥር እንኳን እኔ የምርጫ ቦርድራሱ የሚያውቀው አይመስለኝም ነበር፡፡ ሆኖም የምርጫ ቦርድ ድረዓምባ (ከተጻፈ ቢሰነብትም)በሃገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ 79 ፓርቲዎችን እንደመዘገበ ነግሮናል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በሁለት ይከፈላሉ፤ተቃዋሚዎች እና “ተቃዋሚዎች” ተብለው፡፡ ነገር ቶሎ ለማይገባችሁ ሰዎች፤ “ተቃዋሚዎች” የሚባሉት እነሱ ተቃዋሚዎች ነን ስላሉእና ምርጫ ቦርድም ፓርቲ ናቸው ብሎ ስለመዘገባቸው ነው፡፡
“ተቃዋሚዎች” የምርጫ ሰሞን ብቻ አለሁ የሚሉና በእኔእምነት የተለየ አላማ ያላቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ገዢው ፓርቲ የተቃዋሚዎችን ድምጽ በመበታተን ለማሳነስ የሚፈጥራቸው ሲሆኑጥቂቶቹ ደግሞ በቤተሰብ እና በአካባቢያቸው ሙገሳ የሃገር መሪ የመሆን ምኞት ያደረባቸው ግለሰቦች የፈጠሯቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡
ደግነቱ የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አጀንዳ “ተቃዋሚዎች” ሳይሆኑተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ቢሆንም ግን ከዚያ በፊት Naming and Shaming የሚገባቸው የተቃዋሚ መሪ አሉ፡፡
Naming and Shaming
መኢብን ሲባል ሰምታችሁ ታውቁ ይሆናል፡፡ መላው ኢትዮጵያብሔራዊ ንቅናቄ የሚባለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡ መሪው አቶ መሳፍንት ሽፈራው ይባላሉ፡፡ ሰውየውን በፊት የምታውቋቸው ሰዎችካላችሁ አቶ መስፍን ሽፈራሁ ነበር ስማቸው፡፡ አንዴ ለአውራምባ ታይምስ በሰጡት ቃለ ምልልስ አንድ መስፍን ሽፈራሁ የተባለሰውዬ በታክስ ማጭበርበር ስሙ በቴሌቪዥን ስለተጠራ ደጋፊዎቻቸው ግራ እንዳይጋቡ ሲሉ ስማቸውን እንደቀየሩ ተናግረዋል፡፡
አቶ መሳፍንትን ከአራት ኪሎ እስከ ፒያሳ ደጋግሞየሚንቀሳቀስ ሰው አያጣቸውም፡፡ እኔም ደጋግሜ አገኛቸዋለሁ፡፡ አንድ ቀን ግን ያገኘሁዋቸውን ዓይነት አገኛኘት ባላገኛቸውይሻለኝ ነበር፡፡ እኔ ከቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ወደ አራትኪሎ ስወርድ እሳቸው እያሻቀቡ ተገጣጠምን፡፡ ማለዳ ነበር፤እርሳቸው ደግሞ የስፖርት ትጥቅ የሚመስል ታጥቀዋል፡፡ ጥድፍ፣ ጥድፍ እያሉ የነበረ ቢሆንም ለስፖርት አልነበረም፡፡ ከፊታቸውያለች አንዲት በእሳቸው ዕድሜ ክልል ያለችን ሴት ‹‹እየለከፉ›› ነበር፡፡ ዓይኔን ተጠራጥሬው ቆም አልኩ፡፡ ሁኔታቸውአረጋገጠልኝ፡፡ ሴቲቷ ጥላቸው ወደ ቤተክርስቲያኑ ስትገባ እርሳቸው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ (አሁን ይሄ በስም አጥፊነትያስከስሰኝ ይሆን? ለኢሕአዴግማ ጥሩ ሰበብ ነው፡፡)
ከሰሞኑ ከወጡ ጋዜጦች አንዱ ደግሞ የሚያስደምም ርዕስይዞ ነበር፡፡ “ተቃዋሚዎች” እና ኢሕአዴግ በአንድ መድረክ ሊመክሩ ሲያውጠነጥኑ መክረማቸው ይታወቃል፡፡ ታዲያ ጋዜጣው በዚህየምክክር መድረክ ላይ መኢብን ፕሮግራሙን እንዳላቀረበ ተናግሯል፡፡ በርዕሱ መኢብን ከኢሕአዴግ ጋር ተመሳሳይ ፕሮግራም ስላለውአጀንዳ አልያስያዘም ብሎን እርፍ፡፡ ታዲያ መኢብን የተለየ ፕሮግራም ከሌለው ለምን የኢሕአዴግ አባል አይሆንም፡፡ ኢሕአዴግእስካሁን ብሔር ተኮር ፓርቲዎችን ያሰባሰበ ፓርቲ አይደል? ምናለ ታዲያ ሕብረብሔራዊ የሆነውን መኢብንንም ቢያቅፈው?
ይሄዜና ግን አንድ ነገር ሳያስታውሰኝ አላለፈም፡፡ የመኢብን ሊቀመንበር፣ አቶ መሳፍንት በምርጫ 97 በግል ተወዳድረው ነበር (አዲስአበባ፤ ወረዳ 12/13) ምን ዋጋ አለው ያኔ ያዲሳባ ሕዝብ ቀልቡ ከቅንጅት ጋር ሸፍቶ ስለነበር ያስታወሳቸው የለም፡፡ ነገር ግንያኔም ቢሆን ኢሕአዴግ በጣት የሚቆጠሩ ታማኞች ነበሩት፡፡ ከታማኞቹ መካከል አንድ እኔ የማውቀውን የኢሕአዴግ ታማኝ፣ ገና ምርጫ97 በተጠናቀቀ በጥቂት ጊዜ ውስጥ አቶ መሳፍንት ፓርቲያቸውን ሲመሰርቱ አባል ያስፈልጋቸው ስለነበር ለመኢብን መፈረሙን ነግሮኛል፡፡አሁን ሲገባኝ እሱም የፈረመላቸው ለካ በፕሮግራማቸው መካከል ያለውን መመሳሰል አገናዝቦ ነበር?
ይህንን ርዕስ የተዋስኩት የፍትህ ጋዜጣው ተመስገንደሳለኝ በነሐሴ 20፤ 2003ዓ.ም. እትሙ ‹‹ፓርቲዎቹ [ተቃዋሚዎች] በህዝብ ዘንድ ካላቸው ታዋቂነት ይልቅ አመራሮቹ (በተለይሊቃነመናብርቱ) ያላቸው ታዋቂነት በብዙ እጥፍ በልጦ መገኘቱ››ን ከአተተበት ጽሁፉ ነው፡፡ አባባሉ ትክክል የሚሆነው በኢትዮጵያየተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ገንነው የወጡትን ፖለቲከኞች አመለካከት ከፓርቲያቸው ፕሮግራም የበለጠ የምናውቃቸው በመሆኑ ነው፡፡
አቶ ልደቱ ቅንጅትን በማተራመስና በቁርጥ ቀናት (ምርጫሲመጣ) ኢሕአዴግን በማሞካሸት እናውቃቸዋለን፡፡ ሆኖም ፓርቲያቸው ፕሮግራሙ ምን እንደሆነ የምናውቅ ሰዎች መኖራችን አጠራጣሪነው፡፡ እነ ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል፣ እነ ዶ/ር መረራ፣ እነ ፕ/ር በየነ ከፓርቲያቸው ይልቅ የራሳቸውን ስምና ዝና ገንብተዋልነው የሚለን ተመስገን፡፡
እኔ ደግሞ እላለሁ፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሶሻሊስትናቸው፡፡ ከኢሕአዴግ ፈንቅሎ ያስወጣቸውም ሶሻሊዝምን በነጭ ካፒታሊዝም ለመተካት የማሰቡ ነገር ነው፡፡ አሁን የት ናቸው?የካፒታሊዝም አቀንቃኝ የሆነው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ39 ‹‹በመርሕ ደረጃ›› ይቀበላሉ፤ ፓርቲው ይቃወመዋል፣ መሬት የመንግስት መሆኑን ይቀበላሉ፣ ይህንንም ፓርቲው ይቃወመዋል፡፡ እነዚህንዐቢይ ልዩነቶች እንዴት አቻቻሉት?
በርግጥ ፓርቲዎች በአስተሳሰብ አንድ የሆኑ ሮቦቶችስብስብ እንዲሆኑ አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን እንታገልለታለን የሚሉት ዐቢይ ጉዳይ ላይ ተቃራኒ ሐሳብ ያላቸውን ሰዎች ካቀፉሕልውናቸው አጠራጣሪ ነው፡፡
ከዚህም በላይ ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝግን ሌላ ምክንያት አለ፡፡ ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት ተቃዋሚዎች ለመቃወም ከመቃወም ሌላ ምን አጀንዳ አላቸው?
የአማራጭ ነገር
‹‹መንግስት ነጋዴውን እያዋከበ ነው፣ ነጋዴውንከሕብረተሰቡ ጋር ለማጣላት ፈልጎ ነው፡፡›› እያሉ ሲነግሩን የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠርና የአቅርቦቱን ነገር ለማሻሻል ምንመደረግ አለበት እያሉ ነው? የታክስ አሰባሰቡ ስርአት የተበላሸ እንደሆነ ሲነግሩን ነጋዴው ታክስ መክፈል የለበትም፣ ዝቅተኛነው መክፈል ያለበት፣ የሚያጭበረብር ነጋዴ የለም እያሉ ነው ወይስ ምን? በሌሎችም ዐብይ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲቃወሙአማራጫቸው ምን እንደሆነ ለምን አይነግሩንም? ነው ወይስ ኢሕአዴግ ፕሮግራሜን ይሰርቀኛል የሚል ‹የኮፒ ራይት› ስጋትአለባቸው?
በእኔ እይታ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያወቅታዊ ሁኔታ ተማርሯል፣ የገጠሩ ሕዝብ በረሃብ ከተሜውም በኑሮ ውድነት ውሎ ማደርን እንደስኬት እየቆጠረው ነው፡፡ በኢሕዴግለውጥ ያላመጣ የሩብ ምዕተ ዓመት የስልጣን ጉዞ ተሰላችቷል፣ በነፃነት እጦትና በፍርሃት ተወጥሯል፣ በአድሎአዊ አስተዳደር ውስጡበግኗል፡፡ ግን ደፍሮ አይናገርም፡፡ስለዚህ ደፍረው የሚናገሩትን ተቃዋሚዎች በትክክለኛው መንገድ ባይናገሩለትም ያወድሳቸዋል – የብሶቱ ተጋሪ ስለሚመስሉት ብቻ ይመርጣቸዋል፡፡ከበጣም ክፉ ክፉ ይሻለኛል ዓይነት፡፡ ስለዚህ ተበዳዩ ሕዝብ በድፍረታቸው ተደንቆ የተቀበላቸው ተቃዋሚዎች በሙሉ እኛ ነን ለሕዝቡየምናስፈልገው የሚል ትምክህት ላይ እንዳይደርሱ እፈራለሁ፡፡ መጀመሪያ እጃቸው ከምን? በኢሕአዴግ የተማረርንባቸውን ነገሮች እንዴት እንደሚቀርፉ አሁኑኑ ይንገሩን፡፡
የቁጥር ጫወታ
ኢሕአዴግ የፖለቲካ ምሕዳሩን አጥብቦታል፡፡ የፖለቲካምሕዳሩን ማጥበቡ የተጫዋጮችን ቁጥር ይቀንሰዋል ወይ ስንል ‹‹አይሆንም›› ነው መልሱ፡፡ አሁንም ሰዉ በልቡ ተቃዋሚ ነው፡፡ችግሩ ተሰባስቦ የሚያሰባስብ ቁርጠኛ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ነው ወይስ አሁንም ተቃዋሚዎች የአባላት ቁጥርን የማሳደግ ፋይዳአልተገለጸላቸውም? ተቃዋሚዎች የአባላት ቁጥር ለማሳደግ የሚያደርጉት ምንም ጥረት የለም፡፡ እንዲያውም አሁን፣ አሁን ከተቃዋሚፓርቲዎች አባላት ቁጥር ይልቅ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር የሚበዛ ይመስለኛል፡፡
የሕብረት ጫወታ
በነገራችን ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ቁጥር ብዙ ያደረገውተቀራርበው መነጋገር አለመቻላቸው፣ ሁሉም የፓርቲዎቹ መስራቾች መሪ መሆን ስለሚፈልጉ እና የተቃውሞ አባዜ ስለተጠናወታቸው እንጂፕሮግራማቸውን ቢናበቡ በአብዛኛው ልዩነት የለውም፡፡ በመድረክ ስር የተጠለሉትን ብሔር ተኮር እና ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲዎችስንመለከት እውነታውን ማረጋገጥ አንችላለን፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ሕብረት መፍጠር በመቻላቸው ያለምን ዝግጅት፣ ምሕዳሩ በጣምበጠበበት የምርጫ 2002 ወቅት የተሻለ ድምጽ ማግኘት ችለው ነበር፡፡
ለዚህ ነው እነዚህን ቅሬታዎቻቸንን የሚያሟሉ ተቃዋሚዎችለማግኘት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ማውጣት የሚያስፈልገው፡፡

እናም ይህችን እስከ ቀጣዩ ምርጫመዳረሻ ያለችውን ጊዜ ተቃዋሚዎች የአባላቶቻቸውን ቁጥር በማሳደግ እና እርስ በእርሳቸውም በመዋሃድ ትልቅ የተቃዋሚ ስብስብመፍጠር ይችሉ ነበር፡፡ ከዚያም ኢሕአዴግ አጠበብኩት የሚለውን ምሕዳር ጥቅጥቅ ብለንበት፣ የማጭበርበሪያ መንገድ አሳጥተነው፣ያለሁካታ ምርጫችንን እናሸንፍ ነበር፡፡ ያሸነፍነውን አልሰጣችሁም ካለን ያኔ ነፍጣችንን አንግተን ጫካ ለመግባት ከአሁን የተሻለምክንያት አገኘን ማለት አይደለም? ችግሩ ይሄንን መጣጥፍ ማን ወስዶ ለተቃዋሚዎች ይሰጥልኛል?