የግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ መልኩ በማካሄድ መግለጫ አወጣ
የግንቦት 7 የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄ ከተለያዩ ክፍለ አለማት በተወከሉ አባላቶቹ አማካኝነት ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ መልኩ ማካሄዱ የታወቀ ሲሆን በዚህ የ2 ቀን ውሎ ጉባኤ የድርጅቱን የ 2 አመት የስራ ክንዋኔ ገምግሟል፡፡ የንቅናቄውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመመልከት ጥንካሬውን የበለጠ ለማጥበቅ ድክመቶችን ለማረም እና ለማስወገድ ውሳኔዎችን ወስኗል። በዚህ ጉባኤ ከማናቸውም ጉዳይ በላይ ትኩረት የተሰጠው ነጥብ እየገዘፈ የሄደውን የወያኔን ፀረ- ኢትዮጵያ ፣ ዘረኛና አምባገነናዊ አመለካከቱና ድርጊቱ ላይ መሆኑም የደረሰን ዘገባ አስታውቋል።
ጉባኤው፡ ዛሬ በሀገራችን የነገሰው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ረጅም ታሪክ ውስጥ በአምባገነንነቱ፤ በዘራፊነቱ ፤በዘረኝነቱና በፀረ-ኢትዮጵያዊነቱ ተወዳዳሪ የሌለው አገዛዝ ነው በማለት የፈረጀው ሲሆን አገዛዙ እየዋለና እያደረ ዘረኝነቱን ወርቅ በሚለው ህዝብ አሻግሮ፣ ወርቅ በሚለው ጎጥ ላይ አራምዶ፣ወርቅ ወደሚለው ዘረኛ ቤተሰብ ማውረዱን ገልጿል።
የንቅናቄው ጉባኤ ይህ በወያኔ የተፈጠረ እጅግ አሳሳቢ የሆነ ከዜጎች መብትና ጥቅም መገፈፍ ፣እንዲሁም ከሀገር ህልውና ጋር የተሳሰረ አደጋ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ አሳሳቢ ሆኖ ማግኘቱን ገልጾ በሀገር ውስጥም ሆነ ሀገር ውጭ የሚገኘው፣ ነፃነቱን ሀገሩንና ክብሩን የሚወድ ዜጋ በሙሉ ከግንቦት 7 ንቅናቄ እና ከግንቦት 7 ጋር በፀረ ወያኔነት ከተሰለፉና ከሚታገሉ ሀይሎች ጎን በመቆም ማንኛውንም አይነት ተሳትፎ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ድርጅታዊ ጥሪውን አቅርቧል።