“ስደት በቃ!” እንበል፤ ኢትዮጵያችንን ከወያኔ እንንጠቅ!!!

ስደት የኢትዮጵያዊያን የመከራ ህይወት አካል ሆኗል። የነፃነት እጦት፣ የኑሮ መክበድ እና ተስፋ ማጣት ኢትዮጵያዊያን ከአገራቸው ለመሸሽ በረሃ የማቋረጥን እና ባህር የመሻገርን ድፍረት ሰጥቷቸዋል። ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያዊያን ሲሰደዱ የነበሩ ቢሆንም ስደት እንዳሁን የከፋበት ጊዜ የለም። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መከራ እየሸሹ በሱዳን እና ሊቢያ የበረሃ አሸዋዎች ውስጥ ተቀብረዋል። ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በትናንሽ ጀልባዎች ታጭቀው ወደ የመን ሲሻገሩ ቀይ ባህር ውስጥ ሰጥመው ቀርተዋል። እንዲሁም በርካቶች በተመሳሳይ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ የሜዲትራኒያን ባህር አሳዎች ቀለብ ሁነዋል።

የኢትዮጵያዊያን ዘግናኝ ስደት ታሪክ ቢፃፍ ብዙ ድርሳናት ይወጡታል። ደቡብ አፍሪካ ድረስ በእግር ለመጓዝ ደፍረው ተነስተው፤ መንገድ ጀምረው በድካም፣ ረሃብና ጥም የተፈቱ፤ በጉልበተኞች የተዘረፉ፣ የተደፈሩ፣ የተገደሉ ቤቱ ይቁጠራቸው።

ተሳክቶላቸው አሰቡት አገር የደረሱትም ቢሆንም ሸሽተው ከመጡት አፈናና ጭቆና የባሰ የጠበቃቸው ብዙዎች ናቸው። በአሁኑ ሰዓት በሳዉዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ አስር ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች አሉ ተብሎ ይገመታል። እየደረሰባቸው ያለው መከራ ዘግናኝ ነው። ግማሽ ያህሉ ወደ አገራቸው መመለስ ቢፈልጉም አልቻሉም። “የኢትዮጵያ መንግሥትን እንወክላለን” የሚሉ የወያኔ ዲፕሎማቶች ለኢትዮጵያዊያን ደንታ የላቸውም። “አናውቃችሁም” ብለዋቸዋል። ከብዙ መከራና እንግልት በኋላ ኬንያና ዩጋንዳ የደረሱት ኢትዮጵያዊያንም ከፊሎቹ ታስረዋል፤ ከፊሎቹ ደግሞ በዘወትር ድብብቆሽ የሰቀቀን ህይወት እየመሩ ነው።

ራቅ ያሉት የአረብ አገሮች ቀርቶ እንደ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ የመን፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ ዓይነቶች በባህልም፣ በመልክም በእምነትም ይቀርቡናል የምንላቸው ጎረቤቶቻችን ሳይቀር ንቀውናል። ጎረቤቶቻችንም ኢትዮጵያዊያን ውርደትን፣ ስቃይና እና መከራን የሚቀበሉባቸው አገራት ሆነዋል። አገርም ሆነ መንግሥት የሌለን የተናቅንና የተዋረድን ህዝብ ሆነናል።

ምንድነው ችግሩ? ኢትዮጵያዊያንን ወደ ስደትና መከራ የሚገፋቸው ማነው፣ ምንድነው? ኢትዮጵያዊያንን ወደ ስደት የሚገፏቸው ሶስት ነገሮች ናቸው።

  1. የነፃነት እጦት – ወያኔ ለኢትዮጵያ ህዝብ ባዕዳን ወራሪዎች የነበራቸውን አዘኔታ ያህል እንኳን የለውም። ዘረኝነትን ዋነኛው የአገዛዙ ፓሊሲ በማድረግ ዜጎችን በተለያዩ እርከኖች መድቧቸዋል። ኢትዮጵያ የጥቂት “ወርቆች” መፈንጫ ነች። ሌሎች በወያኔ የተናቁ፣ የተዋረዱና የተገፉት ስደት ምርጫቸው ነው።
  2. ድህነት – ለተመረጡት ኢትዮጵያ ጮማ የሚቆረጥባት፣ ወተት የሚፈስባት አገር ናት። ወያኔዎች በዘረፉት ሃብት የሚገነቧቸውን ቪላዎች፤ የሚነዷቸውን መኪናዎች ማየት ራሱ ያሳምማል። በአንፃሩ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ኑሮ ግን በከፍተኛ ፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው። ወደ አረብ አገራት የሚጓዙ እህቶቻችን እዚያ የሚጠብቃቸው ሥራ ምን ያህል ከባድና አዋራጅ እንደሆነ እያወቁ ተጋፍተው፣ ተለማምጠው፣ ለደላላ ከፍለው ይሄዳሉ። የወያኔ “ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት” ይህንን ሥራ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ለኢትዮጵያዊያን መፍጠር አልቻለም።
  3. ተስፋ ማጣት – በተለይ ወጣቶች ያጡት የዛሬ ኑሮዓቸውን ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋቸውንም ጭምር ነው። የወያኔ የቁጥር ጨዋታ የማንንም ልብ ማማለል አልቻለም። ከራሱ ከወያኔ በስተቀር ነገ ከዛሬ የተሻለ ይሆናል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ የለም። ተስፋ ሲሟጠጥ ሁሉም ነገር ይናጋል። ተስፋ ማጣት የኢትዮጵያዊውያን ወጣቶችን አቋም አናግቷል። ወጣቶቻችን መሄዳቸውን – ከኢትዮጵያ መራቃቸውን – እንጂ ወደ የት እንደሚሄዱ ማስተዋል ተስኗቸዋል። ይህ እጅግ አስደንጋጭ ነገር ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተሰዳጁ ስብጥርም ተቀይሯል። ከጥቂት ዓመታት በፊት ርቆ ተጓዡ ባብዛኛው የተማረውና ከተማ ቀመሱ ወጣት ነበር። ዛሬ ግን አርሶአደሮች ጎጆዓቸውንና ልጆቻቸውን ጥለው ደቡብ አፍሪካ ሲነጉዱ ማስተዋል ቀላል ነው። የወያኔ ደላሎችም አንዴ በኳስ ጨዋታ ሰበብ ሌላ ጊዜ ደግሞ በድብቅ እናሻግራችኋለን እያሉ ጥሪታቸውን ይዘርፋሉ። እንዲህ በተዘረፈ ገንዘብ በተገባ ህንፃ እየተምነሸነሹ ስለ ኢኮኖሚው ፈጣን እድገት ይደሰኩራሉ። ነገሩን በአንክሮ ማስተዋል ያስቆጫል፤ ያንገበግባል።

ይህ ሁኔታ በዚሁ እንዲቀጥል መፍቀድ የለብንም!!! በጭራሽ መፍቀድ የለብንም!!! ፈጽሞ!!! ከማን ነው የምንሸሸው? በስደታችን እና በመከራችን የሚጠቀመው ማነው?

በኛ ስቃይ የሚደሰተው ወያኔ ነው። ስንሰደድለት አገሩ ይሰፋዋል። ወያኔ ማረስ ባይችል መሬታችንን ለህንድና ለቻይና ገበሬ መሸጥ አያቅተውም። የቀን ሠራተኛ ካነሰውም ከፊሊፒንስ ያመጣል። የኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ መሰደድ የወያኔ ፌሽታ ነው። ኢትዮጵያዊያን በስደት አውሬ ቢበላቸው፤ በረሃ ቢውጣቸው፤ ባህር ውስጥ ቢሰጥሙ፤ ቢታሰሩ፣ ቢጉላሉ ደስታው ነው። ድንገት መከራዎችን አልፈው ከተሳካላቸው ደግሞ ለዘመዶቻቸው ገንዘብ እንዲልኩ በማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ይወጣባቸዋል። ከስደተኞቹ መካከል ተፍጨርጭረው በእግራቸው የቆሙ ከተገኙ ደግሞ “ልማታዊ ኢንቨስተር” እንዲሆኑ በመጋበዝ የብዝበዛ ወፍጮው አካል ያደርጋቸዋል።

ስንቴ እንሞኝ? እንደምን አገራችንን ለቀንለት ወያኔ በህዝባችንና በገዛ ራሳችን ህይወት ላይ እንዲሰለጥን እንፈቅዳለን? መቼ ነው አገራችንን፣ ህይወታችንን፣ ተስፋችንን ከወያኔ ነጥቀን የራሳችን የምናደርገው?

የተሰደደው በያለበት ትግሉን አጧጡፎ በድል እንዲመለስ እናድርግ። በያገሩ በችግር ላይ ለሚገኙ ስደተኞች እንድረስላቸው፤ “አለንላችሁ፣ ከጎናችሁ ነን!” እንበላቸው።

ስደት በቃ እንበል!!! ኢትዮጵያ የኛ፤ እኛም የኢትዮጵያ ነን። በዚህ የምታምኑ ሁሉ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲንቅናቄን ተቀላቀሉ።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!