የኢትዮጵያ ወጣቶች 2004 የለውጥ አመት ይሆናል ማለታቸው ተዘገበ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቶ ጫፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያዊያን የመከራ ዘመን ማብቂያው 2004 ዓም ሊሆን እንደሚገባው በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ወጣቶች ገለጹ። ዘጋቢዎቹ ከየስፍራው አሰባስበው የላኩትን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ የ ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት እንደዘገበው የኢትዮጵያዊያን መከራ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገድ ዘንድ ወጣቶቹ 2004 ታሪክ ሳይሰራበት እንዳያልፍ ከፍተኛ ምኞት እንዳአላቸው ገልጹአል።

ኢሳት በዘገባው ላይ እንደገለጸው በአረቡ አለም የታዬው ለውጥ፣ በትዮጵያም ይመጣል ብለው የሚተማመኑት ወጣቶች የፖለቲካ ደርጅቶችን መመሪያ ሳይጠብቁ በራሳቸው ለመነሳሳት እንደሚፈልጉም መግለጻቸው ታውቁአል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ የኢሳት ዘጋቢዎች አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች ለውጥ የሚፈልጉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ተጠይቀው ብዙዎች፣ ኑሮውን፣ ስራ አጥነቱን፣ የመብት አፈናውንና በየጊዜው እየሰፋ የሚሄደውን የሀብታሙንና የደሀውን ልዩነት ጠቅሰዋል። በሃገሪቱ ደቡብ ክፍል የሚገኙት ወጣቶች በአብዛኛው ረሀቡንና ስራ አጥነቱን በዋና ምክንያትነት ሲያቀረቡ፣ በኦሮሚያ የሚገኙት ደግሞ የመብት አፈናውን በዋናነት ጠቅሰዋል።

በሌላም በኩል የአዲስ አበባ ወጣቶች በርካታ ችግሮችን ሲዘረዝሩ፣ ደጋግመው የሚጠቅሱት ግን ወያኔ ኢህአዴግ የአዲስ አበባን ህዝብ በምርጫ 97 ለደረሰበት ሽንፈት እየተበቀለና እየቀጣው መሆኑ የሚገልጽ ነው የሚል መሆኑ ታውቁአል።

በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የኑሮ ውድነቱና ስራ አጥነቱ ወሳኝ ለሆነው ፍልሚያ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል ። ምንም እንኳ ወጣቶቹ የተለያዩ ምክንያቶችን ቢጠቅሱም፣ ሁሉም ግን ለውጥ እንደሚፈልጉና ለውጡም በያዝነው አዲስ አመት እንዲሆን እንደሚመኙ ለኢሳት ዘጋቢዎች ገልጸዋል።

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ የስልጣን ወምበርን ከተቆናጣጠበት ጊዜ ጀምሮ ለሃያ አመታት ኢትዮጵያዊያንን ወደ ባሰ አዘቅትና ጨለማ እየወረወረ እንደሆነ እጂግ በርካቶች የሚስማሙ ሲሆን ከዚህ መከራና ስቃይ መላቀቂያ መንገዱ አንድና አንድ ብቻ ነው፣ ይሄውም፣ የዘረኛውን አገዛዝ ከስሩ ነቅሎ መጣል በማለት አጥብቀው ይመክራሉ።