ዘረኛው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ የሱዳን ፕሬዝዳንት አልባሽር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሴራ ማስተባበሩን በማስተባበል እርስ በርሱ የሚቃረን መግለጫ አስወጣ

በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ያለው የጸጥታ ስጋት እስካለ ድረስ ምዕራባዊያን ለወያኔ አገዛዝ የሚያደርጉት ያልተገደበ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ድጋፍ እንደማይቋረጥበት የተገነዘበው የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ ቡድን፤ አሜሪካኖች የሱዳኑን ፕሬዝዳንት ጀኔራል አልባሽርን ከሥልጣን ያስወግዱ ዘንድ ብላሃት ማቀበሉን ከአሜሪካ ውጪጉዳይ መሥሪያቤት ሾልኮ በዊኪሊክስ መረጃ ድሬገጽ ላይ የወጣው ሠነድ ካጋለጠ ወዲህ የወያኔ የኮሚኒኬሽን ኤጀንሲና የወጪ ጉዳይ ሚንስትር መረጃውን ለማስተባበል ደፋ ቀና እያሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሎአል።

ከትናንትና ወዲያ ሃሙስ መስከረም 3 ቀን አገዛዙ ባወጣው የማስተባባያ መግለጫ መለስ ዜናዊ የሱዳኑን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ለማስወገድ ስለሚቻልበት ሁኔታ ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር አድርጎት የነበረውን ውይይት ሙልጭ አድርጎ ከመካዱም በላይ ቅሌቱን ያጋለጠውን መረጃ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አዛብቶ ያስተለለፈው የሃሰት ወሬ ነው በማለት የተለመደውን ቅጥፈቱን አስነብቦአል።

ከወያኔ አገዛዝ የወጣውን ይህንን ማስተባበያ አስመልክቶ የሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ በትናትናው ዕለት ባሳተመው ዘገባ ፤ መለስ ዜናዊ እንደፈረንጆች አቆጣጠር ጃኒዋሪ 30 2009 ከአሜርካ ውጪጉዳይ ሚንስትር የአፍሪካ ረዳት ሃላፊ ከሆኑት ከሚስቴር | Phil Carter| ፊሊ ካርተር እና በአመሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የሱዳን ጉዳይ ዳይሬክተር ቲም ሾርትለይ |Tim Shortley | በተገኙበት አልባሽርን ከሥልጣን ለማስወገድ አሜሪካ ሁለት ዜዴዎችን መጠቀም እንዳለባት መምከሩ በዊኪሊክስ የወጣው መረጃ የሚያመለክት ሆኖ ሳለ አገዛዙ ባወጣው የማስተባበያ መግለጫ ግን በወቅቱ አዲስ አበባ የነበሩት የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳዳር ያማማቶ የመለስን አስተያየት አዛብቶ እንዳስተላለፉ አስመስሎ ማቅረብ ጠቀሜታ የለውም ሲል ተሳልቆበታል።

ወያኔ የኢትዮጵያን ጥቅም ለሱዳን አሳልፎ በመስጠት ተቃዋሚዎች ላለፉት 20 አመታት በዛች አገር ፈጽሞ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ ለማድረግ የቻለ ሲሆን ርዝመቱ ከ 1600 አንድ ሺህ ስድስት መቶ ኪሎሜትር በላይ የሆነ ለም መሬታችንን በገጸ በረከትነት አሳልፎ እንደሰጠ ይታወቃል።

መለስ በአንድ በኩል ለአልበሽር ወዳጅ እየመሰለ እና የኢትዮጶያን ለም መሬት አሳልፎ እየሰጠ በሌላ በኩል አልበሽርን ከሥልጣን ለማስፈንገል ሴራ የሚሸርበው በሱዳን ውስጥ ሌላ ተጨማሪ አለመረጋጋት እንዲፈጠርና በቀጠናው ብቸኛ የሰላም አስከባሪ ሆኖ ገዝፎ ለመታየት የሚያደርገው ጥረት እንደሆነ መረጃውን የተመለከቱ ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።

በዊኪ ሊክስ መረጃ መሠረት መለስ ዜናዊ የአልበሽርን በዘር ማጥፋት ወንጀል ለአለም አቀፍ ፍርድ ቤት መቅረብ የተቃወመው በርሱ አገዛዝ ዘመን በሱማሌ ክልልና በተቀሩት የአገራችን ክፍሎች ለተፈጸመው ተመሳሳይ እልቂት እንደሚያስጠይቀው በመስጋት መሆኑን የአሜሪካ ባለስልጣናት ተገንዝበዋል።