የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አንዱአለም አራጌንና ታዋቂውን ጋዜጤኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያዊያን ታሠሩ፣ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያዊያኑ የታሰሩት ከግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው ተብሎአል

ያለህዝብ ፈቃድ ለዘመናት ሥልጣን ላይ ሆነው የህዝብና የአገራቸውን ደም የሚመጡ አምባገነኖችን የሥልጣን መሠረት እያናጋ የመጣው የሰሜን አፍሪካ ህዝባዊ አብዮት ያስደነገጠው የወያኔ አገዛዝ፤ ተመሳሳይ ህዝባዊ አመጽ ሊቀሰቀስብኝ ይችላል ከሚል ስጋት በአገር ውስጥ ተመዝግበው ሠላማዊ ትግል ለማካሄድ የሚንቀሳቀሱትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መሪዎችና፣ የዲሞክራሲ አክትቪስቶችን በገፍ ማሰር እንደቀጠለ የግንቦት 7 ዜና ዘጋቢ ከአዲስ አበባ በላከልን ዜና አስታወቀ። እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ባለፈው ረቡዕ መስከረም 3 ቀን የአንድነት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አንዱአለም አራጌንና ታዋቂውን ጋዜጤኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ አምስት ኢትዮጵያዊያን የታሠሩ፣ ሲሆን፣ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያዊያኑ የታሰሩት ከግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው ማለቱን ዘጋቢያችን የላከልን ሪፖርት ያመለክታል።

የኦሮሞ ፈደራሊስት ንቅናቄና የኦሮሞ ኮንግረስ ደጋፊዎችና አባላት ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት የተጀመረው ይህ የጅምላ እስር በተጠናከረ መልኩ ቀጥሎ፣ በ60 ዎቹ የ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘውን አርቲስት ደበበ እሼቱን በታሠረ ሳምንት ዕድሜ ውስጥ የአንድነት ፓርቲ ዋናጸሃፊ የሆኑት አቶ አንዱአለም አራጌ፤ ታዋቂው ጋዜጤኛ እስክንድር ነጋ፣ ዘመኑ ሞላ፣ ናትናኤል መኮንንና አሳምነው ብርሃኑ በአረመኔው አገዛዝ ታስረዋል።

የወያኔ አገዛዝ በአገሪቱ ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት እየከፋ ለመጣው የኑሮ ውድነት መላ እንዲያበጅለት በሠላማዊ ሠልፍ ለመጠየቅ ለመስከረም 21 ቀን የሠልፍ ፈቃድ የጠየቀው የመላው ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትም ከታሳሪዎቹ አንዱ እንደሆኑና በወያኔ የጸጥታ ሰዎች ታፍነው እንደተወሰዱ ታውቆአል።

ለወያነ የደህንነት ምንጮች ቅርበት ያላቸው የንቅናቄያችን መረጃ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት ይህ የጅምላ እሥር እርምጃ የተጀመረው የህወሃት ፖሊቲ ቢሮ በአገራችን ውስጥ ህዝባዊ አመጽ መፈንዳቱ አይቀሬ መሆኑን መረጃ ካሰባሰበ ቦኋላ፤ ተቃውሞ ሊያደራጅ ወይም ሊቀሰቅስ የሚችል ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴ በ ዕንጪጩ ለማምከን እርምጃ እንዲወሰድ በምስጥር ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ ካስተላለፈ ከቀናት ቦኋላ እንደሆነ ታውቆአል።

እንደመረጃ ምንጮቻችን አመጽ ለማምከን መወሰድ ስላበት እርምጃ በህወሃት ውስጥ ውይይት በተደረገበት ወቅት የሶሪያው መሪ ሃሰን አላሳድ ተቃውሞ ለማፈን እየተጠቀመበት ያለው አይነት እርምጃ መውሰድ አዋጭ ነው የሚል ነጥብ ተነስቶ እንደነበር ለማወቅ ተችሎአል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አንድነት ዲሞክራሲያዊ ድርጅት(ኢአዲድ) እና የመላው ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፤መስከረም 21 ቀን ለማካሄድ ያቀዱትን ሰልፍ አስመልከቶ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸውን ኢሳት ዘግቦአል።

እንደኢሳት ዘገባ የፓርቲዎቹ መግለጫ የሰልፉ ዋነኛ አላማ፤ ድህነትንና የኑሮ ውድነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች አገራችንን አስረው ለያዟት ማነቆዎች ዋነኛ ምክንያት የሆነውን የወያኔ ፓርቲ ፖሊሲና አሠራር አጥብቆ መቃወም ነው ተብሎኦል።

የፈቃድ ጥያቄ የገባለት የአዲስ አበባ መስተዳድር የህዝባዊ ስብሰባና ሰልፍ ፈቃድ ክፍል እስካሁን ምላሽ ባይሰጣቸውም፤ ወያኔ አለኝ በሚለው ህገ-መንግስት ሰልፍና ስብሰባ ለማከናወን ማሳወቅ ብቻ በቂ እንደሆነ ፓርቲዎቹ አስታውሰዋል።

ከጧቱ 3፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 8፡00 ሰዓት ድረስ በሚቆየው የ5 ሰዓታት ሰልፍ፤ እጅግ በርካታ ሰዎች በመውጣት ብሶታቸውን ያሰማሉ፤ በስርዓቱ ላይ ያላቸውንም ተቃውሞ ይገልፃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፓርቲዎቹ እንዳሉት ሰልፉ በተያዘለት ፕሮግራም ከተካሄደ፤ ከስድስት ዓመታት በሁዋላ በኢትዮጵያ የሚደረግ የመጀመሪያው የተቃውሞ ሰልፍ ይሆናል ተብሎአል።